አዲስ የሚመሠረተው መንግስት ለፀረ-ሙስና ትግሉ ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ሲሉ የሀረሪ ክልል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ካሊድ ኑሬ አሳሰቡ፡፡
ሀገር በሙስና እየተጎዳች ለውጥ ማምጣት ይከብዳል ያሉት ኮሚሽነሩ ሙስናን ለመታገልም የመንግስት ቁርጠኝነት ከምንም በላይ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አዲስ የሚመሠረተው መንግስት ለትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል እንዲሁም ሙሰኞች በህግ እንዲጠየቁ ከማድረግ አኳያ በከፍተኛ ቁርጠኝነት ካልሠራ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት አይቻልም ሲሉም ኮሚሽነር ካሊድ አሳስበዋል፡፡
በ2013 በጀት ዓመት የፌደራሉና የክልል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች ሥራዎችን በቅንጅት መስራት መጀመራቸው ውጤት እያስገኘ መሆኑንም ኮሚሽነር ካሊድ ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽነሩ አያይዘውም ክልሎች ከፈደራሉ የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር የጀመሩትን ቅንጅታዊ አሰራሮች ይበልጥ አጠናክረው ማስቀጠል እንደሚገባቸው ገልፀዋል።
የተጀመሩ የአቅም ግንባታ፣ የልምድና ተሞክሮ ልውውጦች፣ በየጊዜው የሚደረጉ ክትትልና ድጋፎች እንዲሁም የአፈጻጸም ምዘናዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም መጠቆማቸውን ከሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ፡፡
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



