በአዲስ አበባ ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ ታክሲዎች ተሳፋሪዎችን እጥፍ እያስከፈሉ ነው

0
1543

በአዲስ አበባ ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ ታክሲዎች ተሳፋሪዎችን እጥፍ እያስከፈሉ ነውበአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች አስቸኳይ ጊዜ መታወጁን ሠበብ በማድረግ ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ ተሳፋሪዎችን እጥፍ እያስከፈሉ ነው።
አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በተለያዩ የአዲስ አበባ ታክሲ መጫኛ እና ማውረጃ ቦታዎች ተገኝታ እንደተመለከተችው፣ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ታክሲዎች ዕጥፍ እና አንዳንዶቹ ከዕጥፍ በላይ ዋጋ እያስከፈሉ መሆኑን ታዝባለች።

ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ እጥፍ የሚያስከፍሉ ታክሲዎች በሚጭኑባቸው አንዳንድ ቦታዎች ላይ ምንም ዓይነት ተቆጣጣሪ አለመኖሩን አዲስ ማለዳ በተገኘችባቸው ቦታዎች ለመታዘብ ችላለች። ምንም እንኳን ተቆጣጣሪ ባይኖርም ተራ በማስከበር ከባለታክሲዎች ብር የሚሰበሰቡ ተራ አስከባሪዎች መኖራቸውን አዲስ ማለዳ ታዝባለች። ይሁን እንጂ ባለ ታክሲዎች የሚጭኑበተን ዋጋ ለተሳፋሪዎች ከመጫናቸው አስቀድመው በእጥፍ አሳድገው በግልጽ ቢናገሩም ተራ አስከባሪዎች እየሰሙ ጭማሪ እንዳይደረግ ሲያደርጉ አይታይም።

በተወሰኑ የታክሲ መጫኛ እና ማውረጃ ቦታዎች ላይ ተራ አስከባሪዎቹ ራሳቸው ተሳፋሪዎች የሚከፍሉትን ዋጋ በእጥፍ ጨምረው እየነገሩ ወደ ታክሲ ሲያስገቡ አዲስ ማለዳ ታዝባለች። በዚህም ተሳፋሪዎች ለባለ ታክሲዎች በእጥፍ ጨምረው ሲከፍሉ፣ ተራ አስከባሪዎች የሚቀበሉት የተራ ማስከበሪያ ብርም በእጥፍ ይጨምራል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የትራንሰፖርት ተጠቃሚዎች “ባለታክሲዎች እጥፍ ቢያስከፍሉንም እየመሸ ስለሚሄድ እና ሕግ የሚያስከብር አካል በሰዓቱ ባለመኖሩ ለመክፈል እየተገደድን ነው” ሲሉ ተናግረዋል። አዲስ ማለዳ በተመለከተቻቸው አካባቢዎች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባለታክሲዎች ለምን የዋጋ ጭማሪ እንዳደረጉ ጠይቃ ያገኘችው ምላሽ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን እና ምሽቱን ምክንያት በማድረግ የተጨመረ እንጅ ምክንያታዊ ጭማሪ እንዳልሆነ ነው።

መንግሥት በመላው ኢትዮጵያ ተፈጻሚ የሚሆን አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ካዋጀበት ቀን ጀምሮ በአዲስ አበባ ምሽት ላይ ያለው እንቅስቃሴ እንደወትሮው አለመሆኑን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች። የከተማዋ ነዋሪ የምሽት እንቅስቃሴ በመጠኑም ቢሆን የመቀዛቀዝ ሁኔታ ይታይበታል።
የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባለ ታክሲዎች ይህን አጋጣሚ ትርፍ ለማግኘት እየተጠቀሙበት መሆኑን አዲስ ማለዳ ባለፉት ቀናት በተለያዩ አካባቢዎች ምሽት ላይ ተገኝታ ተመልክታለች። ባለ ታክሲዎች ወትሮውንም ምሽት ላይ የዋጋ ጭማሪ የሚደርጉ ቢሆንም፣ አሁን ላይ የሰዓት ማሻሻያ አድርገው የተናበበ በሚመስል ሁኔታ ከአንድ ሰዓት በኋላ በእጥፍ ከማስከፈላቸው በተጨማሪ መጫን ከሚችሉት በላይ እንደሚጭኑ አዲስ ማለዳ ታዝባለች።

ወቅቱን ተጠቅመው የሕግ ጥሰት የሚፈጽሙ የትራንስፖርት አግልግሎት ሰጭዎች መኖራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አረጋዊ ማሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ነዋሪው ወቅቱንና አስቸኳይ ጊዜውን መሠረት በማድረግ በጊዜ የመግባት አዝማሚያ መኖሩን በመረዳት ትራንስፖርት ቢሮው ባለሙያዎችን አሰማርቶ ልዩ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

ቢሮው ወቅቱን መሠረት በማድረግ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማሳለጥ ባለሙያዎችን ቢያሰማራም፣ ነዋሪው በጊዜ ለመግባት የሚደርገውን ጥረት እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ ባለ ታክሲዎች መኖራቸውን አረጋዊ ጠቁመዋል።
ቢሮው የሚታየውን ሥርዓት አልበኝነት ወደ ሥርዓት ለማስያዝ እየሠራ መሆኑን የጠቆሙት አረጋዊ፣ የትራንስፖርት ተጠቃሚው መብቱን ለማስከበር ጥቆማ በመስጠት መተባበር እንዳለበት ገልጸዋል። ቢሮው ሕግ ለማስከበር በሚያደርገው ጥረት ችግሩን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ስለማይቻል፣ ማኅበረሰቡ እና ባለ ድርሻ አካላት ትብብር ማድረግ ይገባቸዋል ተብሏል።

በከተማዋ በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታየው የሕግ ጥሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። በዚህም ሕግ በመጣስ ተጠያቂ የሚሆኑ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች ቁጥር እየጨመረ ነው ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here