ዳሸን ባንክ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ገንዘብ በቀላሉ መላክና መቀበል የሚያስችል ሥምምነት መፈራረሙ ተገለጸ

0
902

ባንኩ “ቱንስ” ከተሰኘ ዓለም አቀፍ የክፍያ ኔትወርክ ተቋም ጋር መስማማቱ ነው የታወቀው። ይህም ደንበኞቹ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ገንዘብ በቀላሉ መላክ እንዲሁም የሚላክላቸዉን ገንዘብ መቀበል እንደሚያስችላቸው ተመላክቷል።
ኹለቱ ተቋማት ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ በአጭር ጊዜና በተመጣጣኝ ክፍያ ለመላክ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸዉ፣ ዳሽን ባንክ የኢትዮጵያን የፋይናንስ አገልግሎት ዘርፍ ለመለወጥና ደንበኞቹን በተሻሉ የፈጠራ ዉጤቶች ለማገልገል ለሚያደርገው ጥረት፣ ተጨማሪ አዎንታዊ ዕርምጃ እንደሚፈጥርለትም የባንኩ ባለሙያ አስረድተዋል።
ይህ የተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮችን የሚያቀርብ ተቋም፣ ደንበኞች በባንክ ሒሳባቸውም ሆነ በአሞሌ የሞባይል ‹ዋሌት› በኩል ከዉጭ የሚላክላቸዉን ገንዘብ ፈጣንና አመቺ በሆነ መንገድ መቀበል የሚችሉበትን አሠራር ይዞ ከባንኩ ጋር በጋራ ለመሥራት መስማማቱ ነው የተገለጸው።
ይህም ሥምምነት፣ አዳዲስ ደንበኞች በዳሸን ባንክ ሒሳብ በመክፈትና በአሞሌ ዋሌት በኩል አገልግሎቱን በቀጥታ የማግኘት ፍላጎት ስለሚኖራቸዉ፣ ባንኩ የሚሰጠዉን የፋይናንስ አገልግሎት ይበልጥ እንደሚያሰፋውም በቱንስ በኩል ተገልጿል።
እንዲሁም፣ ቱንስ በአለም ላይ ገንዘብ የማስተላለፍ አገልግሎትን በማሳለጥ ታዋቂ ከሆኑ ተቋማት አንዱ ሲሆን፣ በበርካታ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ባንኮችና የገንዘብ ማስተላለፍ አገልጎሎት ተቋማትን በማገናኘት ገንዘብ ወደ ባንክ ሒሳብ፣ ሞባይል ዋሌትና ሌሎች አማራጮች ማስተላለፍ እንዲቻል ከፍተኛ ሚና በመጫወት እንደሚገኝ ተነገሯል።
ቱንስ በአሁኑ ወቅትም ዋና መሥሪያ ቤቱ በሲንጋፖር የሚገኝ ሲሆን፣ በለንደን፣ ፓሪስ፣ ሻንጋይ፣ ኒዉ ዮርክ፣ ዱባይና ናይሮቢ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች እንዳሉትም ለማወቅ ተችሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here