ቅርስ የአንድን አገር ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነት፣ እሴት፣ ኃይማኖት፣ ወግና ባህል የያዘና የማንነት መገለጫ የሆነ ትልቅ ሀብት ነው። በዚህም የብዙ ቅርስ ባለቤት የሆነች አገር በቱሪዝም ሀብት ለማግኘት፣ ማንነቷን ለመረዳትና በዓለም ታዋቂነትን ለማትረፍ ይረዳታል።
ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የብዙ ቅርሶች ባለቤት መሆኗ ይታወቃል። ጥንታዊ አገር የመሆኗን ያህል አያሌ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች አሏት። ከነዚህ መካከል ዘጠኝ የሚዳሰሱ ቅርሶቿ የዓለም ቅርስ ተብለው በዓለም ቅርስ መዝገብ ማህደር ውስጥ ሰፍረው ይገኛሉ።
እነሱም የአክሱም ሐውልት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስትያናት፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የጎንደር ቤተ መንግሥት፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፣ የሐረር ጀጎል ግንብ፣ የጥያ ትክል ድንጋይ፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ እና የሸካ ደን ናቸው።
በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኒስኮ) የሠው ልጅ ወካይ የማይጨበጡ (ኢንታንጀብል) ባህላዊ ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ከማይዳሰሱ ቅርሶች ጎራ ተመድበው በዓለም ሕዝቦች ቅርስነት ከተመዘገቡት ደግሞ የመስቀል በዓል፣ የጥምቅት በዓል፣ ፊቼ ጫምባላላ እና የገዳ ሥርዓት ይገኙበታል።
አንድ ቅርስ ዩኔስኮ ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች አልፎ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ለማድረግ ረዘም ያለ ጊዜ እና ብዙ ገንዘብ እንደሚጠይቅ ይነገራል።
ሆኖም ወደ ፊትም ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ለማስመዘገብ ጥረት የምታደርግባቸው የሚዳስሱና የማይዳስሱ በርካታ ቅርሶች እንዳሏት ይነገራል። ከነዚህም እንደምሳሌ በኦሮሚያ ክልል አዋሽ መልካ የሚገኘውን የመልካቁንጥሬ መካነ ቅርስ፣ የባሌ ተራሮች እና በሰሜን ኢትዮጵያ በልጃገረዶች በድምቀት የሚከበረውን የሻደይ አሸንድየ ሶለል በዓል መጥቀስ ይቻላል።
ከዚህ ለየት በሚል መልኩ ደግሞ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ጥንታዊ የጽሑፍ ቅርሶች ያሏት በመሆኑ አዲስ ማለዳ የጽሑፍ ቅርሶች ከፍተኛ ባለሙያና የጥንታውያን ጽሑፎች ቤተ-መጻሕፍት ቡድን መሪ ከሆኑት ከመሪጌታ ብርሀኑ አበራ መረጃ በመሰብሰብ የሚከተለውን አሰናድታለች።
በዩኔስኮ በዓለም የሥነ ጽሑፍ ቅርስነት የተመዘገቡ አስራ ኹለት የጽሁፍ ቅርሶች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ (በድሮ ስሙ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ጥበባት፣ ወዜና ዓለማት ) የጽሑፍ ቅርስ ክምችት ክፍል (በቀድሞ ስሙ የግዕዝ ክፍል) ውስጥ ይገኛሉ።
የመጀመሪያው፣ አርባዕቱ ወንጌል (አራቱ ወንጌላት) ነው። ይህ ጥንታዊ ጽሑፍ ቅዱስ ማቲዎስ፣ ቅዱስ ማርቆስ፣ ቅዱስ ሉቃስና ቅዱስ ዮሐንስ የጻፉት ቅዱስ ወንጌል ሲሆን፣ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በግዕዝ ቋንቋ በብራና ላይ በቁም ጽሕፈት ተጽፎ የተዘጋጀ ጥንታዊ የብራና መጽሐፍ ነው።
ኹለተኛው፣ መጽሐፈ ሔኖክ ነብይ ነው። ይህም በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በብራና ላይ በቁም ጽሕፈት በግዕዝ ቋንቋ የተጻፈ የጽሑፍ ቅርስ ነው።
ሶስተኛው፣ በዩኔስኮ የተመዘገበው ጥንታዊ ቅርስ ደግሞ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ነው። ይህ ጽሑፍ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በግዕዝ ቋንቋ በብራና ላይ እጅግ ባማረ የአጻጻፍ ስልት የተጻፈ የጽሑፍ ቅርስ ሲሆን፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የጻፋቸውን አስራ አራቱን መልዕክታት አጠቃሎ በአንድ ላይ የያዘ ነው።
አራተኛው፣ መዝሙረ ዳዊት ይሰኛል። መዝሙረ ዳዊት በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስትያን ሊቃውንት በግዕዝ ቋንቋ የተጻፈ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመ ጥንታዊ መጽሐፍ ነው። ከመዝሙረ ዳዊት በፊት በኢትዮጵያ የታተመ ምንም አይነት መጽሐፍ አይገኝም። ያሳተሙትም ወደ ውጭ አገር በመላክ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ናቸው።
አምስተኛው፣ መጽሐፈ ፍትሐ ነገሥት ነው። መጽሐፈ ፍትሐ ነገሥት የቀደምት ኢትዮጵያውያን ነገሥታት መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲመሩብት እና ሲያስተዳድሩበት የነበረ ጥንታዊ የጽሑፍ ቅርስ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሕግ ምንጭ ሆኖ አገልግሎት ሲሰጥበት የነበረ ጥንታዊ የጽሑፍ ቅርስ ነው። ነገሥታት ፍርድ እና ብይን የሚሰጡበት፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሥርወ ሕግ ሆኖ ለብዙ ዘመናት ሲሠራበት የቆዬ ከመሆኑ ጋር አሁንም የሕግ ምንጭነቱን እንደያዘ ይገኛል። የተጻፈውም በግዕዝ ቋንቋ በብራና ላይ እጅግ ባማረ የአጻጻፍ ስልት፣ በቁም ጽሕፈት ነው።
ስድስተኛው ጥንታዊ ጽሑፍ፣ መጽሐፈ ቅዳሴ (መጻሕፍተ_ቅዳሴ) ሲሆን፣ በ17ኛው ክፍለ ዘመን በግዕዝ ቋንቋ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስትያን ሊቃውንት በብራና ላይ የተጻፈ የጽሑፍ ቅርስ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስትያን ለሥርዓተ አምልኮ መንፈሳዊ አገልግሎት የምትጠቀምባቸውና የእየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ስጋውንና ክቡር ደሙን የምታከብርባቸው፣ ከቅኖና ቤተ ክርስትያን የተወሰኑትን አስራ አራቱን መጻሕፍተ ቅዳሴያትን አጠቃሎ የያዘ የጽሑፍ ቅርስ ነው።
መጽሐፈ ታሪከ ነገሥት፣ ሰባተኛው በዩኒስኮ የተመዘገበ የኢትዮጵያ ጥንታዊ የጽሑፍ ቅርስ ነው። በጥንት የነበሩ ኢትዮጵያውያን ነገሥታትን ታሪክ በስፋትና በጥልቀት የሚያብራራ ሲሆን፣ የሠው ልጆች ዘር ኹሉ አባት ከሆነው ከአዳም ጀምሮ በዓለም የታወቁ ነገሥታትን ታሪክ ጨምሮ የያዘ ጥንታዊ የብራና የጽሑፍ ቅርስ ነው። በዚህም የኹሉንም ኢትዮጵያውያን ነገሥታት ታሪክ በማካተት በዓለም ታዋቂ የሆኑ እንደ ታላቁ እስክንድር፣ ንጉሥ ዳዊት፣ ንጉሥ ሰሎሞን እና የመሳሰሉ ታላላቅ ነገሥታትን ታሪክ ሰንዶ ይዟል።
የዳግማዊ አጼ ምኒልክን ግለ ታሪክ የያዘው ሠነድ “መጽሐፈ ታሪክ ዘዳግማዊ አጼ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ሌላኛው ስምንተኛ ሆኖ በዩኒስኮ የተመዘገበ የጽሑፍ ቅርስ ነው።
ዘጠነኛው፣ በዓለም ቅርስ መዝገብ ዝርዝር ውስጥ ተካቶ የሚገኘው ጥንታዊ የጽሑፍ ቅርስ ደግሞ መጽሐፈ ግብረ ሕማማት ነው። መጽሐፈ ግብረ ሕማማት በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በግዕዝ ቋንቋ፣ በፈረስ ቆዳ ብራና ላይ በቁም ጽሕፈት የተጻፈ ድንቅ ጥንታዊ ቅርስ ነው። ሌሎች ከላይ የተጠቀሱት በበግና በፍየል ቆዳ ብራና ላይ የተጻፉ በመሆኑ፣ መጽሐፈ ግብረ ሕማማት በፈረስ ቆዳ ብራና ላይ መከተቡ የተለየ ያደርገዋል። የዚህ ጥንታዊ ቅርስ ጸሐፊዎችም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስትያን የተመረጡ ሊቃውንት ናቸው።
በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከተመዘገቡ አስራ ኹለት የኢትዮጵያ ጥንታዊ የጽሑፍ ቅርሶች ቀሪ ሦስቱ ደግሞ የነገሥታት ደብዳቤዎች ናቸው።
ከነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ለሞስኮው ንጉሠ ነገሥት ኒኮላስ ቄሳር በአማርኛ ቋንቋ ጽፈው በ1884 የላኩት ደብዳቤ ነው። በደብዳቤው አጼ ምኒልክ ለሞስኮው ንጉሥ በወቅቱ አስቸግሯቸው የነበረውን የጣሊያንን ትንኮሳ ያስረዱበት ነው። ደብዳቤው ሲጀምር ‹‹. . . ይድረስ ከመስኮብ ንጉሠ ነገሥት ኒቆላዎስ ቄሳር ፪ኛ ሠላም ለርስዎ፡ ክቡር ንጉሠ ነገሥት ሆይ፡ …ይልና በዚህ ደብዳቤ ቀጥሎ የሚፃፈውን ግፌን አስታውቀዎታለሁ። የኢትዮጵያን ነፃነቷን፡ እራሷን የቻለች መንግስት ባጠገቧም ጎረቤት የሌላት መሆኗ አስቀድሞ በሮፓ ነገሥታት ሁሉ የታወቀ ነው። ከግራኝ ጀምሮ እስካሁን በአሕዛብ እጅ ተከባ ዘወትር በጦርነት ድካም ነው ኑሮአችን። ከሮፓ የጦር መሳሪያ አስመጥቼ ሠራዊቴን ዘወትር ከጦርነት ድካም አሳርፋለሁ ስል ከንጉሥ ዖምበርቶ አባት ጋር የፍቅርን ነገር ጀመርኩኝ። . . .›› እያለ ይቀጥላል።
ኹለተኛው ደብዳቤ የሸዋው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ለእንግሊዝ ንግሥት በአማርኛ ቋንቋ ጽፈው የላኩት ነው።
ደብዳቤውም ‹‹. . . አቺ አቺ ደህና ነሾይ፡ እኔም ደህና ነኝ፡ ያቺ ልጆች እኔም ዘንድ የመጡ የተቀመጡም አመጡልኝ መልካም መልካም ነገር፡ ያላየሁትን ነገር። እኔ አገሬም ተቀመጡ፡ መልካሙን ክፉውንም ሁሉንም አዩ። አሁንም ፈለጉ ለመሄድ፡ ከዚህ አገር እኔም መሄዳቸውን በሰማሁ ቀን ያገሬን የፈለጉትን አንዳንድ እቃ አሠርቼ ሰጠኋቸው። እኔ የሠራሁት ጥቂት ነገር ነው። ስለፍቅር፡ ስለወዳጅነት ያንቺ ልጆች መላኬ ይኸን ሥራ ያሳዩሽ ብዬ ነው። አንቺ በልብሽ አታስቢ፡ አትጠራጠሪ፡ በኛ ባገራችን ጌጣጌጣችንም ይኸ ነው። የኛ ባገራችን የምንችለው ነገር ይኸ ነው። ይኸ ነገር ለፍቅርና ለመዋደድ ነው። የኔ ልቤ ለወዳጅነት ለፍቅር ነው። . . . እያለ ሲያትት ይቆይና . . . በሀገረ አንኮበር በዘመነ ሉቃስ በወርኃ ጥር በ፬ መዓልት በ፲ ሌሊት ተኃተመ፡ እም ልደቱ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሺተ፯፻ከ፴፭ ዘመን ደብተራ ወልደ ዜና ማርቆስ ጻፈ፡ ሰአለ፡›› ብሎ ይጨርሳል።
ሦስተኛው ደብዳቤና የመጨረሻው የጽሑፍ ቅርስ ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ለእንግሊዝ ንግሥት ቪክቶሪያ በአማርኛ ቋንቋ ጽፈው የላኩት ነው። ይህ ደብዳቤ በንጉሠ ነገስቱ ዘመን የነበረውን ኋላቀርነትና እሳቸው አገራቸውን ለማሰልጠን የነበራቸውን ጽኑ ፍላጎት ያሳያል። እንዲህም የሚል ነው፤ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ፡ ይድረስ ከታላቂቱ ከዕንገሊዝ ንግሥት ወዳጅ፡ ከሎሌዎ ልኬብዎአለሁ። ስምዎን እከሌ ብዬ እንዳልጥፍ ባላሠብሁት ጉዳይ ድንገት ተገናኘነ። ትላትና ለናቶ ፍላጥ የሰደድሁት ደብዳቤ ከናንተ ከወዳጆቼ ጋራ በመጣላቴ ሁለተኛ የወጊያአችሁን፡ ያገራችሁን ሥራት በማየቴ ያገሬ ሰው ከትዕዛዝ መውጣቱን አይቼ፡ ብገለው፡ ብቀጣው፡ አልመለስልኝ ቢል፡ ቢነደኝ፡ ብቀና፡ በገዛ ጠበንጃዬ እሞታለሁ ብዬ ሰይጣን አሣብ አሳደረበኝ። አይ ይህን ሁሉ ሠራዊት ዋቢ አልቦ ትቼው አልሂድ እግዚአብሔር ይጣላኛል ብዬ፡ አጣድፌ ከርስዎ ሰደድሁት። እኔ ስሞት ሲድበለበል ቃሌ ሳይደርስዎ ይቀራል ብዬ። ከሰደድሁልዎ በኋላ ግን ጠበንጃየን ቃታ ከፍቼ ካፌ አጉርሼ ብስበው ብስበው እምቢ አለኝ። ሰዎች ሩጠው መጥተው ካፌ ሲመዙት ተተኮሰ። እግዚአብሔር አትሙት ካለኝ ግን ብተርፍ ልብዎ ይሻቅላል ብዬ አቶ ርሳምን ሰድጀው አደርሁ። ዛሬ ትንሳኤ ነውና ፍሪዳ እንድሰድልዎ ይፍቀዱልኝ። ደብዳቤዎንም መልሸ የሰደድሁት በሰማይ እንጂ በምድር እንገናኛለን አላልሁም ነበር።
ፊታውራሪ ገብርዬን የኔን ወዳጅ፡ ሣላስነሣው ያደርሁ ከሞትሁኝ ሁሉንም አብረው ይቅበሩን። ብዬ ነበር ቁሜ ከዋልሁ ግን ልቅበረው ይፍቀዱልኝ።
ፈረንጆች ሁሉ ይምጡ ያሉኝንም እንኳን ሌላው፡ እነአቶ ወልድ ማየርም ወዳጆች ከወደዱ፡ እሺ ይምጡ። ዳሩ ግን እኔ ወዳጅዎ ሥራ ወዳጅ ነኝና እንዲያው እንዳልቀርብዎ ያርጉ።››
አስራ ኹለቱም የጽሑፍ ቅርሶች በዩኔስኮ የተመዘገቡት በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1989 በተመሳሳይ ጊዜ ነው።
በመጨረሻም፣ ኢትዮጵያ እነዚህን ጥንታዊ የጽሑፍ ቅርሶች በዩኒስኮ በማስመዝገቧ በቱሪዝም መስክ ትልቅ የገቢ ምንጨ ታገኛለች ያሉት መሪጌታ ብርሀኑ፣ ለታሪክ ተመራማሪዎች እና ለዓለም አጥኝዎች ከሚሰጡት ጠቀሜታ ይበልጥ የማንነት መገለጫዎቻችን በመሆናቸው ወደፊትም ሌሎች ኹለት የጽሑፍ ቅርሶች ተመርጠው በዓለም የጽሑፍ ቅርስነት እንዲመዘገቡ ማመልከቻ ወደ ዩኔስኮ ተልኳል ብለዋል። እነዚህም መጽሐፈ ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ እና የኢትዮጵን የዘመን አቆጣጠር ትንታኔ በስፋትና በጥልቀት የሚገልጸውና በብራና የተጻፈው መጽሐፈ ባህረ ሐሳብ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
በጥቅሉ ቅርሶች በዩኔስኮ መመዝገባቸው ትልቅ ዋጋ ያለው ቢሆንም፣ በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚደከመውን ያህል ለእንክባካቤና ለጥገና የሚደረገው ጥረት እምብዛም ባለመሆኑ ይህ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው። በቸልተኝነት ሊዘረፉ፣ ሊወድሙ እና ሊበላሹ አይገባም።
ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014