አክብሮት እና እኩልነት!

0
973

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ክብር መስጠት እና እኩልነት በደፈናው ሲጠቀሱ ብዙ አሻሚ አይመስሉም። ብዙ ጊዜ በማኅበረሰባችን ግን ትልቅ ክፍተትና ልዩነት የሚያመጣ ነጥብ ከእነዚህ ጉዳዮች ይነሳል። ክብር እና እኩልነት ምን እና ምን ናቸው?
ለዛሬ ለመጻፍ መነሻ የሆነኝ ባሳለፍነው ሳምንት አለቃ ዩሐንስ በተባሉ ጸሐፊ በዚሁ አምድ ላይ የጻፉት ጉዳይ ነው። ይልቁንም ጸሐፊው እንደማጣቀሻ ያነሱት አንድ ነጥብ ላይ አተኮርኩኝ። ጽሑፉ ‹ሴቶች እኩል ነን ብለው ካሰቡ ወንበር እንዲለቀቅላቸው ሊጠብቁ አይገባም። ኹለት ወድዶ አይሆንምና ይምረጡ።› የሚሉ እንዳሉ ይጠቅሳል። በዚህ የሚስማሙ ሴቶችም ወንዶችም በመኖራቸው፣ ይህ ጉዳይ እንደፍላጎት ይሁንና እኩል ነን ያለች ትራንስፖርት ላይ ትጋፋ፣ ያልፈለገች ደግሞ በክብር ወንበር ይለቀቅለት የሚል ሐሳብ ተያይዞ እንደሚነሳ ጽሑፉ ያስረዳል።
እርግጥ ነው! ይህ ጉዳይ በተለያየ ጊዜ ይሰማል። እኔ የምለው… የእኩልነትና የአክብሮትን ጉዳይ ማን አንድ አደረገው? ለአንድ አዛውንት ወንበር ስንለቅ ምን ማለታችን ነው? አካል ጉዳት ላለበት ሰውስ? ነፍሰጡር ለሆነች ሴት ከወንበራችን ስንነሳላት ምን እያልን ነው? አክብሮት መስጠትን በእኩልነት ሚዛን እንዴት ልንመዝን እንችላለን? ቀድሞ ነገርስ ይገናኛል ወይ? እህቴስ አንድ ወንድ ወንበር ሲለቅልሽ አሳንሶ ያየሽ ይመስልሻል? የትራንስፖርት ግፊያ ላይ ቅድሚያ ብታገኚ የእኩልነት ጥያቄሽን የሚያሳጣሽ ሆኖ ይሰማሻል?
በበኩሌ ትክክል አይመስለኝም። ምክንያቱም እኔ ሴት ነኝ፣ ምቹ ባልመሰሉኝ ሁኔታዎች መካከል ለእህቴ ወንበር ልለቅ እችላለሁ፣ አድርጌውም አውቃለሁ። በእድሜ ጠና ላሉ አዛውንትም እንደዛው። ይህ አክብሮታችንን የምንገልጽበት መንገድ እንጂ የእኩልነት መለኪያ ሚዛን አይደለም፣ ሊሆንም አይችልም። አክብሮቴን ለመግለጽ ከወንበሬ አልነሳም የሚል ሰው መብቱ ነው፤ አይነሳ ወይም አትነሳ።
በመግቢያዬ ላይ እንዳነሳሁት በማኅበረሰባችን ክፍተትና ልዩነት የሚያመጣው አንድ ነጥብ ይህ ነው። አክብሮት ስንሰጥ መስፈርት አለን። አለባበስ፣ የኑሮ ደረጃ፣ የትምህርት ሁኔታ፣ የእውቅና ጉዳይ ወዘተ የምንጠቅሳቸው ነጥቦች አሉ። ይህ በእርግጥ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ አውድ ከሆነ ከ‹ትራንስፖርት› ጉዳይ ጋር የሚገናኝ ላይመስል ይችላል። ግን ዞሮ ዞሮ የሚያደርሰን እዛ ነው።
ጸሐፊው በጽሑፉ የጠቀሷቸው አንዳንድ የተባሉ ሰዎችም አመለካከታቸው ለአክብሮት ሚዛን ከመሰጠት የተነሳ ነው። ለአንዲት ሴት ወንበርህን የምትለቀው ሴት ስለሆነች አይደለም፣ ከሁኔታዎች አንጻር ነው። እንጂኮ ለእናቶችም፣ ለሽማግሌም ወንበር ይለቀቃል። ጉዳዮ የጾታ አይደለም። ወንድሜ! ለሰው ክብር ያለህ ከሆነ አክብሮትህን ለመግለጽ ባስቻለህና በተመቸህ መንገድ ግለጥ።
እንደው ነገሩ ስለተነሳ እንጂ በአገራችን በተለይ በአዲስ አበባ ካለው የትራንስፖርት እጥረት አንጻር መከባበርንም መተሳሰብንም ውሃ በልቷቸዋል። እንደውም የታክሲ ተራ ላይ ሰልፎች መኖራቸው ጥሩ ሆነ እንጂ፤ መንገድ ላይ መሽቶባቸው የሚገኙት አዛውንት፣ ነፍሰጡርና ሕጻናት የያዙ ሰዎች በሆኑ ነበር። በድምሩ አክብሮትን ተላብሰው ቅድሚያ ለሚሰጡ ሁሉ ምስጋናችን ይድረስ፤ ክብረት ይስጥልን። አደራ! ለሴቶች የምንሰጠውን አክብሮት እና የሴቶችን የእኩልነት ጥያቄ ግን በአንድ ሚዛን አናስቀምጥ።
መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here