የአሜሪካው የመስከረም 11 ጉድ!

0
1580

መስከረም 1 ቀንን አይረሴ ከሚያደርጉ የቅርብ ታሪኮች መካከል በአሜሪካዎቹ የኒውዮርክ መንትዮቹ ህንፃዎች ላይ ተፈፀመ የተባለው የሽብር ጥቃት በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል፡፡ በዓለማችን ላይ የታሪክ አቅጣጫን የቀየረው ይህ ክስተት በብዙ አሉባልታዎችና ምስጢሮች የታጀበ ነው፡፡ ጥቃቱን ማን ፈፀመው? የአሜሪካ መንግስትስ እጁ አለበት ወይ? የሚያስብሉ ነጥቦች በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ 20 ዓመት ስለሞላው ይህ ውስብስብ ክስተት ግዛቸው አበበ ይህን አስፍረዋል፡፡

ሰሞኑን ከወደ አሜሪካ አንድ አስገራሚ ዜና ተሰምቷል። ዜናው በኮሮና ምክንያት ተቋርጦ የነበረ አንድ የፍርድ ሒደት ሊቀጥል መሆኑን የሚያሳውቅ ነው። ይህ የፍርድ ሒደት ከሃያ ዓመታት በፊት ከተፈጸመና በሽብር ጥቃትነት ከተፈረጀ አውዳሚ ጥቃት ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ዜና ይፋ ያላደረጋቸው ጉዳዮች አሉ። ጉዳዮቹ የተድበሰበሱት በዚህ ጥቃት ዙሪያ በርካታ ምስጢሮችና አጠያያቂ ጉዳዮች ስላሉ ነው።

የ9/11 የሽብር ጥቃት ተብሎ የሚጠራው ይህ ጥቃት፣ በፈረንጆች አቆጣጠር መስከረም 11/2001፣ ወይም የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት መግቢያ እየተከበረ በነበረበት መስከረም 1 ቀን 1994 ዓም ከሰዓት በኋላ የተፈጸመ ነው። በአሜሪካ ምስራቃዊ ክፍል የሰዓት አቆጣጠር ከጥዋቱ 7፡59 ሲሆን የአሜሪካን አየር መንገድ ንብረት የሆነ፣ የበረራ ቁጥር AA-11፣ ቦይንግ-767 ጀት አውሮፕላን 92 መንገደኞችን አሳፍሮ ከቦስተን ሎጋን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነሳ (በዚህ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው የሰዓት አቆጣጠር በሙሉ በምስራቃዊ አሜሪካ የቀን ሰዓት አቆጣጠር Eastern Daylight Time-EDT-AM መሆኑ ልብ ይባል)።

የዚህ በረራ መዳረሻ ሎስ አንጀለስ ነበረ። ነገር ግን 8:19 ሲሆን ረዳት አብራሪው የአውሮፕላኑን መጠለፍ ለአየር መንገዱ አሳወቀ፤ አየር መንገዱም ለኤፍ.ቢ.አይ. ይህንኑ ገለጠ። 8:40 ላይ የአሜሪካ ፌደራላዊ የበረራዎች አስተዳር ለሰሜን አሜሪካ የአየርና ሕዋ መከላከያ ዕዝ (North American Aerospace Defense Command-NORAD) ለተባለው ወታራዊ ክፍል የበረራውን መጠለፍ አሳወቀ። ይህን ተከትሎ ኹለት ተዋጊ ጀቶች ከኬፕ ኮድስ ኦቲስ ብሔራዊ የአየር መከላከል መደብር ተነስተው መብረር ጀመሩ። ጀቶቹ ምንም ዓይነት ዕርምጃ ሳይወዱ ወደ መደብራቸው ተመልሰው አረፉ። 8:46 ላይ የተጠለፈው ቦይንግ-767 ጀት አውሮፕላን የዓለም የንግድ ማዕከል መንታ ሕንጻዎች ተብለው ከሚጠሩትና እያንዳንዳቸው ባለ 110 ፎቅ ከሆኑት ኹለት ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች አንደኛው፣ ማለትም በሰሜን በኩል ከሚገኘው ሕንጻ (North Tower) ላይ መመሰጉ በቴሌቪዥን መስኮቶች ላይ ታዬ። ይህ ጀት አውሮፕላን መጠለፉ በኤፍ.ቢ.አይ. ከታወቀ ከ26 ደቂቃዎች በኋላ ነው ይህን አደጋ ያደረሰው።

የበረራ ቁጥር 11፣ ቦይንግ-767 ጀት አውሮፕላን መጠለፍና ከሕንጻው ጋር የመላተም ዜና አደጋ ተብሎ እየተዘገበ ባለበትና በዓለም ዙሪያ ሚሊዮኖች ዐይኖቻቸውን በቴሌቪዥን ላይ አፍጥጠው ነገሩን በመከታተል ላይ በነበሩበት ጊዜ ሌላ መንገደኞችን የጫነ፣ የዩናይትድ አየር መንገድ ንብረት የሆነ፣ በረራ ቁጥሩ UA-175 ቦይንግ-767 ጀት አውሮፕላን በኹለተኛው ሕንጻ (South Tower) ላይ ሲመሰግ በቀጥታ ስርጭት ታዬ። ይህ ቦይንግ-767 ጀት አውሮፕላን 8:14 ላይ 65 መንገደኞችን ጭኖ ወደ ሎስ አንጀለስ ለመብረር ከቦስተን አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ጥቂት ለማይባል ጊዜ በረራ ካደረገ በኋላ 9:03 ላይ ነው ከሕንጻው ጋር የተላተመው።

ይኸኛው አውሮፕላንም ያለ ከልካይ ወደ 50 ደቂቃዎች በአየር ላይ ቆይቶ ነው አደጋውን ያደረሰው። ይኸኛው ጥቃት የተከሰተው ከአንደኛው ጥቃት በ18 ደቂቃዎች ብቻ ዘግይቶ ስለነበረ የዜና ማሰራጫዎች ጉዳዩን አደጋ ማለታቸውን ትተው አሜሪካ እየተጠቃች ነው ሲሉ ተደመጡ።

8:20 ላይ ከዋሽንግተን ዱላስ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ወደ ሎስ አንጀልስ የሚበር፣ 59 መንገደኞችን የጫነ የአሜሪካን አየር መንገድ ንብረት የሆነ፣ በረራ ቁጥር AA-77 ቦይንግ-757 ጀት አውሮፕላን ከ17 ደቂቃች በኋላ (9:37 a.m) ከፔንታጎን ጋር ተላትሞ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ተዘገበ።

8:41 ላይ ዬናይትድ አየር መንገድ ንብረት የሆነ፣ 44 መንገደኞችን የጫነ፣ በረራ ቁጥር UA-93 ቦይንግ-757 ጀት አውሮፕላን ከኒውጀርሲ-ኒዋርክ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ 10:03 ላይ ፔንሰልቫን ሻንካስቪሊ ሜዳ ላይ መከስከሱ ተነገረ። አውሮፕላኑ የተከሰከሰው ተሳፋሪዎቹ የሌሎቹን የተጠለፉ አውሮፕላኖች ዕጣ ሰምተው ስለነበረ ከጠላፊዎቹ ጋር ግብግብ በገጠሙበት ወቅት አውሮፕላኑ ከቁጥጥር ውጭ በመሆኑ ነው ይባላል።

በሌላ በኩል ደግሞ አውሮፕላኑን የከሰከሱት ጠላፊዎቹ መሆናቸውንና ይህን ያደረጉትም ተሳፋሪዎቹ በፈጠሩት ግብግብ አውሮፕላኑ ወደ ታለመለት የጥቃት ዒላማ መድረስ አለመቻሉን በመረዳታቸው በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተገፋፍተው ነው ሲባል ይሰማል። የአሜሪካ መንግስት የሌሎችን አውሮፕላኖችን መጠለፍ እየሰማ ዝም ባለበት ሰዓት የዚህ አውሮፕላን ተሳፋሪዎች የጠለፋ ወሬ ሰምተው እርምጃ ወሰዱ መባሉ ብዙ አነጋግሯል።

የዚህ አውሮፕላን ጠላፊዎች ዒላማ ኋይት ሃውስን ወይም የአሜሪካ ምክር ቤት ሕንጻ ወይም ካምፕ ዴቪድ የሚገኘውን ፕሬዝዳንታዊ ማረፊያ ወይም ከአሜሪካ የኒውክለር ኃይል ማመንጫዎች በአንዱ ላይ ነው የሚሉ የተለያዩ ግምቶች የተነገሩ ቢሆንም፣ ትክክለኛው ግቡ ምን እንደነበረ ማረጋገጫ አልተገኘለትም። ነገር ግን ይህ የበረራ ቁጥሩ 93 የሆነ ጀት አውሮፕላን በመጀመሪያ ተይዞለት የነበረው የበረራ ሰዓት 8:00 የነበረ መሆኑና የሌሎች አውሮፕላኖች መጠለፍ ሲሰማ በረራው እንዲዘገይ መደረጉ፣ ከዚያም በ40 ደቂቃዎች ዘግይቶ በረራውን እንዲቀጥል መደረጉ ይፋ ተደርጓልና ምን መተማመኛ ተገኝቶ ነው በረራው የቀጠለው? የሚለው ጥያቄ ተገቢውን መልስ የሚሻ ነው።

መስከረም 11 በመጣ ቁጥር በአሜሪካዋ ኒውዮርክና በሌሎችም አካባቢዎች ዕለቱ ሽብርን በማውገዝ፣ የሞቱትን በመዘከርና አሜሪካ ጠላቶቿን በሚያሳምም ቅጣት የምትበቀል አገር መሆኗን የሚያሳዩ ዝግጅቶች በማቅረብ ዕለቷን የምትከበር መሆኗን ታላላቅ መገናኛ ብዙኃን እየነገሩን ዓመታት ተቆጥረዋል። ነገር ግን፣ ይች ዕለት የአሜሪካን መንግሥት የሚቃወሙ፣ የአሜሪካን መንግሥት በቸልተኝነት ተጠያቂ የሚያርጉ ወይም የአሜሪካ መንግሥት ጥቃቱን ሊካሄድ መሆኑን እያወቀ መከላከል ሲገባው ችላ ብሎ ጦርነት ለማካሄድ ሰበብ ይሆነው ዘንድ ቤተሰቦቻችንን አስጨርሶብናል የሚሉ ወገኖችም ጭምር ሰልፎችን ያካሂዳሉ።

ከዚህም አልፎ እነዚህ የታፈኑ ሰልፎች በጥቃቱ ውስጥ አሜሪካዊ ሥውር እጆች እንዳሉበት የሚናሩ፣ የአሜሪካን መንግሥት በሴራ ሸራቢነት የሚወነጅሉና ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባቸው የአሜሪካ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚጠይቁ ሰልፈኞችም ድምጻቸውን ለማሰማት የሚሞክሩባቸው አጋጣሚወች ቢሆኑም፣ የምዕራቡ ዓለም ታላላቅ መገናኛ ብዙኃን የነዚህን ሰልፈኞች ድምጽ ለማስተጋባት ፈቃደኞች ሳይሆኑ ለረዥም ጊዜ ዘልቀዋል። ይህም በመሆኑ በሌላው ዓለም የሚገኙ መገናኛ ብዙኃንም ትኩረት ያልሰጡት ነገር ሆኗል። እንዲያውም ሰምተውት የማያውቁት ጉዳይ ሊሆን ይችላል።

ይህ ጽሑፍ መስከረም 11/2011 በተካሄደው ጥቃት ዙሪያ ከተነሱትና ትኩረት ካልተሰጣቸው አወዛጋቢ ጉዳዮች መካከል አንዱን የሚያስታውስ ነው። በዓለም ሚዲያዎች ሆነ ተብሎ ችላ የተባሉት እነዚህ እውነታዎች ለብዙዎቻችን እንግዳ ታሪኮች ሊሆኑ ይችላሉ። ምክንያቱ ደግሞ አንድም እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን የሌላው ታዳጊ ዓለም ሕዝብ ወሬዎችን የሚያገኘው የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች ቅርንጫፍ ከሆኑትና በብዙ ቋንቋዎች ከሚሰሩት ቪኦኤን፣ ዶቸቨለን፣ ቢቢሲን፣ ወዘተ. ከመሳሰሉት ሚዲያዎች ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአገራችንና በሌላው ውስጥ ያሉ የግልም ሆኑ የመንግሥት ሚዲያዎች ፈረንጆች በሚዲያዎቻቸው በኩል ያንቆረቁሩትን ወሬ በቀጥታ የማቅረብ ልምድ ያዳበሩ በመሆናቸውና ታላላቆቹ የፈረንጆቹ ሚዲያወች ያላወሩት ወሬ ሁሉ ሐሰት መስሎ የሚታያቸው በመሆናቸው ነው።

ከዚህ ሌላ ብዙዎቹ የታዳጊው ዓለም መገናኛ ብዙኃን ግራና ቀኝ አይቶ ማመዛዘንንና በሌላ ወገን በኩል ምን ይነገራል ብሎ ቆም ብሎ ማሰብን ልምድ ስላላደረጉ የመስከረሙን ጥቃት ተከትሎ ከአሜሪካና ከሌላው የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ የሚንቆረቆረውን እንደ ወረደ ከማቅረብ ውጭ ሌላ ሥራ ሲሠሩ አይታዩም።

ከነዚህ የታፈኑ ሰልፈኞችና ሰልፎች በተጨማሪ ሌሎች ትኩረት የተነፈጉ ነገር ግን በተደራጀ ሁኔታ የአሜሪካን መንግሥት ተጠያቂ ለማድረግ የሚሠሩ ቡድኖችም አሉ። እነዚህ ቡድኖች ‘የ9/11 እውነት አፈላላጊ ንቅናቄዎች’ (9/11 Truth movement) ተብለው በጅምላ የሚጠሩ ሲሆን፣ አደረጃጀታው በየሙያቸው ላይ የተመሠረተ ነው። እነዚህ ቡድኖች ችግሩን በሚመለከት ሙያዊ ምርመራና ምርምር በማድረግ ተሰውሯል የሚሉትን ሴራ በማነፍነፍ ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚሠሩ ምሁራን ያዋቀሯቸው ሲሆኑ፣ ከነዚህ ቡድኖች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።

Pilots for 9/11 Truth
Architects & Engineers for 9/11 Truth
9/11: Press for Truth
Scholars for 9/11 Truth
Scholars for 9/11 Truth and Justice
9/11 Citizens Watch
Military Officers for 9/11 Truth
Medical Professionals for 9/11 Truth
Christians for 9/11 Truth

የመስከረሙን አደጋ በሚመለከለት በሰፊው ከሚሰማው ዜና እና ታሪክ ለየት ያለውን ጉዳይ አስመልክቶ በርካታ ፊልሞች በብዙ ቋንቋዎች ተዘጋጅተው በመቶ ሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ታይተዋል፤ በርካታ መጽሐፍትም ተጽፈዋል። አደጋውን አስመልክቶ ውዝግብ ካስከተሉት ጉዳዮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።
የአደጋው ውድመት ስፋት ድብቅ መሆን፣
በጠላፊዎቹ ዙሪያ የተነሳው ውዝግብ፣
የመንትዮቹ የዓለም ንግድ ማዕከል ሕንጻዎች ሙሉ በሙሉ በተመሳሳይ መንገድ መደርመስ፣
ምንም ዓይነት ጥቃት ያልደረሰበት የዓለም ንግድ ማዕከል ቁጥር ሰባት፣ የሌሎች ሕንጻዎችና ድልድዮች፣ ወዘተ. መደርመስ
የፔንታጎን በቀላሉ መጠቃት፣
በተጠለፉት አውሮፕላኖች ውስጥ ተሳፋሪ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች አደረጓቸው የተባሉት የስልክ ጥሪዎች፣
የአውሮፕላኖቹ መረጃ መሰብሳቢያ ሳጥኖች በሙሉ የውኃ ሽታ መሆን፣
በ9/11 ጥቃት ጊዜ የአሜሪካ መንግሥት ማድፈጥ፤
ጉዳዩ ጥልቀት ያለውና ብዙ ዝርዝሮችን የያዘ ስለሆነ በዚህ ጽሑፍ የምናወሳው አውሮፕላኖቹን ጠልፈው አጥፍተው ጠፍተዋል ከተባሉት ግለሰቦች ውስጥ ዜናውን አነጋጋሪ ስላደረጉት ሰባት ሰዎች ጉዳይ ብቻ ይሆናል።

ቢቢሲ አውሮፕላን ጠልፈው አጥፍተው ጠፍተዋል ብሎ ኤፍ.ቢ.አይ. በአደጋው ማግስት ስማቸው ይፋ ካደረገባቸው ሰዎች መካከል አራቱ በሕይዎት ያሉና ከጉዳዩ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳልነበራቸው በመናገር እሮሮ እያሰሙ መሆኑን በፈረንጆቹ አቆጣጠር መስከረም 23/2001 ላይ (የ9/11 አደጋ በተፈጸመ በ12ኛ ቀን) ዘገበ። ብዙም ሳይቆይ ሲኤንኤን አጥፍተው ጠፍተዋል ከተባሉት 19 ሰዎች መካከል ስድስቱ በሕይወት መኖራቸውንና አንዱ ደግሞ ከመስከረሙ ጥቃት በአንድ ዓመት ቀደም ብሎ በአውሮፕላን አደጋ መመሞቱን ዘገበ። ግለሰቦቹ ከነ አስገራሚ አጋጣሚያቸው የሚከተሉት ናቸው።

(1) ዋሊድ አልሸኽሪ- በረራ ቁጥሩ 11 የሆነውን ቦይንግ ከጠለፉት 5 ሰዎች አንዱ ነው ተብሎ የተነገረለት ዋሊድ አል-ሸኽሪ የሳዑዲ አረቢያ ዜጋ የሆነ፣ እዚያው አሜሪካ ውስጥ የበረራ ሥልጠና የወሰደ፣ ከአደጋው በአንድ ዓመት ቀደም ብሎ አሜሪካን ለቆ የወጣ እና ሳዑዲ ውስጥ በአብራሪነት ሥራ ላይ የተሠማራ ሰው ነው።

የ9/11 ጥቃት እንደተፈጸመ የተለቀቀውን የኤፍ.ቢ.አይ. መግለጫ ተከትሎ የዚህ ሰው ምስል በጋዜጦችና በቴሌቪዥን መሰኮቶች መታየት ጀመረ። በዚህ ጊዜ እሱ ሞሮኮ ራባት ውስጥ ተጨማሪ የበረራ ሥልጠና በመከታል ላይ ነበረ። የእሱን ምስል ያካተተው ዜና ከተለቀቀ በኋላ ከደሙ ንጹህ መሆኑንና ከሚባለው የሽብር ጥቃት ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንደሌለው ለመግለጽ የአሜሪካና የሳዑዲ-ዓረቢ ባለሥልጣናትን ለማነጋር እንዲሁም በሚዲዎች ላይ ሃሳቡን ለመግለጽ ተሯሩጧል።

(2) አብዱልአዚ አልኦማሪ- በረራ ቁጥሩ 11 የሆነውን ቦይንግ ከጠለፉት መካከል አንዱ ነው ተብሎ በኤፍ.ቢ.አይ. ከተጠቀሱትና በቦታው እንዳልነበረ ከታወቁት ሰዎች መካከል ኹለተኛው ሰው ነው። ይህ ሰው በምህንድስና ሙያ የተመረቀና በሳዑዲ አረቢያ ቴሌኮም ካምፓኒ ውስጥ የሚሠራ ነው። የዚህ ሰው ፓስፖርት ከስድስት ዓመት በፊት አሜሪካ ዴንቨር ውስጥ በትምህርት ላይ እያለ መጥፋቱ ታውቋል።

ይህ ሰው ፓስፖርቱ መጥፋቱን አሳውቆ ሌላ ፓስፖርት አውጥቶ ወደ አገሩ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተመልሶ በሥራ ላይ ተሰማርቶ ያለ ሰው ነው። በኤፍ.ቢ.አይ. ይፋ የተደረገው የጠላፊዎቹ ዝርዝር የዚህን ሰው ሙሉ ስም፣ የልደት ቀን፣ ዜግነት እና ሥራ በትክክል ቢያስቀምጥም ከመረጃው ጋር የተያያዘው ምስል ግን የእሱ አልነበረም። ይህ ሰው “… አኔ በሕይወት አለሁ፣ አኔ አውሮፕላን የማብረር ችሎታ የለኝም… እኔን ከዚህ ጥቃት ጋር የሚያገናኝ ምንም ነገር የለም…” እያለ ኡኡታውን በሚዲያዎች ላይ አሰማ። ይህን ተከትሎ ሌላ በዚህ ስም የሚጠራ ነገር ግን ከዝርዝር መረጃው ጋር የሚመሳል ታሪክ የሌለው ሰውም ኡኡታውን ማሰማት ጀመረ። ይኸኛው አብዱልአዚ አል-ኦማሪ የሳዑዲ አረቢያ አውሮፕላን አብራሪ ስለነበረ ኤፍ.ቢ.አይ. በረራ ቁጥሩ 11 የሆነውን ቦይንግ ጀት አውሮፕላን እያበረረ ከሕንጻው ጋር ያላተመው አብዱልአዚ አል-ኦማሪ ነው ተብሎ የተለቀቀውን መረጃው አሳማኝ ያስመሰለ ሆኖ ነበረ። ነገር ግን የአጥፍቶ የመጥፋቱ ዜና ሲናኝ እሱም ዜናውን ቁጭ ብለው ከሚከታሉት የዓለም ሕዝቦች አንዱ ስለነበረ ሌላ እንቆቅልሽ ተፈጠረ።

ኦማሪ የእሱን በአጥፍቶ ጠፊነት ሥራ ላይ ተሰማርቶ ሞተ ተብሎ የተነገረውን የራሱን መርዶ እንደሰማ ጅዳ ወደሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አምርቶ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ይሰጠው ዘንድ ጠይቋል። የዚህ ሰው በሕይወት መኖር እንደታወቀ ኤፍ.ቢ.አይ. ይቅርታ እሰከ መጠየቅ ደርሶ የተጠለፈው ቦይንግ አብራሪ መሐመድ አታ መሆኑን አወጀ።

ከዚህ ኹሉ ግርግር በኋላ በኤፍ.ቢ.ኤይ. ሌላ ድራማ ሠርቷል። አንዳንድ ሚዲያዎች አጥፍቶ ጠፊው አብዱልአዚ አል-ኦማሪ የሳዑዲ አረቢያ አየር ማረፊያ የጥበቃ ሠራተኛ የነበረ ሰው ነው የሚል ዜና አስተጋብተዋል።

(3) ሳዒድ አል-ጋምዲ-. ስሙ፣ ሥራው፣ የልደቱ ቀኑ በኤፍ.ቢ.አይ ተጠቅሶ አጥፍቶ ጠፊ ተደርጎ ከተጠቀሱት ወጣቶች አንዱ ነው። በዚህ የኤፍ.ቢ.አይ. መረጃ ላይ የሰፈረው ምስል ግን የእሱ አልነበረም። በወቅቱ አል-ጋምዲ ከሌሎች 22 የሳዑዲ አረቢያ ፓይለቶች ጋር ቱኒዝያ ውስጥ ኤር ባስ-320 የማብረር ሥልጠና መውሰድ ከጀመረ 10ኛ ወሩን ይዞ ነበረ። ሲ.ኤን.ኤን. ቴሌቪዥን የአል-ጋምዲን ትክክለኛ ፎቶ ከኤፍ.ቢ.አይ. መግለጫ ጋር አያይዞ ወሬውን ነዛው። አልጋምዲ “በቁምህ እያለህ አሸባሪው አጥፍቶ ጠፋ ተብሎ ሲነገርብህ መስማት በጣም ግራ ያጋባል” ሲል ቃለ ምልልስ ላደረገለት ለአንድ ለንደን ውስጥ ለሚታተም አሽራቅ አል-አውሳት የተባለ የዓረቢኛ ጋዜጣ ተናግሯል።

(4) ካሊድ አል-ምድሐር- የእንግሊዙ መገናኛ ብዙኃን ቢቢሲ ሞተዋል ከተባሉት አጥፍቶ ጠፊዎች መካከል በሕይዎት ያሉ መኖራቸውን በዘገበበት ሪፖርት ላይ የካሊድ አል-ምድሐር ፎቶ ለጥፎ ከፎቶው ስር ‘ካሊድ አል-ምድሐርም በሕይወት ሳይኖር አይቀርም’ የሚል ጥርጣሬ ያጠላበት የሚመስል ጽሁፍ አስነብቦ ነበረ።

የ9/11 ጥቃት በደረሰ በማግስቱ የካድ አል-ምድሐር ንብረት የሆነች ቶዮታ ኮሮላ መኪና በዱላስ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመኪና ማቆሚያ ቦታ መገኘቷ ተነግሯል። በመኪናዋ ውስጥ በሞሐመድ አታ የተጻፈ ደብዳቤ፣ የዋሽንግተንና የኒውዮርክ ከተሞች ካርታ፣ የቦይንግ 757 የበረራ ክፍል ምስሎች፣ ለወንጀል ምርመራው የሚያግዙ ሌሎች ሰነዶች መገኘታቸውም አብሮ ተነገሮ ነበረ።

ከአደጋው በስምንት ቀናት ዘግይቶ ግን ካሊድ አል-ምድሐርም በሕይወት እንዳለ የሚያሳይ ደብዳቤ ከአንድ የአሜሪካ የፌደራል መድኅን ኮርፖሬሽን ይፋ ተደረገ። ውዝግቡን ለማርገብ በሚመስል አኳኋን ችግሩ የዓረቢኛ ስሞች መመሳሰልና መደጋገም ነው የሚል ማስተባበያ ተሰጠ። ኤፍ.ቢ.አይ. ይፋ ያደረጋቸውን ፎቶዎችና ስሞች በመቀየር ስህተቱን የማረም ዕርምጃ መውሰዱን አስታወቀ። ካሊድ አል-ምድሐር የሚለው ስም ካሊድ አል-ምሐመዲ በሚል ስም ተተካ፤ ቀጥሎም ምስሉን በመቀየር ውንጀላው ቀጠለ።

(5) አሚር ቡኻሪ- ሲ.ኤን.ኤን. የ9/11 አደጋ ከደረሰ በሦስተኛ ቀን (እ.አ.አ. መስከረም 13/2001) የበረራ ቁጥሩ 11 የሆነውን ቦይንግ ጠልፈው አጥፍተው የጠፉ ከተባሉት ሰዎች መካከል አሚር አባስ ቡኻሪ እና የእሱ ወንድም የሆነው አድናን ቡኻሪ እንዳሉበት የፌደራል መሥሪያ ቤቱን ጠቅሶ ዘግቦ ነበረ። ነገር ግን አሚር ቡኻሪ ከዓመት በፊት (እ.አ.አ. መስከረም 11/2000) እዚያው አሜሪካ ውስጥ እያበረራት የነበረችው ፒፐር-ቼሮኬ የተባለች ትንሽ አውሮፕላን ከሌላ ፒፐር-አዜትክ ከተባለች ትንሽ አውሮፕላች ጋር በፍሎሪዳ ፎርት-ፒርስ ሰማይ ላይ ተጋጭታ በአደጋው የሞተ ሰው ነው።

የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት አሚር አባስ ቡኻሪ የሳዑዲ አየር መንገድ አብራሪ አንደነበረ፣ በረራ እያረገ በነበረበት ወቅት በተከሰተ የአየር ላይ ግጭት እዚያው አሜሪካ ውስጥ መሞቱን ወዲያውኑ ገልጸዋል።

(6) አድናን ቡኻሪ- አድናን ቡኻሪ ደግሞ በአጥፍቶ ጠፊነት መሞቱ ሲነገር እዚው ፍሎሪዳ ውስጥ በሕይወት ነበረ። ይህ በኤፍ.ቢ.አይ. ሞተ የተባለ ሰው መኖሩ እንደታወቀ በራሱ በኤፍ.ቢ.አይ. ቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ ተደርጎበታል።
ይህ ወንድማማቾቹን የሚመለከት ሐቅ ይፋ መሆኑን ተከትሎ አድናን ቡኻሪ ከወንጀሉ ነጻ መሆኑ በኤፍ.ቢ.አይ. እንደታመነለት ሲ.ኤን.ኤን. ወዲያውኑ ጥፋቱን አምኖ ይቅርታ ጠይቋል። ሲ.ኤን.ኤን. ይቅርታውን በዚያው ዘገባውን ባቀረበበት ገጽ ላይ ከዘገባው ጋር አያይዞት ይገኛል።

(7) አሚር ሞሐመድ ካምፋር- ኤቢሲ ኒውስ የተባለው ሚዲያ ኤፍ.ቢ.አይን ጠቅሶ የ9/11ን ጥቃት ያካሄዱ ብሎ ከጠቀሳቸው ሰዎች መካል አሚር ሞሐመድ ካምፋር ይገኝበታል። የኤፍ.ቢ.አይ. መግለጫ እንደወጣ የሳዑዲ አረቢያ አየር መንገድ ባለሥልጣናት አሚር ሞሐመድ ካምፋር የተባለው የሳዑዲ የበረራ መሐንዲስ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በሕይወት እንዳለ መረጃ ሰጥተዋል።

አሚር ሞሐመድ ካምፋር እሱ በአጥፍቶ ጠፊነት እንደሞተ ሲነገር መካ ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ሆኖ ነበረ ዜናውን የሰማው። በነገሩ ግራ የተጋባው አሚር ካምፋር ይህን እንደሰማ ወደ ሳዑዲ አየር መንገድ ባለሥልጣናት ደውሎ እዚያው ሳዑዲ ውስጥ በሕይወት ያለ መሆኑን ለማሳሰብ ተገድዶ ነበረ።

ኤፍ.ቢ.አይ. ቆየት ብሎ አሚር ሞሐመድ ካምፋርም ልክ እንደ አድናን ቡኻሪ በይፋ ከወንጀሉ ነጻ ነው ብሎ አውጆለታል። ይህ ሲባል ግን ኤፍ.ቢ.አይ. በቀላሉ እጁን ሰጥቷል ማለት አይደለም። ኤፍ.ቢ.አይ. የአሚር ካምፋርን በሕይወት መኖር እንደሰማ ካምፋር ከ9/11 ከአጥቂዎች ጋር ግንኙነት እንዳለው ከመግለጽ አልፎ ኤኬ-47 ታጥቆ ብርማ ቀለም ባላት ፕለይማውዝ መኪና በመዘዋር ላይ ያለ አደገኛ ሰው መሆኑን አውጆ የቬሮ-ፍሎሪዳ ነዋሪዎችን አስጠንቅቆ ነበረ።
ግዛቸው አበበ በኢሜል አድራሻቸው

gizachewabe@gmail.com ማግኘት ይችላሉ፡፡


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here