የእንስሳት ክትባት መድኃኒት የሽያጭና የአቅርቦት መጠን በ2014 በጀት አንደኛ ሩብ ዓመት ከታቀደው በታች መሆኑን የብሔራዊ እንሰሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
የእንስሳት ክትባት ምርቶች አቅርቦትን በተመለከተ፣ በ2014 በጀት አንደኛ ሩብ ዓመት በአጠቃላይ በውስጥና በውጭ አገራት 79.19 ሚሊዮን ዶዝ የክትባት ምርት በማቅረብ 54.65 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ቢታቀድም፣ 50.70 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት በመሸጥ 39.46 ሚሊዮን ብር መገኘቱን የብሔራዊ እንስሳት የጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አደይአበባ ታምሩ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዋ አያይዘውም፣ በዘንድሮው በጀት ሩብ ዓመት ከክትባት አቅርቦትና ሽያጭ የተገኘው ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን 21.52 ሚሊዮን ዶዝ፣ እንዲሁም በገንዘብ በ5.34 ሚሊዮን ብር ዝቅ ያለ አፈጻጸም ማሳየቱን ነው የገለጹት።
በኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዋ ገለጻ መሠረትም፣ በክትባት ሽያጩ የተገኘው ገቢ ከታቀደው በታች ሲሆን፣ በፐርሰንት ደረጃም ሲሰላ የሩብ ዓመቱን የመጠን ዕቅድ 64 በመቶ እና በገንዘብ 72 በመቶ እንደተከናወነ ነው መረዳት የተቻለው።
አደይአበባ አገሪቱ ያላት የሠላም ሁኔታ የክትባት ሽያጭ መጠን እንዲቀንስ ማድረጉን ነው የጠቆሙት።
ከኢንስቲትዩቱ የመረጃ ምልከታም መረዳት የተቻለው፣ በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ ባሉ አካባቢዎች የእንስሳት ክትባቱን በተለመደው መልኩ ለሽያጭ ማሰራጨት አለመቻሉ፣ በሩብ ዓመቱ ይገኛል ተብሎ ከታቀደው ገቢ በታች ለመገኘቱ አንደኛው ምክንያት መሆኑን ነው።
ከእዚህም በተጨማሪ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ከዕቅድ በታች ለተገኘው ገቢ አስተዋጽዖ አድርገዋል ተብለው ከሚነሱ ችግሮች ተጠቃሽ መሆናቸውን አደይአበባ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
የውጭ ምንዛሬ ዕጥረቱ፣ የጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩቱ ለመግዛት አቅዷቸው የነበሩትን የመድኃኒት ኬሚካሎችን (ምን ያክል እንዳልተገዛ ገና በቁጥር ባይገለጽም) ሙሉ ለሙሉ መግዛት እንዳይቻል መሰናክል መሆኑን ኃላፊዋ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የእንስሳት ክትባት መድኃኒቶችን ከማምረት አኳያ፣ በሩብ ዓመቱ 89.07 ሚሊዮን ዶዝ የተለያዩ የባክቴሪያል፣ የቫይራልና የዶሮ ክትባቶች ለማምረት ታቅዶ እንደነበር ያመላከቱት የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዋ፣ 76.21 ሚሊዮን ዶዝ ክትባቶችን በማምረት የዕቅዱን 86 በመቶ ማከናዎን እንደተቻለም ነው የተናገሩት።
በሌላ በኩል፣ ኢንስቲትዩቱ በዐዋጅ ከመንግሥት በተሰጠው ኃላፊነት በመነሳት ሦስት የትኩረት መስኮችን ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ነው የተመላከተው።
ኢንስቲትዩቱ ሦስት የትኩረት መስኮች ላይ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል የሚሉት አደይአበባ፣ የመጀመሪያው ትኩረት የእንስሳት ክትባት ምርትንና ሽያጭን ማሳደግ ሲሆን፣ በዚህም ረገድ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የእንስሳት ክትባት ምርት በዓይነት፣ በመጠንና በጊዜ አምርቶ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የአገር ኢኮኖሚ አጋዥ መሆንና ትርፍና ትርፋማነትን ማሳደግ ላይ ማተኮሩን ገልጸዋል።
በኹለተኛ ደረጃ የተቀመጠው ትኩረት፣ የእንስሳት ክትባት ምርምርን ማጠናከር ሲሆን፣ በዚህ በኩል ደግሞ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም፣ ክትባት ላልተመረተላቸው የእንስሳት በሽታዎች ክትባት ማልማትና ኢንስቲትዩቱ ከሚያመርታቸው ክትባቶች ውስጥ መሻሻል የሚሹ ክትባቶችን የመለየት ሥራ ነው።
በሦስተኛ ደረጃ የእንስሳት መድኃኒቶችን የማቀነባበር ክንውን ታቅዶ የፋብሪካው ግንባታ መጠናቀቁን ኃላፊዋ ጠቁመው፣ ፋብሪካው የምርት ሥራው ሙሉ ለሙሉ ሲጀምር የእንስሳት መድኃኒቶችን በሚፈለገው ዓይነት፣ መጠንና ጥራት አቀነባብሮ ለተጠቃሚው ማኅበረሰብ በማዳረስ፣ ለተለያዩ የእንስሳት መድኃኒቶች የሚወጣውን የአገሪቷን የውጭ ምንዛሬ መቀነስ እንደሚያስችል ነው የተገለጸው።
የእንስሳት መድኃኒቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካው ተገንብቶ ቢጠናቀቅም አንዳንድ ያልተስተካከሉ ነገሮች በመኖራቸው ገና ወደ ሥራ አልገባም።
ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014



