እነአብዲ ኢሌ ክሳቸውን እንዲያደምጡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

0
667

ባለፈው ዓመት በሱማሌ ክልል የተፈጠረውን ሁከትና ረብሻ መርተዋል በማለት በቁጥጥር ሥር የዋሉት የቀድሞ የክልሉን ፕሬዝዳንት አበዲ ሙሃመድ ኡመርን (አብዲ ኢሌ) ጨምሮ በሌሎች 47 ሰዎች ላይ ክስ መመሥረቱን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውቁል። ይሁን እንጂ አቃቤ ሕግ ክሱን ባሰማበት ወቅት አብዛኞቹ ተከሳሾች ችሎት ፊት ባለመቅረባቸው ምክንያት ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሠረተባቸው ተከሳሾቹ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎቸ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ ጦር መሣሪያ እንዲያነሳ በማድረግ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ለማድረስ መንቀሳቀሳቸውን የዐቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል።

የሱማሌ ብሔር ተወላጆች እና በሱማሌ ክልል በሚኖሩ የሌሎች ብሔር ተወላጆች መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር በማሰብ በግጭቱ ውስጥ የሚሳተፉ ወጣቶችን ማደራጀታቸውንም ክሱ አክሏል።

ዐቃቤ ሕግ በመሠረተው ክስ፣ የተደራጀውን የወጣት ቡድን በገንዘብ እና በተለያዩ ቁሳቁሶች በመደገፍ፣ በጦር መሣሪያ ድጋፍ በማድረግ፣ ግጭቱ የሚመራበትንና መልዕክት የሚተላለፍበትን ‹‹ሄጎ ዋሄገን›› የተሰኘ የፌስ ቡክ ገጽ ከመክፈት ባሻገር በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ ሰዎችን ሊያነሳሱ የሚችሉ መልዕክቶች እንዲተላለፉ አድርገዋልም ብሏል።

ተከሳሾቹ ግጭት እንዲነሳ በማድረግና በግጭቱ ምክንያት የሰው ሕይወት እንዲጠፋ፣ በመንግሥት እና በእምነት ተቋማት እንዲሁም በግለሰብ ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ፣ ሴቶች እንዲደፈሩ እንዲሁም ኅብረተሰቡ እንዲፈናቀል ማድረጋቸውም በክሱ ተካቷል።

1ኛ ተከሳሽ አብዲ ሙሃመድን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች አመጽና ሁከት በመቀስቀስና በማነሳሳት በሱማሌ ብሔር ተወላጆች እና በክልሉ የሚኖሩ ሌሎች ብሔሮች መካከል አለመግባባት እና ግጭት እንዲፈጠር አድርገዋልም ሲል ዐቃቤ ሕግ ከሷል። በዚህም ተከሳሾች በፈፀሙት የጦር መሣሪያ ይዞ በማመጽ ወይም የእርስ በእርስ ጦርነት በማስነሳት በመንግሥት ላይ በሚፈጸም ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

በነበሩ ግጭቶች ከ59 ሰዎች በላይ ሕይወት እንዲጠፋና ከ266 በላይ ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንዲደርስ ማደረጋቸውን ክሱ ያትታል። የዐቃቤ ሕግን ክስ ያዳመጠው ፍርድ ቤቱም ለተከሳሾች ክሳቸውን በንባብ ለማሰማት ለጥር 29/2011 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here