በአፋር እና አማራ ክልል አጎራባች ወረዳ የአንበጣ መንጋ ተከሠተ

0
715

በአፋር ክልል 12 ወረዳዎች ላይ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በእንስሳት መኖ ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተገለጸ።
የአፋር ክልል አንበጣ መከላከል ግብረ ኃይል አስተባባሪ የሆኑት መሐመድ ሰኢድ፣ ከሐምሌ ወር ጀምሮ ከፌደራል ግብርና ሚኒስቴር ጋር የችግሩን አሳሳቢነት በመመልከት ዕርምጃ የመዉሰድ ተግባር ተጀምሮ እንደነበር ገልጸዋል። በመሀል የክትትል ሥራው በመቋረጡ የበረሀ አንበጣዉ በስፋት ሊፈለፈል ችሏል ብለዋል።
አንበጣዉን በምድር ላይ እያለ የማጥፊያ ጊዜዉ በማለፉ የአዉሮፕላል ኬሚካል እርጭት እንደሚያስፈልግ ነው አቶ መሐመድ ሰኢድ የተናገሩት።
በተመሳሳይ የአንበጣ መንጋዉ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን እንዳይገባ የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የመከላከል ስራ ከዉዲሁ እየሠራ መሆኑን የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ አሊ ሰይድ ገልጸዋል።
የአንበጣ መንጋዉ በባለፈው ዓመት መነሻዉን አፋር ክልል በማድረግ በ61 ሺሕ የሰብል ምርት አብቃይ አርሶ ደሮች ማሳ ላይ ጉዳት አድርሷል።
በአፋር ክልል እየተፈለፈለ የሚገኘዉ የአንበጣ መንጋ ስጋት የፈጠረው ከነሐሴ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሆን፣ እስካሁን አንበጣዉን አስቀድሞ ለመከላከል የተደረገው ጥረት አነስተኛ እንደሆነ ተገልጿል።
የበርሀ አንበጣ መንጋዉ በአፋር ክልል የተለያዩ ወረዳዎች የስርጭት መጠኑን በማስፋት እየተፈለፈለ ሲሆን፣ ወደ ሌሎች ክልሎች እንዳይዛመት የተቀናጀ ሥራ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here