የእስክንድር ድብደባና ምስክሮቹ

0
427

ከጦርነቱ ቀጥሎ ሠሞኑን መነጋገሪያ የሆነው ርዕሰ ጉዳይ የባልደራስ አመራሮች ላይ የቀረቡ ምስክሮችን የተመለከተ ነበር። በዚህ ጉዳይ ሕብረተሰቡ ተወያይቶና የሆነውን ተችቶ ሳያበቃ፣ እስክንድር ተደበደበ የሚል ዜና ማኅበራዊ ሚዲያውን ተቆጣጥሮት ነበር።
ተደብድቦ ፍርድ ቤት መምጣት አልቻለም ከመባሉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የምስክር ማሰማት ሒደት ተጀምሮ ነበር። በዕለቱ በእነእስክንድር ላይ ሊመሰክሩ ከቀረቡት መካካል አንዱን፣ “እግዚአብሄር ይቅር ይበልህ” ብሎ እስክንድር ነጋ ሦስት ጊዜ ደጋግሞ መናገሩ መወያያ ሆኖ ነበር።
ይህ ክስተት መወያያ መሆኑ ሳያባራ፣ ሌላ እውነት ይፋ ተደርጎ የብዙዎችን አግራሞት ከማጫሩ በተጨማሪም ጥያቄ አስነስቶ ነበር። በነፍሰ ገዳይነቱ እና የዕድሜ ልክ እስረኛነቱም የሚታወቅ ግለሰብ ምስክር ሆኗል መባሉ ነበር ብዙዎችን ያስደነቀው። ሴቶችን በመድፈር በሰፈራቸው ያስቸገረ እንደነበር፣ ነፍሰ ገዳይ መሆኑን፣ እንዲሁም በእስር ቤት ጭምር ሰው ላይ ያልሆነ ወሬ በማቀበል የሚታወቅ እንደነበረ በርካቶች ስለእሱ ጽፈዋል።
የግለሰቡ ሰብዕና እንደዚህ መነጋገሪያ የነበረው፣ በሕግ አንድ ሰው መመስከር የሚችለው ባህሪው ተጠንቶ ታማኝ የማይዋሽ መሆኑ ከተረጋገጠ ነው። ይህ ሰው ግን በተደጋጋሚ በወንጀል የተቀጣ ባህሪው ምሳሌ የማይሆን መሆኑ የፍትሕ ሥርዓቱን ችግር አጉልቶ የሚያሳይ ነው ሲሉ ብዙዎች ሐሳባቸውን ሠንዝረዋል።
ሌላ ምስክር ሆኖ የቀረበም፣ ተከሳሾቹን እንደማያውቃቸውና የባልደራስ ፓርቲ አባል እንዳልሆነም ለፍርድ ቤቱ በመናገር መስክር ተብሎ ብቻ መምጣቱን ተናገረ ተብሎ ለበርካቶች አስተያየትም ምክንያት ሁኖ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በቀጣይ ቀን ቀጠሮ ምስክር ሊሰማ ሕዝብ ተሰብስቦ ባለበት እስክንድር ድብደባ ስለተፈጸመበት መምጣት አልቻለም መባሉ ጉድ አሰኝቷል። በማረሚያ ቤት ለኹለተኛ ጊዜ መደብደቡን፣ በሕይወቱ ላይም አራተኛው የመግደል ሙከራ መሆኑንም እያጣቀሱ ድርጊቱን ብዙዎች ኮንነውታል።
በድብደባው ምክንያት የምስክር መስማቱ ሒደት ለሰኞ ቢቀጠርም፣ ችሎት ሊከታተሉ የሔዱ 40 ሰዎች ከፍረድ ቤት እንደወጡ በጅምላ ታስረው ማረሚያ ቤት መወሰዳቸውም ሌላ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኖ ነበር። ከታሰሩት 5ቱ ተመርጠው ያድራሉ ተብሎ በእለቱ ሲጠብቋቸው ለነበሩ መነገሩ የታሰበበት እስኪመስል አግራሞትን የፈጠረ ክስተትም ነበር።
ሒደቱ የተወሳሰበ ቢሆንም፣ በኋላ ላይ ሁለቱ ደብዳቢዎች አብረው ታስረው በነበሩበት ጊዜ ስጋት መሆናቸው ተነግሮ ወደ ቃሊቲ እንደዘዋወሩ ከተደረገ በኋላ በእለቱ መመለሳቸው ለምን? ማን ጠይቆ? አስብሏል። ምክንያቱስ ምን እንደሆነ፣ ያንንስ ቀን ለምን እንደመረጡ የተብራራ ነገር የለም። እስክንድር ነጋ ላይ የደረሰው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነም በዝርዝር ይፋ ባይደረግም፣ ግንባሩና ጉልበቱ ላይ የመቁሰል አደጋ እስኪደርስበት ድረስ መደብደቡ
ተነግሯል::


ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here