‹‹የአቦቦ-ሜጤ፤ አቦቦ-ኪ.ሜ 76›› የአስፋልት መንገድ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተገለጸ

0
630

የጋምቤላ እና የደቡብ ክልሎችን የሚያስተሳስረው ‹‹የአቦቦ-ሜጤ፤ አቦቦ-ኪ.ሜ 76›› የአስፋልት መንገድ የሚል መጠሪያ ስም ያለው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ ለትራፊክ ክፍት ሆኖ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ 98 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ ቀሪ ውስን ሥራዎች ማለትም የእግረኛ መተላለፊያ ዜብራ፣ የመንገድ ላይ የትራፊክ ቅቦች የማቅለም ሥራ እንዲሁም ሌሎች ከመንገድ ግንባታው ጋር የተያያዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ነው የተባለው። እነዚህ የማጠቃለያ ሥራዎች አሁን ላይ የትራፊክ ፍሰቱን የማያስተጓጉሉ እንደሆኑ እና በኹለት ወር ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቁም ባለሥልጣኑ ጨምሮ ገልጿል።
ለመንግድ ግንባታው አጠቃላይ 960 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን፣ ወጪው ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግሥት መሸፈኑ ተነግሯል።
ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው ቻይና ‹‹ሬይል ዌይ ሰቨንዝ ግሩፕ›› የተባለ ዓለም አቀፍ መንገድ ሥራ ተቋራጭ ድርጅት ሲሆን፣ ፕሮጀክቱን የማማከር እና የመቆጣጠር ሥራ የሚሠራው ደግሞ ‹‹ሲቪል ወርክስ ኮንሰልቲንግ ኢንጅነርስ›› የተባለ አገር በቀል ድርጅት ነው።
መንገዱ 74.65 ኪ.ሜ. የሚረዝም መሆኑን እና መነሻውን የአኝዋ ዞን መቀመጫ ከሆነችው አቦቦ ወረዳ በማድረግ አልዌሮ ግድብ ሰፈራ፣ ቴኒ፣ ዱቦንግ፣ ፖታለም እንዲሁም ኩኩሪ የተሰኙ ከተሞችን እንደሚያቆራኝም ተነግሯል።
የመንገዱ መገንባት በአካባቢው የሚመረቱ በቆሎ፣ ሩዝ እና ፍራፍሬ እንዲሁም የቅባት እህሎችን ወደ ማዕከላዊ ገበያ በስፋት እና በአነስተኛ ወጪ ለማድረስም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተጠቁሟል።


ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here