በ2014 በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበ ቆዳና የቆዳ ምርቶች 10 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንደስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ባለፈው መስከረም 30 በተጠናቀቀው የ2014 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት፣ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንደስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከውጭ ገበያ ለማግኘት ካቀደው 13.3 ሚሊዮን ዶላር 10.3 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን ኢንስቲትዩቱ ኮሚኒኬሽን ጉዳይ ዳይሬክተር የሆኑት ብርሃኑ ሰርጀቦ ገልጸዋል። ይህም ኢንስቲትዩቱ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለማግኘት ካቀደው አንጻር አፈጻጸሙ 78 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል::
ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው የቆዳ ውጤቶች በአራት ደረጃ የተከፈሉ መሆናቸውን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳይ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። የመጀመሪያው ‹ፒክል› የሚባል ሲሆን፣ የመጀመሪያው የቆዳው ጸጉር ከተላቀቀ በኋላ ለገበያ የሚቀርብ ነው። ኹለተኛው ‹ዌትብሉ› የሚባል ሲሆን፣ የተወሰነ ኬሚካል ተጨምሮበት ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ነው።
ሦስተኛው ‹ክረስት› የሚባል ሲሆን፣ በከፊል ያለቀ ማለት ሲሆን፣ አራተኛው ደግሞ ያለቀለት ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቆዳ ሲሆን፣ ሦስቱን ደረጃዎች አልፎ ሙሉ በሙሉ ያለቀለት ቆዳ ማለት መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። አራቱንም ደረጃዎች ለውጭ ገበያ ከሚያቀርቡ የቆዳ ውጤት አምራቾች 9.1 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ በሩብ ዓመቱ የተገኘው ገቢ 7.3 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ከ2013 በፊት ኢትዮጵያ ለውጭ በብዛት የምታቀርበው ያልቀለት ቆዳ እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፣ አሁን ላይ ያላለቀላቸው ቆዳዎችንም ለውጭ ገበያ እያቀረበች ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ያለቀለት ቆዳ ብቻ ውጤት አለማምጣጡን ተከትሎ ከ2013 ወዲህ ሒደታቸው ያልተጠናቀቀ ቆዳዎች ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ መፈቀዱ ተገልጿል።
በቆዳ ውጤቶች ዘረፍ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙት ምርቶች መካከል ጫማ አንዱ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለማግኘት ከታቀደው 2.4 ሚሊዮን ዶላር የተገኘው ገቢ 800 ሺሕ ዶላር ነው። በጫማ ዘርፍ የሚፈለገውን ያክል የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ያልተቻለው፣ ሥራ ላይ የነበሩ ጫማ አምራች የውጭ ድርጅቶች ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ የምርት ሥራ በማቆማቸው መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። ጫማ አምራቾቹ የማምረት ሥራቸው ያቋረጡት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባስከተለው የገበያ መቀዛቀዝ ምክንያት ገበያዎች በመዘጋታቸው ነውም ተብሏል።
የምርት ሥራ ያቆሙት ድርጅቶች ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው ጫማ 80 በመቶ የሚደርሰውን ምርት የሚሸፍኑ እንደነበሩ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከጫማ የተገኘው የውጭ ገቢ አብዛኛው በአገር ውስጥ ጫማ አምራቾች ከቀረበ ምርት ነው:: ሌላኛው ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው የቆዳ ውጤት ጓንት ሲሆን፣ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከጓንት ለማግኘት የታቀደው 530 ዶላር ገቢ ከ99 በመቶ በላይ መሳካቱ ተመላክቷል። አንዲሁም ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ የቆዳ አልባሳት 990 ሺሕ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ፣ 1.7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።
የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንደስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ2013 በጀት አመት ለማስገባት አቅዶ ከነበረው የውጭ ምንዛሬ ግኝት ውስጥ ከግማሽ በታች ብቻ ማግኘቱን አዲስ ማለዳ መዘገቧ የሚታወስ ነው። ተቋሙ በበጀት ዓመቱ 100 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማስገባት አቅዶ ወደ ሥራ ቢገባም ማሳካት የቻለው ግን 40 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነበር። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዘርፉን እጅጉን እንደፈተነው እና የታቀደውን ያህል የውጭ ምንዛሬ እንዳይገኝም ትልቅ እንቅፋት እንደፈጠረ መግለጹ የሚታወስ ነው።
ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



