ከሞት ያላዳነ የንጹኃን ዜጎች የድረሱልን ጩኸት

0
1156

ሰይድ አደም ይባላል። ተወልዶ ያደገው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን አንገር ጉትን መንደር አራት ቀበሌ ነው። ሰይድ በንግድ ሥራ የሚንቀሳቀስ ታታሪ ወጣት ሲሆን፡ በኦሮሚያ ክልል ይወለድ እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ክልሎች በተደጋጋሚ ሲዘዋወር እንደኖረ ያወሳል።

ከዓመታት ወዲህ ግን ነገሮች መልካቸውን በመቀየራቸው እንኳን ከክልል ወደ ክልል፣ ከቀበሌ ወደ ቀበሌ መንቀሳቀስ አልተቻለም ይላል። ሰይድ አደም በተለይም ከ2012 ወዲህ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከሥራ ውሎ ለመግባት እንኳን ብዙ ፍርሃትና መሸማቅቅ ውስጥ እንዳለ ይናገራል።

በየዕለቱ ከተለያዩ ሰዎች የሚሠማው የወሬ ጭምጭምታ ባለፉት ዘመናት የነበሩ ሹማምንቶች ሲያከናውኗቸው የነበሩትን ድርጊቶች መለስ ብለው በማየት አሁን ባለው ትውልድ ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የጥላቻ መንፈስ የያዙ እንደሆኑ አረጋግጧል።
ሰይድ የኹሉንም አዝማሚያ አርምሞ በተሞላበት ንቃተ-ሕሊና መከታተሉን ያስረዳል። ሰዎች እየተከፋፈሉና ውስጣቸው እየተራራቀ ሳይመጣ እንዳልቀረ ይመሰክራል። አንዱ ብሔር ሌላኛውን ብሔር በዘረኝነት የማየት የጨለምተኝነት አስተሳሰብ፣ ቅኝ ግዛት ሥር ወስጥ እንደገባ ለሰይድ ፍንትው ብሎ እየታየው ከመጣ ሰንበትበት እንዳለ ያወሳል።

በሚኖርበት አካባቢ ያሉት የኦሮሞ፣ አማራና የትግራይ ተወላጆች ሲመለከታቸው ውስጣቸው እየተራራቀ መምጣቱን ይናገራል። ሰዎች ቀስ በቀስ የውስጥ ለውስጥ አለመጣጣማቸውን ወደ ተግባተር እየቀየሩት እንደመጡ ለመመልከት ጊዜ አይወስድም ይላል። ሰይድ አደም ንጹኃን ጭካኔ በተሞላበት ድርጊት ሲገደሉ እንደተመለከተ ይናገራል። ከመጋቢት ወር 2012 ጀምሮ አንዱ በአንዱ ላይ ማንነቱን መሠረት አድርጎ መነሳሳቱንና ጥቃት መፈጸሙን እንደተያያዘውም ያረጋግጣል።

ይህን ችግር የሚያወግዘው ከፊሉ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከከተማ ከንቲባ ወደ ዞኑ አስተዳደር፣ ከዞኑ አስተዳደር ወደ ክልሉ አስተዳደር የሚደርስበትን ጥቃት ለማሳሰብ ቢፍጨረጨርም ችግሩ ለትንሽ ጊዜ ተረጋግቶ ይቆይና ባልጠበቁት መልኩ ተመልሶ ከመከሰት በዘለለ ዘላቂ መፍትሔ ሊገኝለት እንዳልቻለ በየዕለቱ የሚፈጠረው የንጹኃን ግድያ ምስክር እየሆነ እንደመጣ ሰይድ ይገልጻል።

ሰይድ እንደሚናገረው ከሆነ፣ ተከባብረው ብዙ አመትን በገፉት የአካባቢው ሰዎች ዘንድ የነበረው ፍቅርና አንድነት ወደ ጥላቻና መገዳደል ተቀይሮ አለመግባባቶች ሥር ሰደው በሒደት ከቀጠሉ ሰንበትበት ብለዋል።

በተለይም ከነሐሴ ወር ማገባደጃ 2013 በኋላ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ኦነግ ሸኔ በንጹኃን ላይ በሚሰነዝረው ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት በየቀኑ የብዙዎች ሕይወት ማለፉን ተከትሎ፣ ቀሪዎቹ ነዋሪዎች ወደ ሚዲያ ተቋማቶች ድምጻቸውን ለማሰማት እንደተገደዱ ይናገራል።
ንጹኃን የድረሱልን ጥሪያቸውን ማቅረቡን፣ የሚዲያ ተቋማት መዘገቡን ተያይዘውታል፤ ነገር ግን ከድካም ውጭ የተቀየረ ነገር የለም የሚለው ሰይድ፣ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ ቀጣዩን መልዕክት አስተላልፎ ንግግሩን አጠናቋል።

አሁን ላይ አገራችን ያለችበትና በአካባበው የሚያስተውለው ጦርነት ቀላል የማይባል የሥነ- ልቦና ጉዳት እንዳስከተለበት የሚናገረው ሰይድ፣ “እንደ አለመታደል ሆኖ እርስ በእርሳችን ለመባላት ከተገባበዝን፣ ቀድሞ ከተናገረው በግማሽ የዳነ መሆኑን በማመን ከሕልፈታቸው በፊት ድረሱልን ቢሉም ከመሞታቸው ያላመለጡት የንጹኃኑን የድረሱልኝ ጥሪ የቅዠት ተስፋ ሆኖ ቀርቷል” ሲል ነው የተናገረው።

አያይዞም ‹‹ሊፈጠር በሚችለው ችግር ድረሱልን የሚል ጥሪ በተደጋጋሚ ሲሰማ መፍትሔ መሆን ሲገባ፣ በአንደኛው ጆሮው ሰምቶ በሌላኛው ማፍሰስ መሆኑን ከማስመስከር የዘለለ ምን ስያሜ ሊሰጠው ይችላል? ብሎ ይጠይቃል። ሰይድ፡ በተለያዩ አካባቢዎች በጅምላ እየተጨፈጨፉ ያሉት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከመሞታቸው በፊት ወደ መንግሥት ድረሱልን ብለው በተደጋጋሚ ለፍፈው ነበር። ሰሚ ጆሮ ከተነፈጋቸው ግን ሰንበትበት ብለዋል›› በማለት ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጸው።

አንድ ዓመት ወደ ኋላ መለስ ብለን ብንመለከት በሕዝብ ተወካዮች ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት ጥቅምት 30/2012 ማይካድራ ላይ በሰነዘረው ንጹኃን ላይ ያነጣጠረ የጀምላ ጭፍጭፋ በአንድ የመቃብር ጉድጓድ እንኳን 74 ሰዎች ተቀብረው እንደተገኙ እና በአንድ ቀን ውስጥ ከስድስት መቶ በላይ ንጹኃን አንደተገደሉ፣ እንዲሁም በመጨረሻም ኢሰመኮ ባደረገው ጥናት መሰረት በጠቅላላው ከ1ሺሕ በላይ የሚገመቱ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ መዘገቡ የሚታወስ ነው።

ጥቃቱ ሲሰነዘርበት በነበረበት ወቅት የአካባቢው ማኅበረሰቦች የድረሱልን ጥሪ ቢያሰሙም ማንም ሊደርስላቸው ባለመቻሉ የሞትን ጽዋ እንዲቀምሱ ተላልፈው መሰጠታቸውን በወቅቱ ሲዘግቡ የነበሩ የኢትዮጵያና የውጭ ሚዲያዎችን ሪፖርት ዘወር ብለን መመልከት ብቻ የድርጊቱን እውነታ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው።

የግድያውን መንስኤ ለመረዳት ያክል ማይካድራ ላይ “እየተጨፈጨፍን ያለነው የአማራ ተወላጆች በመሆናችን ብቻ ነው” በማለት በወቅቱ ሲናገሩ የነበሩት የገፈቱ ቀማሾች እንደነበሩ የሚታወስ ነው። ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ በአፋር፣ በአማራ፣ በቤንሻነጉል ጉምዝ፣ በኦሮሚያ፣ እና በትግራይ ክልል እየተገደሉ ያሉ ሰዎችም ለሚሰነዘርባቸው ጥቃት ምክንያቱ ያው ዘርን መሠረት ያደረገ መፍትሔ ሊሰጠው ያልቻለ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል።

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ያሉ ነዋሪዎች “በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች እየተገደልን ነው” ካሉ ሰንበትበት ያሉ ለመሆናቸው የውጭም የውስጥ አገር የሚዲያ ተቋማት ሪፖርቶች ምስክር ናቸው። ቢሆንም ግን ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ችግሩ እንደቀጠለ የአካባቢው ነዋሪዎች ያወሳሉ።

ሽብርተኛ የተባለው የሽኔ ታጣቂ እስከዛሬ ድረስ ጥቃት እያደረሰብን ነው የሚሉት የኪረሙ ወረዳ ነዋሪ፣ ባሳለፍነው ጥቅምት 3/2014 “ድረሱልን እባካችሁ ድምጽ ሁኑንና ወደ መንግሥት ጩኹልን፣ በዚህ ሳምንት ብቻ በኪረሙ ወረዳ ሀሮ ቀበሌ የሟቾች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ ነው፤ መንግሥት መከላከያ አስገብቶ ያድነን ዘንድ አሳስቡልን” ሲሉ ነው የተናገሩት።

በአፋር ክልል የሚገኙ ዜጎች በበኩላቸው፣ ሽብርተኛ በተባለው ህወሓት ከሐምሌ ወር 2013 ጀምሮ ጥቃት እየተሰነዘረባቸው መሆኑን ሲናገሩ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ባለንበት የጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት በድጋሚ ጥቃቱ እንደተጀመረና በአካባቢው ንጹኃን እየሞቱ መሆኑን ለተለያዩ ሚዲያዎች እየተናገሩ ይገኛሉ።

ከዚህም በተጨማሪ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ዜጎች በበኩላቸው፣ ከሐምሌ ወር 2013 ጀምሮ ንጹኃን እየተገደሉ መሆኑን ከተናገሩ ሰንበትበት ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ሽበርተኛ የተባለው ህወሓት ያለማቋረጥ ጥቃት እየሰነዘረባቸው መሆኑን የአዲስ ማለዳ ምንጮች አመላክተዋል።

የአገራችን ኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት፣ ሰብዓዊ መብትን ለመጠበቅ የተደነገጉ በቂ አንቀጾች እንዳሉት የሚታወቅ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካካል አንቀጽ 25ትን ብንመለከት ‹‹ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በዘሩ፣ በእምነቱ፣ በጾታው፣ እንዲሁም በሌሎች ምክንቶች መድሎ አይደረግበትም ይላል።››

በተጨማሪም አንቀጽ 10 ‹‹የዜጎችና የሕዝቦች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ ይላል።›› ኢትዮጵያ ብዙ የጸደቁ ሕጎች በጽሑፍ አሏት እንጂ ተግባር ላይ ላለመዋላቸው በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው ጦርነት ሕያው ምስክር ነው የሚሉ ሰዎችን መስማት እየተለመደ መጥቷል።

በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት መሠረት ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ በየትኛውም አካባቢ ተዘዋውረው የመኖር የእኩልነት መብት አላቸው። ነገር ግን ይህ በተግባር ላይ እየዋለ ላለመሆኑ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋለ ያለው ችግር ማሳያ ነው የሚሉት በባህርዳር ከተማ የሕግ መምህር ሆነው የሚያገግሉት ተመስገን ሲሳይ (ፕ/ር) ናቸው።

አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አገራት የተቀመጡ የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብቶችን የመመሪያ ሕግጋቶች አድርጋ ተቀብላ አጽድቃቸዋለች። ከእነዚህም መካከል ኹሉም ኢትዮጵያዊያን ዘርና ቀለም ሳይገድባቸው በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው የመኖርና የመሥራት መብት እንዳላቸው የሚያሳስበው አንቀጽ ይታወቃል ይላሉ የሕግ ባለሙያው።

ነገር ግን፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የዜጎች ሰብዓዊ መብት እየተጣሰ ይስተዋላል የሚሉት ተመስገን ሲሳይ፣ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ የመንግሥት ትልቁና ዋናው ኃላፊነት ዜጎች ባሉበት አካባቢ ሠላምና ደህንነታቸውን ማስጠበቅ ነው። ይህን ካላደረገ ግን ኃላፊነቱና ግዴታውን አልተወጣም ማለት ነው ሲሉ ነው አስተያየታቸውን ያስቀመጡት።

አክለውም፣ አሁን በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል፣ በአማራና በአፋር ክልል ልዩ ልዩ አካባቢዎች የሰው ልጆች እየተፈናቀሉ፣ ሕይወታቸውን እያጡና አካላቸውም እየጎደለ እንደሆነ በመናገር የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከሚዲያ ተቋማት መካከል የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እራሱ ጉዳዩን በተደጋጋሚ እንደዘገበው የሚመሰክሩት ተመስገን፣ ከእያንዳንዱ ማኅበረሰብ የሚጠበቀው ኃላፊነት እንዳለ ሆኖ በመንግሥት በኩል እስካሁን ለችግሩ መፍትሔ አለመገኘቱ ግን የሚያመላክተው፣ መንግሥት ማድረግ ያለበትን ያላደረገ መሆኑን ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አያይዘውም፣ የመንግሥት መኖሩ ትልቁና ዋናው ኃላፊነት ዜጎች ደህንነት እንዲሰማቸው፣ ሕይወታቸው፣ ንብረታቸው እንዲሁም ጤናቸው እንዲጠበቅ ማድረግ ሲሆን፣ አሁን እየሰማን ያለው ሁኔታ ግን የሚያሳየው መንግሥት ግዴታውን ያልተወጣና ኃላፊነቱን ያላከበረ መሆኑን ነው ይላሉ።

የዜጎች ግዴታ እንዳለ ሆኖ ከመንግሥት ግዴታ ስንነሳ፣ ዜጎች ተናገሩም አልተናገሩም የመንግሥት ትልቁና ዋናው ኃላፊነት በየትኛውም አካባቢ የሚኖረውን ሰው ጥቅምና መብት ማስከበር ነው የሚሉት የሕግ መምህሩ፣ አሁን እየሆነ ያለው ግን ይህ እንዳልሆነ አብራርተዋል። ለዚህም ምክንያቱ ኢትዮጵያ በፌደራልና በክልል ደረጃ ያዋቀረቻቸው የጸጥታ አካላት ኃላፊነታቸው በተመደቡበት አካባቢ ያሉ ዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ቢሆንም፣ ይህን ማድረግ አለመቻላቸው ነው ሲሉ አስረድተዋል።

አያይዘውም፣ ዜጎች ድረሱልን ብለው መናገራቸውና አለመናገራቸው እንዳለ ሆኖ ሕይወታቸውና ንብረታቸው ጠፍቶ፣ አካላቸው ጎድሎ መመልከታችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ማብራሪያ መንግሥት የተጣለበትን ግዴታውን አልተወጣም ወደሚል ድምዳሜ ለመድረስ ያስችላል ነው ያሉት።

ተመሰገን አያይዘውም፣ አዲስ መንግሥት ተመሠረተ ሲባል የሰዎችን ደኅንነትና ሕልውና ለማረጋገጥ የሚያስችል ተቋም እንደሚሆን በማመን ኹሉም ሰው ተስፋ እንደነበረው የገለጹ ሲሆን፣ ይህ በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት ታአማኒነቱ እንዲቀጥል፣ በርግጥም ዜጎች መርጠውኛል ብሎ እንዲያምን በየትኛውም አካባቢ የሚገኙ የአገሪቱን ዜጎች ደኅንነት መጠበቅ አለበት ሲሉ አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል። በመጨረሻም ይህን በመንግሥት በኩል አልን እንጅ ችግሩን ለመቅረፍ የኹሉም የአገሪቱ ዜጎችና ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ትብብር ያስፈልጋል በማለት ነው ምክራቸውን የለገሱት።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here