ብልፅግና እና ኢሕአዴግ አንድ ናቸው በዘፈን ምርጫቸው?

Views: 466

ኢሕአዴግ በውህደት ወደ ብልፅግና ፓርቲ ተቀይሯል። በዚህ አዲስ ፓርቲም አዳዲስ የተባሉ አሠራሮችና አካሔዶች የተነሱ ሲሆን፣ በአብዛኛው ‹አገር በቀል› የሚለው ሐረግም በብዛት ይሰማ ጀምሯል። ይህን የሚያነሱት ሙሉጌታ አያሌው፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሆነ ልማታዊ መንግሥት ወይም አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎቹ እንዲሁም መደመር፤ ሊመዘኑ የሚገባው ከውጤታማነት፥ አዋጭነት ወይም ፍትሃዊነት አንፃር እንጂ ከአገር በቀልነታቸው አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ። ካልሆነ ግን የቀድሞው ኢሕአዴግና የአሁኑ ብልፅግና ፓርቲ ‹አገር በቀል› በሚል ሥም መጓዛቸው አንድ ያደርጋቸዋል ሲሉ ያብራራሉ።

‹‹ሳም ሳም አርጊኝ
ሳም ሳም አርጊኝ
ያገርሽ ልጅ ነኝ፤››
ኢሕአዴግና ብልፅግና የሚያዜሙልን የፍቅር ዘፈን አንድ አይነት ነው እንዴ?
ኢሕአዴግ
ከአስራ ኹለት ዓመታት ግድም ጀምሮ ኢሕአዴግ ራሱን ልማታዊ መንግሥት አድርጎ ሰይሟል። በእርግጥ ትክክለኛው አባባል “ልማታዊ መንግሥትን ለመገንባት ወስኗል” ነው። ግና በቅፅበታዊና ምትሃታዊ ሁኔታ ውሳኔውን እውን ከሚያደርገው የፈጣሪ ውሳኔ ጋር እያምታታው ይመስለኛል፤ በተለያዩ መግለጫዎች ራሱን የሚገልፀው፤ ልማታዊ ለመሆን እንደሚሠራ መንግሥት ሳይሆን፤ ልማታዊ እንደሆነ መንግሥት ነው።

ልማታዊ መንግሥት ምንድን ነው? ኢሕአዴግ፤ ለአባላቱና ለሕዝቡ ልማታዊ መንግሥት ምን አይነት መንግሥት እንደሆነ፤ በሚገባ አላስረዳም። በሞከረው ልክ ያደረገው ነገር ቢኖር፤ ራሱን ከኒዮሊብራል መንግሥታት መለየት ነው። በኢሕአዴግ ትርክት ኒዮሊብራል የሚባሉት አክራሪ ገበያተኞች ወይም የገበያ አፍቃሪዎች ናቸው። እንደ ማንኛውም አፍቃሪ፤ በፍቅር የከነፉበት ገበያ፤ ጉድለት እንደሌለው ያምናሉ በሚል ኢሕአዴግ ቢከሳቸውም፤ ክሱ ግን ሙሉ ለሙሉ እውነት አይደለም።

ኒዮሊብራሊዝምን ከውጭ ኃይሎች ጋር ያያይዘዋል፤ ኢሕአዴግ። ሐሳባቸውን በጉልበትና በተለያዩ ስልቶች ሌሎች ላይ እንደሚጭኑ ኢሕአዴግ ይከሳል። የአገርንና የሕዝብን ጥቅም ወደ ጎን በማድረግ የዓለም ዐቀፍ ቱጃሮችን ጥቅም ለማስከበር ይተጋል፤ ኒዮሊብራል መንግሥት።

ኒዮሊብራሊዝምን በመቃወምና በማፈንገጥ፤ ራሱን ልማታዊ ነኝ ማለቱ ኢሕአዴግን የአገር ልጅ ያደርገዋል። ኒዮሊብራሊዝምን የሚደግፉ ኢትዮጵያውያን ካሉ ባንዳዎች ናቸው። በአጭሩ ራሱን ልማታዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው መንግሥት፤ ኢትዮጵያውያንን ለመሳም ሲያቀርብ የከረመው ምክንያት፤ የአገራቹ ልጅ ነኝ የሚል ነበር።
አብዛኛው የአገራችን ሕዝብ አርሶና አርብቶ አደር ነው። ኢሕአዴግ ራሱን የአርሶና የአርብቶ አደር የፓለቲካ ድርጅት አድርጎ ይቆጥራል። እውነት እንደዛ ነው? አይደለም። በእርግጥ ድርጅቱ ከፍተኛ የአርሶና የአርብቶ አደሩ ሕዝብ ውለታ፥ እዳ አለበት። “ሳም ሳም አርጊኝ የአገርሽ ልጅ ነኝ” የሚለው ሁሉ እኮ የአገሯ ልጅ አይደለም። ግን መስሎ ለመታዬት ይሞክራል። ኢሕአዴግም የአርሶና አርብቶ አደሩ ድርጅት እንደሆነ ለማስመሰል ሲሞክር ነበር።
የቀደመው ኢሕአዴግ መሪዎች የአዲሱን ኢሕአዴግ መሪዎች ይከሷቸዋል። የውጭ ኃይል ተላላኪዎች እንደሆኑና አገሪቱን ለውጭ እየሸጧት እንደሆነ። ይሄም ቢሆን የዘፈኑ አንድ አካል ነው።

ብልፅግና
ኢሕአዴግ የሥም ለውጥ አድርጓል። ራሱን ብልፅግና እያለ መጥራት ጀምሯል። ሌሎቹም እንዲሁ እንዲጠሩት ይሻል። ጥያቄው፤ ሥሙን የቀየረው ኢሕአዴግ ዘፈኑን ቀይሯል ወይ? ነው።
ሙሉ ለሙሉ አልቀየረም ማለት አልደፍርም፤ የተቀየሩ አሉ። ወደፊት በሌሎች ጽሑፎች ለመነካካት እሞክራለሁ። አሁን ግን ያልተቀየሩት ላይ እናተኩር። ዘፈኑ እንዳልተቀየረ እንደውም ተጠናክሮ እንደቀጠለ የሚያሳዩ ኹለት ነገሮችን ልጥቀስ።

አንደኛው የመደመር ፍልስፍናን ይመለከታል። የፍልስፍናውን ይዘት ሳይሆን፤ ፍልስፍናውን ለመሸጥ፤ አዲሱ ኢሕአዴግ የሞከረበት መንገድ ነው። የአሻሻጥ ስልቱ አንድ አካል የሆነው፤ የድሮው ኢሕአዴግ ለአገር በቀል ሐሳቦች፤ ያለውን ንቀት ወይም ቸልተኝነት ማሳየት ነው።

የድሮው ኢሕአዴግ ራሱን የአርሶና አርብቶ አደሮች ፓርቲ አድርጎ መቁጠሩ፤ ኢትዮጵያዊ ያልሆነውን የማርክሲዝም ሐሳብ አራምጀነቱን እንደሚያሳይ፤ ከዚህ በተጨማሪ ለአገራችን የማይሆኑ የፓሊሲ ሐሳቦችን ከውጭ ያመጣና ይጭን እንደነበር አዲሶቹ ይናገራሉ። በአንፃሩ የመደመር ፍልስፍናው፤ ፈፅሞ ኢትዮጵያዊ፤ ምንጩና አስተዳደጉም እንደ ቡናችን ሁሉ ጅማ ላይ እንደሚጀምር ይናገራሉ።
መደመርን ሳም ሳም አድርጉት፤ የአገራችሁ ልጅ ነው፤ ነው ነገሩ።

ኹለተኛው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ይመለከታል። እንደውም ሙሉ መጠሪያ ሥሙ “አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች” የሚል ነው። የዚሁ የአገራችሁ ልጅ ነኝ ዘፈን አካል ነው። ልክ እንደ መደመር የኢኮኖሚ ፓሊሲዎቻችን አገር በቀል ናቸው።

ሦስት ጥያቄዎች። አንደኛ፤ የመደመር ፍልስፍና እና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ምን ያህል አገር በቀል ናቸው? ኹለተኛ፤ አገር በቀልነታቸው ፋይዳው ምንድን ነው? ሦስተኛ፤ የአገርሽ ልጅ ነኝ ሳሚኝን፤ አገር በቀል ነኝን፤ ምን አመጣው?
አገር በቀልነት የሚለካበት ብዙ መንገድ አለ። አንደኛው የአምራቹ ማንነት ነው። አምራቹ የት አገር እንደሚገኝ፣ ባለቤቶቹ እነማን እንደሆኑ፣ ዋና መሥሪያ ቤቱ የት አገር እንደሚገኝ መመርመር ይጠይቃል።

ኹለተኛው ለሸቀጡ ምርት ጥቅም ላይ የዋሉት ግብአቶች ውስጥ ምን ያህል ከአገር ውስጥ የተገኙ ናቸው? ምን ያህሉስ የውጭ የመጡ ናቸው? ለምሳሌ፤ አጎዋ ተብሎ በሚጠራው ፕሮግራም፣ የአሜሪካ መንግሥት ከአፍሪካ አገራት ለሚመጡ የቴክስታይል ምርቶች ልዩ እድል ይሰጣል። አንድ ቻይናዊ ድርጅት ሸሚዞችን ቻይና አገር አምርቶ ሲያበቃ ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት፤ በኢትዮጵያ የተመረተ በሚል ፌስታል እያሸገ፤ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የሰጠችውን ልዩ እድል ተጠቅሞ ወደ አሜሪካ አገር መላክ ይችላል?

ይህ የሚወሰነው ለሌላ ጥያቄ በምንሰጠው መልስ ነው። ይሄውም፤ ይህ ሸሚዝ ምን ያህል ኢትዮጵያ በቀል ነው? አብዛኛው የምርት ሂደት ቻይና ተጠናቆ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከናውነው ሥራ ሸሚዞቹን ፌስታል ውስጥ ማሸግ ከሆነ ምርቱ የኢትዮጵያ ምርት ሊባል እንደማይቻል የሚወሰን ይመስለኛል።

ከዚህ በላይ ካሉት አንፃር፤ መደመርና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎቹ ምን ያህል ሀገር በቀል ናቸው? ስንል፤ እንግዲህ በዋናነት የምንወስደው ጉዳይ የግብአቶቹን ምንጭ ሳይሆን የአምራቹን ማንነት ከሆነ፤ በእርግጥም መደመርና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎቹ አገር በቀል ናቸው። ግን ደግሞ በዚህ መለኪያም አብዮታዊ ዴሞክራሲና ልማታዊ መንግሥት አገር በቀል ናቸው።

ነገሮች የሚወሳሰቡት የግብአቶችን ምንጭ የምንወስድ ከሆነ ነው። ፓሊሲዎችና ፍልስፍናዎች ሐሳቦች ናቸው። የተገነቡትም በብዙ ሐሳቦች ነው። ግብአቶቻቸው ሐሳቦች ናቸው። የሐሳቦቹ ምንጭ የት ነው? የሐሳቦቹ ባለቤት ማን ነው? ሐሳቦች ከየት ይመጣሉ? እነዚህን ጥያቄዎች አስመልክቶ፤ በተለያየ ጊዜ ሐሳቦች አካፍዬ ነበር።
ሐሳቦች በቦታና በጊዜ አይወሰኑም። በሁሉም ቦታና ጊዜ አሉ። በሁሉም ቦታና ጊዜ ግን ለሁሉም ተደራሽ ላይሆኑ ይችላሉ። አንዳንድ ከዘመናቸው የቀደሙ ሰዎች አንዳንድ ሐሳቦችን ቀድመው ይረዷቸዋል። ከተረዷቸው በኋላ ደግሞ በልብወለድ፥ በሌሎች ጥበቦች፥ ወይም በፓለቲካ ፕሮግራም አማካኝነት ለሌሎች ተደራሽ እንዲሆኑ ያደርጋሉ። ልብወለዱ ወይም ጥበቡ ወይም ጽሑፉ የእነዚህ ዘመናቸውን የቀደሙ ሰዎች ሊባል ይችላል። ሐሳቡ ግን የእነርሱ አይደለም። ሐሳብ ባለቤት የለውም ወይም በሌላ አነጋገር ያመነበት በሙሉ ባለቤቱ ነው።

አገር በቀልነትን ከዚህ አንፃር ስንመለከተው፤ መደመር፥ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎቹ፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲና፥ ልማታዊ መንግሥት፤ ኢትዮጵያዊ ናቸው ሊባሉ የሚችሉበት መስፈርት የለም። እንደውም እኮ ብዙዎቹን ሐሳቦች ሌሎች አገሮች በታተሙ ጽሑፎች ላይ ልናገኛቸው እንችላለን። ይህ መሆኑም ኢትዮጵያዊ ላለመሆናቸው ማስረጃ አይደለም። በአጭሩ ሐሳቦች ዜግነት የላቸውም።

መደመር፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ልማታዊ መንግሥት፣ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎቹ፤ አገር በቀል መሆናቸው ወይም አለመሆናቸው ለሕዝብ አስተዳደር ምን ፋይዳ አለው?
የሕዝብ አስተዳደር ሥራዎችና ውሳኔዎች መለካት ያለባቸው ከሦስት መመዘኛዎች አንፃር ነው። አንደኛ ውጤታማነታቸው። ኹለተኛ አዋጭነታቸው። ሦስተኛ ፍትሃዊነታቸው። በመሆኑም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ልማታዊ መንግሥት ወይም አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎቹ ወይም መደመር፤ መመዘን ያለባቸው ከውጤታማነት፥ አዋጭነት ወይም ፍትሃዊነት አንፃር እንጂ ከአገር በቀልነታቸው አይደለም።
የአገርሽ ልጅ ነኝ ሳሚኝን፤ አገር በቀል ነኝን፤ ምን አመጣው? በተለይ ደግሞ በብልፅግና ዘመን።

ኹለት ምክንያቶች ይመስሉኛል። አንደኛው የድሮው ኢሕአዴግ መሪዎች አዲሶቹ ላይ የሚያቀርቡት ክስ ነው። እርሱም የውጭ ተላላኪዎች ናቸው ይላል። ኹለተኛው የሐሳቦቹ አዋጭነት፥ ውጤታማነትና፥ ፍትሃዊነት በቀላሉ የማይረጋገጡ መሆናቸው ነው፤ ጊዜ ይወስዳሉ። መሞከር አለባቸው። ቅድመ ትግበራ መዋቅራዊ ግምገማ ማድረግ ይቻላል፤ ያም ቢሆን ጊዜ ይወስዳል። ሸማቹ ግን ጊዜ የለውም። የምርጫ ወቅት ነው። ለነገሩ፤ ጊዜ ቢኖርም እንኳ፤ በብዙ የምርጫ ዴሞክራሲዎች ምርጫዎች የሚወሰኑት በዝርዝር ግምገማ ሳይሆን፤ በብጣቂና ቀላል መረጃዎች ነው። ስለዚህ አገር በቀል የሚለው መግለጫ የዚሁ አካል ነው።

አመጣጣቸውን መረዳት ማለት ግን ተገቢነታቸውን እና ውጤታማነታቸውን ማረጋገጥ አይደለም።

ሙሉጌታ አያሌው
mm.ayalew@gmail.com

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com