የወጥ ቤት ችሎታ!

Views: 236

እንዲህ ሆነ፤ እድሜያቸው ሰማንያውን እየጨረሰ እንደሆነ አኳኋናቸው የሚያሳብቅ፤ ቁመታቸው አጠር ያለ፤ እንደው እንዲህ ነው ብለው የማይገልጹት ግን አለ ቢባል ሁሉም ሊስማማበት የሚችል ደርባባነት የሚታይባቸው እናት ናቸው። በለጋ እድሜ የትዳር አጋራቸው በሞት ከተለይዋቸው በኋላ ብዙውን የሕይወት ፈተና ለብቻቸው ተጋፍጠው ልጆቻቸውን ከቁምነገር አድርሰዋል። አጋጣሚ ቤታቸው የተገኘነው ካሳደጓቸው የልጅ ልጆቻቸው መካከል አንዷን ድረው፤ በሰርጉ ማግስት ነው።

ሰርጉ እንዴት አለፈ? ምግቡ እንዴት ነበር? ወዘተ የሚሉ ጨዋታዎች ተነስተው ቤቱ በደመቀበት ሰዓት ‹‹እንጀራ መጋገር’ኮ አልችልም›› አሉ፤ እኚህ ብዙ ልጆችን ያሳደጉ ሴት። ነገሩን በጨዋታ መካከል ቀለል አድርገው አነሱት እንጂ አግዝፎ የሰማቸው ምን ሊያስብ እንደሚችል አልጠረጠሩም።

አልቀረላቸውም! በማግስቱ ‹‹አይገርሙም! በዚህ እድሜያቸው እንጀራ መጋገር አይችሉም!›› ተብሎ ሥማቸው በሰፈር ተነሳ። የአካባቢው ሴቶች ለተወሰነ ቀን እንጀራ ስለመጋገር ሲነሳ እርሳቸውን አነሱ፣ ባሎችም ምሳሌ አድርገው እየጠቀሱ ተሳሳቁ። እርሳቸው ግን መታማታቸውን የሰሙ አይመስለኝም። በበኩሌም ነገሩን ስሰማ አዲስ ነገር አልሆነብኝም። እርግጥ ነው የቤት ውስጥ ሙያን ሆነ መሠረታዊ የሚባሉ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያስፈልጉ ክህሎቶችን ማሟላት ይመረጣል። የእኚህ ሴት እንጀራ መጋገር አለመቻል መነጋገሪያ የሆነው ግን ካለመቻላቸው ሳይሆን ሴት ከመሆናቸው ነው። ‹‹ሴት አይደሉ እንዴ!›› ያለው ይበዛል።

ከአቅም በላይ ካልሆነ በቀር ምንም ነገርን አልችልም ማለት ከስንፍና ሊቆጠር ይችላል። ይልቁንም ለመቻል አጋጣሚው እያለ፣ ያንን ሙያ መቻል በአንዳች ሁኔታ መፍትሔ ሊሰጥ የሚችል ከሆነ፣ አለመቻልን ሆነ ብለው ከመረጡት ወዘተ አለመቻል፣ አለማወቅ ሊስወቅስ ይችላል። እንዳልኩት ነው፤ ማንኛውንም ነገር ማወቅ ተገቢ ነው። የጾታ ጉዳይ ግን አይደለም።

ዶሮ መገንጠል ትችያለሽ? ሙያ ስለሆነ ብታውቂበት ደስ ይላል። ሴት ስለሆንሽ ግዴታሽ ነው ማለት ግን አይደለም።
የሥራ ባልደረባዬ ጋር በዚህ ጉዳይ ስንነጋገር፤ ‹‹ብዙ የማናውቀውና የማንችለው ነገር አለ። ለምን ዶሮ ወጥ መሥራት አልችልም ወይም እንጀራ መጋገር አልችልም ማለት እንደሚያስወቅስ ይገርመኛል›› አለችኝ።
እውነት ነው! ምግብ ማብሰል አሁን ላይ ክህሎት ሆኗል። በእርግጥ በቀን ሦስት ጊዜ መብላት ርዕሰ ጉዳይ በሆነባት አገራችን ላይ በጣት ለሚቆጠሩ በየዓመት ለሚመጡ በዓላት ተናፍቆ የሚሠራን የዶሮ ወጥ መሥራት መቻል አለመቻል ሊያነጋግርም ሙያ ሆኖ እልል ሊባልለትም አይገባም ባይ ነኝ። አነጋጋሪ ከሆነም ግን፤ ዶሮ ወጥ መሥራት ወይም እንጀራ መጋገር አለመቻል ለሴት ልጅ ተለይቶ የሚያሳፍር አይደለም።

ይሄ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር፤ ‹‹ይህ የመከራከሪያ ሐሳብ ሙያ የሌላቸው ሴቶች አባባል ነው›› የሚሉ አይጠፉም። ሁሉን የሴቶች ጉዳይ በወንዶች እያነጻጸሩና በወንድሞች ሚዛን እያስቀመጡ መለካት እንደሚሰለች ቢገባኝም፤ አሁን ላይ ባለሙያ የሆኑ ወንድሞች አሉን። ለወንዶች ወጥ ቤት ገብቶ ጉድ ጉድ ማለት፣ እንጀራ መጋገርና ምግብ ማዘጋጀት ከማያሳፍርበትና ሙያ ከሆነበት ጊዜ ከደረስን፣ እንግዲህ ቀስ በቀስ ይህ የእኛ ማኅበረሰብ ‹‹እንጀራ መጋገር አልችልም›› የምትል ሴትን ያለመደነቅ ያስተናግዳል ብለን እናስባለን።

እንዳልኩት ነው፤ አለመቻል በምንም መስፈርትና በየትኛውም ሁኔታ ‹‹ይበል!›› የሚባል አይደለም። አጋጣሚው ካለ ሁሉን መቻል ጥሩ ነው፤ ወደ ሆድ ለሚገባው ብቻ ሳይሆን ለኑሮ የሚያስፈልጉ ክህሎቶች ጭምር ማለት ነው። ወጥ መሥራት፣ እንጀራ መጋር፣ ዶሮ መገንጠል፣ ቡና ማፍላት ወዘተ ከማትችል ሴት ይልቅ፣ በሕይወት የትኛውም ሰልፍ ‹‹አልችልም!›› ይሉት ነገር የሚያሸንፋት ሴት እንዳትኖር ነው መስጋት።
ሊድያ ተስፋዬ

የወጥ ቤት ችሎታ!

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com