የዐይን ያወጣው ጣልቃ ገብነት!

0
792

ሠሞኑን መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የምዕራባውያን በተለይም የአሜሪካ ጣልቃ ገብነትን የተመለከተ ነው። ጣልቃ መግባት የሚለው ቃል እስኪያንስና እኛ በአገራችን ጉዳይ ጣልቃ የገባንባቸው እስኪመስላቸው ድረስ ማስፈራሪያ መሰንዘርና ማዕቀብ መጣል ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
በግድቡም ሆነ በጦርነቱ ምክንያት በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያ ጉዳይን ደጋግመው በማንሳት የፈለጉትን ሊጭኑብን እየተሯሯጡ ይገኛል። መላው አገሪቷን የሚጎዳ ውሳኔን ሲወስኑም ኹሉም በመቆጣት ፈንታ ፖለቲካዊ ይዘት በመስጠት ሲደሰትም ሆነ ዝም ብሎ ሲመለከትም የነበረ አለ። ከአጎዋ አባልነት ማስወጣት መብቷ ቢሆንም፣ ከዓለም አገራት ጋር ያለንን ግንኙነት ለማቋረጥ ብላ ያየችውን ድንጋይ ሁሉ ስትፈነቅል ዝም መባል አልነበረባትም።

በጦርነቱ መጀመሪያ ሰሞን ዕርዳታን ጣልቃ መግቢያ አድርጋ የነበረችው አሜሪካ፣ በኋላ ላይ ቀጥታ በውስጥ ጉዳይ በመግባት የሽግግር መንግሥትን እንደለመደችው አቋቁማ እውቅና ለመስጠት እየተንደፋደፈች ነው ሲሉ በርካቶች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ራሷን የዓለም ፖሊስ አድርጋለች እያሉ በጎ ሥም እየሰጡ ሊወቅሷት የሚሞክሩ ቢኖሩም፣ ውስጠ ሥራዋን የሚያውቁ ግን ሕጋዊ ሌባ በመሆን እየሠረቀችና እያሠረቀች ለመኖር እየተፍጨረጨረች ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሠንዝረዋል።

“… ካላሉት፣ ገብቶ ይፈተፍታል” እንደሚባለው፣ አሜሪካና አጋሮቿ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብተን እንወስንላችሁ ሲሉ የመጀመሪያቸው አይደለም። የአሁኑን ለየት የሚያደርገው ፊት ለፊት ሳያፍሩ ውሸትን ተመርኩዘው ጫና ለማሳደርን የፈለጉትን በግላጭ ሥልጣን ላይ ለማስቀመት መፈለጋቸው ነው ሲሉ ምልከታቸውን ያስነበቡ አሉ።

ምዕራባውያን እንደፈለጉ በእኛ ጉዳይ እየገቡ ሲወስኑብን ዝም ብለን ማየት የለብንም የሚሉ ብዙዎች ናቸው። እኩልነታችንን እንዲያከብሩልን መጠበቅ የለብንም፤ እኛው ነን ማስከበር ያለብን የሚሉ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል። የአቻ ግንኙነት እንዲሆን በሆነ ነገር ሲጎዱን በአቅማችን እኛም ምላሹን መስጠት አለብን ይላሉ። አጸፋውን ለመመለስ በእነሱ የውስጥ ጉዳይ መግባት ባይጠበቅብንም፣ እዚህ ያላቸው የሚሳሱለት ጉዳይ ላይ ውሳኔ ማሳለፍ ግድ ይላል።

መንግሥት ሳይፈራ ቁርጡን አውቆ ዓለም አቀፍ ሕግ በማይከለክለው አማራጭ መጠቀም እንዳለበት በርካቶች ሲወተውቱ ነበር። ለምሳሌ፣ ኤምባሲዎቻቸውን በተመለከተ እኛ በእነሱ አገር ባለን ተመጣጣኝ ስፋት ያላቸውን ሰፋፊ ግዛት መቀነስ፣ አሊያም ከከተማ መሃል ርቀቱ በንፅፅር ተሰልቶ ምትክ የሚያገኙበትን መንገድ መዘርጋት ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ዜጎቻቸውን ሲያስወጡ ሌሎችን እንዲጨምሩ ማድረግ፣ ፈቃዳቸውን መሠረዝና ተመጣጣኝ የሆነ ክብራችንን የሚያስመልስልንን ዕርምጃ መውሰድ እንደሚገባ የፃፉ አሉ። በተቃራኒው ምን ይውጠናል በሚል የሚለማመጡ የፈሩት እንደማይቀርላቸው ተገንዝበው፣ ራሳችንን የመቻያ አጋጣሚ እንድናደርገው የጠየቁም አሉ።

አንዳንዶች ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው ጦርነት ዘመናዊ ባርነትን ማስቀጠያ ነው በሚል በአፍሪካውያን ጭምር የተሰጠ አስተያየት ላይ በመመርኮዝ፣ አፍሪካውያን አንድ ሆነን ኢምፔሪያሊስቶችን እንደቀደመው ዘመን እንፋለም እያሉ ጥሪ አቅርበዋል። ጣልቃ ገቢዎች ላይ ኢትዮጵያ የምትወስነውን ውሳኔ ሌሎች አፍሪካውያንና ድሃ አገሮች በአንድነት እንዲወስኑም ቅስቀሳ መሥራት እንዳለበት የጠቆሙ አሉ። ነግ በኔ ነውና እስከመቼ እሹሩሩ እያልናቸው እንቆያለን በማለት፣ የጭቆና ቀንበርን ለመስበርና እውነተኛ ነጻነትን ለማግኘት ጊዜው አሁን እንደሆነ በርካቶች ተናግረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here