የጉሙዝ ታጣቂዎች በሴዳል ወረዳ 145 ሰዎች ማገታቸውንና 5 ሺህ ያህል ሰዎችም አደጋውን ሸሽተው መፈናቀላቸውን ኢሰመኮ ገለጸ

0
646

የጉሙዝ ታጣቂዎች በሴዳል ወረዳ 145 ሰዎች ማገታቸውንና 5 ሺህ ሰዎችም አደጋውን ሸሽተው መፈናቀላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በመተከልና ካማሺ ዞኖች የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ሊፋጠኑ ይገባል ሲልም ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ ላይ አሳስቧል።

ኢሰመኮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል እና ካማሺ ዞኖች ያለውን የፀጥታ ሁኔታና የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ በፌዴራል መንግስቱና በአካባቢው ኮማንድ ፖስት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በተሻለ ፍጥነት ሊተገበሩና ሊጠናከሩ እንደሚገባም አሳስቧል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት ከሴዳል ወረዳ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሸሽተው የሚገኙ ነዋሪዎች እንደሚገልጹት፣ ከጥር ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በወረዳው በሚደርሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ምክንያት በርካታ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውንና፣ ከመጋቢት ወር 2013 ጀምሮ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ዝግ ሆነው መቆየታቸውን የኢሰመኮ መግለጫ አስታውቋል።

ከመስከረም 14 ቀን 2014 ጀምሮ ደግሞ የአካባቢው ነዋሪዎች “የጉሙዝ ታጣቂዎች” ብለው የሚጠሯቸው ኃይሎች በወረዳው የሚኖሩ ሕጻናትን፣ ሴቶችንና አረጋውያንን ጨምሮ ወደ 145 የሚገመቱ የጉሙዝ ብሔር ተወላጅ የሆኑ አባወራዎችን (ቤተሰቦችን) ማገታቸውን ከዚሁ ሁኔታ የሸሹ ነዋሪዎች ለኮሚሽኑ አሳውቀዋል።

ታጣቂዎቹ “ዓላማችንን አልደገፋችሁም” በሚል ምክንያት አፍሰው እንደወሰዷቸውና በተለምዶ “መርሻው” እና “ኤክፈት” ተብሎ በሚጠራ አካባቢ እንዳገቷቸው አክለው አስረድተዋል።

ከታጋቾቹ መካከል “ቢያንስ ሁለት ሰዎች በታጣቂዎቹ መገደላቸውንና” ቀሪው “በአስከፊ ስቃይ ውስጥ የተያዙ” መሆናቸውንም ከነዋሪዎቹ ማረጋገጡን ኢሰመኮ ገልጿል።

በመስከረም 14 ቀን 2014 በደረሰው ጥቃት ምክንያት 5 ሺህ የሚሆኑ ተጨማሪ የሴዳል ወረዳ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ለጊዜው በወረዳው መስተዳደር ግቢ ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙም አንስቷል።

ኢሰመኮ አደረኩት ባለው ክትትል፣ ከመስከረም 16 ቀን 2014 ጀምሮ በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ኃይሎቹ መካከል “ውጊያ” በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጿል።

ከመስከረም 19 ቀን 2014 ጀምሮም ነዋሪዎችን ወደ ዳሊቲ ከተማ ለማሸሽ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣ ነገርግን የሴዳል ወረዳ አመራሮችም ሆነ ከወረዳው የሸሹ ነዋሪዎች በአካባቢው የተሰማራው የፀጥታ ኃይል በቂ አለመሆኑን አስረድተዋል ብሏል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በካማሺ እና በመተከል ዞኖች በተደጋጋሚ የሲቪል ሰዎችን ሕይወት፣ አካል እና ንብረት አደጋ ላይ የጣሉ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ቢቆዩም፣ በፌዴራል እና ክልል መንግሥታት የተወሰዱት እርምጃዎች አደጋውን ለመቀልበስ እና የሲቪል ሰዎችን ሕይወት ከሞት ለመታደግ በቂ አለመሆናቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።

ስለሆነም መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ሁለንተናዊ መፍትሔ የማፈላለጉ ሂደት አሁንም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲል አሳስቧል።
__________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here