ተስካሩ ሲደገስ የመጣው ‹‹ሟች››

0
592

በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ቀልብ ስበው ከነበሩት መካከል አንዱ ሞተ ተብሎ የተለቀሰለትና የተቀበረው ግለሰብ ከሳምንት በኋላ አልሞትኩም ብሎ ወደ ቤተሰቦቹ ከተፍ ያለው ግለሰብ ነው።

የአማራ ብዙኃን መገናኘ ድርጅት ያስነበበው ዘገባ ኅዳር 19/2011 በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ አስተዳደር አንድ ወጣት ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተገድሎ መገኘቱን ይገልጻል።

ፖሊስ የሟችንም ሆነ የገዳይን ማንነት ለጊዜው ባለማወቁ ወደ ቆቦ ሆስፒታል ወስዶታል።

በማግሥቱ ከሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ 02 ቀበሌ ገረገራ አካባቢ ነዋሪው ታረቀ መንግሥቴ ለፖሊስ በመሄድ ‹‹ሟች የእኔ ልጅ ነው›› አስከሬን በመረከብ ኅዳር 21 ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር በመሆን ይቀብራሉ። ኅዳር 24 ደግሞ ፖሊስ የልጃቸውን ገዳይ አጣርቶ እንዲያሳውቃቸው ያመለክታሉ።

ይሁንና የልጃቸውን ሰልስትና ሰባት ያወጡትና የቀጣዩን ጊዜ ተስካር ለመደገስ ሲዘጋጁ የነበሩት አባት ድንገት በተደወለ ስልክ ልጃቸው እንዳልሞተ ተነገራቸው። ደዋዩም ሞተ የተባለው ልጅ ሲሆን ‹ሞቷል ብላችሁ እንዳለቀሳችሁ ሰምቻለሁ› ካለ በኋላ በአካል ወደ ቤተሰቡ መምጣቱ ታውቋል።

አባት አስከሬኑን እና ፖሊስ የያዘውን ፎቶግራፍ ባዩ ጊዜ ልጄ ነው ብለው ያለቀሱለትና ከዘመድ ጋር ሆነው እንደቀበሩት ያመኑት ልጅ ‹ከሟች ጋር እንዴት እንደተመሳሰልኩ ገርሞኛል› ማለቱም እያስገረመ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here