ለቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት የቀረበው ጥሪ የሚኖረው ፋይዳ

0
877

የአገር መከላከያ ሚኒስቴር የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት አባላት የአገር መከላከያን እንዲቀላቀሉ እና ኢትዮጵያ ከገጠማት ችግር ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት እንዲያግዙ ባሳለፍነው ሳምንት ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት አባላት፣ በመላው አገሪቱ በሚገኙ ከ290 በላይ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቻቸው አማካይነት በቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የልማትና የድጋፍ ማኅበር የታቀፉ ሲሆን፣ ማኅበሩ ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ መገባቷን ተከትሎ ከመከላከያ ጎን በመሰለፍ የበኩሉን ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጦርነቱ በተጀመረ ሰሞን መግለጹ የሚታወስ ነው።

ማኅበሩ በውስጡ ያቀፋቸው አባላት ከአገር መከላከያ ጎን ተሰልፈው ኢትዮጵያ ከገባችበት ጦርነት እንድትወጣ የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን የገለጸው ገና ጦርነቱ በተጀመረ ሰሞን ቢሆንም፣ በመንግሥት በኩል ጦርነቱ አንድ ዓመት እስከሚዘልቅ ድረስ ለማኅበሩ ፈቃድ ምላሽ አልተሰጠውም ነበር።

ማኅበሩ አገርን ለማገልገል አባላቱ ያላቸውን ፍላጎት ገልጾ፣ መንግሥት ጥሪውን ተቀብሎ ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ዕድሉን እንዲያመቻች የጠየቀው አባላቱ ካላቸው ሙያዊ ብቃት እና ፍላጎት አንጻር መሆኑን መግለጹ የሚታወስ ነው። አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በሚካሄደው ጦርነት ላይ በሠራቻቸው ዘገባዎች፣ የቀድሞው ሠራዊት አባላት ሙያዊ ሐሳባቸውን አካፍለው ነበር። በዘገባዎቹም ላይ ብዙዎቹ ከዚህ ቀደም በህወሓትና በደርግ መካከል በተደረገው ጦርነት ከህወሓት ጋር በጦር ግንባር ተገናኝተው የነበረና የጦር ስልቱን የሚያውቁት መሆኑ አስታውሰው፣ መንግሥት ጥሪያቸውን ቢቀበል ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እና የተሻለ የጦር ሜዳ ውጤት ለማስመዘግብ እንደሚችሉ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት ጥሪ ያቀረቡት ገና ጦርነቱ በተጀመረ ሰሞን ይሁን እንጅ፣ ምላሽ ሳይሰጣቸው ጦርነቱ አንድ ዓመት አስቆጥሯል። የአገር መካላከያ ሚኒስቴር ለአባላቱ ጥያቄ ከሰሞኑ በሰጠው ምላሽ፣ “በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን አገርን የማፍረስ ሴራ በማክሸፍ አገርን የማዳን ዘመቻ ላይ ባላቸው ዕውቀት፣ ልምድ እና አቅም ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ይህ አፍራሽ ኃይል እስኪደመሰስ ድረስ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ባላቸው ተነሳሽነት፣ ከአገር መከላከያ ጎን በመቆም አቅማቸውና ዕውቀታቸው የፈቀደውን አስዋጽዖ ለማበርከት ጥያቄ አቅርበዋል” ብሏል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ይህንን ተልዕኮ መወጣት የሚያስችል አካላዊ ሁኔታ፣ የጤና፣ የሥነ አእምሮ ዝግጁነት፣ እውቀት እና ልምድ ያላቸውን አባላት ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት አባላት ባቀረበው ጥሪ የመመልመያ መስፈርቶችን አስቀምጧል። በዚህም የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥትን የተቀበሉ፣ በሕዝቦች ሉዓላዊነትና አንድነት የሚያምኑ እና በፅናት ለማገልገል ሙሉ ፍቃደኝነት ያላቸው፣ ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነፃ የሆኑ፣ በወንጀል ይሁን በፍታ-ብሔር ተከሰው የፍርድ ቤት ክርክር የሌለባቸው እና መከላከያ በሚያሰማራቸው የጦር ክፍሎች ሁሉ ተዘዋውረው ለመሥራት ሙሉ ፍቃደኛ የሆኑና የአካል ብቃት ያላቸው መሆን አለባቸው ተብሏል። እንዲሁም፣ ለእግረኛ አዋጊ መኮንኖች ሻለቃ አመራርና ከዚያ በላይ ኃላፊነት የነበራቸው፣ በየትኛውም የማዕረግ ደረጃ ላይ በየማሰልጠኛ ማዕከላት አሠልጣኝ የነበሩ እና ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ፣ የሜካናይዝድ እና የቡድን መሣሪያ አመራርና ምድብተኛ የነበሩ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

በቀረበው ጥሪ መከላከያን መቀላቀል የሚችሉ አባላት የጤንነት ኹኔታን በተመለከተ የወጣው መስፈርት የዐይን፣ የአፍንጫ፣ የጆሮ፣ የጥርስ፣ የከንፈር ችግር የሌለባቸው፣ ከቲቢ፣ ከሚጥል በሽታ፣ ከስኳር፣ ከደም ግፊት፣ ከኪንታሮት፣ ከእንቅርት በሽታዎች ነጻ የሆኑ እና ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ የሆነ አካላዊ ችግር የሌለባቸው መሆን አለባቸው ይላል። እንዲሁም የትምህርት ማስረጃን በተመለከተ የተቀመጠው መስፈር ሁኔታ ማቀድ፣ ማሠልጠን፣ የሥልጠና ዶክሜንት ማዘጋጀት የሚያስችል የትምህርት ዝግጅት ያላቸው መሆን ይጠበቅባቸዋል።
የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ዕድሜን በተመለከተ ያቀረበው መስፈርት ከወታደር እስከ ከፍተኛ የበታች ሹም ያሉ ከ55 ዓመት ያልበለጡ፣ መስመራዊ መኮንኖች ከ60 ዓመት ያልበለጡ እና ከሻለቃ በላይ ያሉ ከፍተኛ መኮንኖች ከ64 ዓመት ያልበለጡ መሆን አለባቸው።

አባለቱ በሚመለመሉበት አካባቢ ከቀበሌ፣ ከመስተዳድር እና ከፖሊስ
ከወንጀል ነጻ ስለመሆናቸው የጽሑፍ ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ፣ የቀድሞ ጦር ሠራዊት አባል ስለመሆናቸው ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ መሆን ይገባቸዋል ተብሏል። የምዝገባ ጊዜው ከኅዳር 1/2014 እስከ ኅዳር 15/ 2014 መሆኑን የአገር መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የአገር መከላላከያ ሚኒስቴር ባቀረበው ጥሪ መሠረት፣ ጥያቄ ሲያቀርብ የነበረው የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የልማትና ድጋፍ ማኅበር ባሳለፍነው ማክሰኞ ምላሽ ሰጥቷል። ማኅበሩ በሰጠው ምላሽ መንግሥት ለረጅም ጊዜ ሲቀርብ ለነበረው ጥያቄ ምላሽ መስጠቱ ተገቢ መሆኑን እና አባላቱ ጥሪውን ተቀብለው በጦር ግንባር ለመሰለፍ ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጿል።

ማኅበሩ በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ጥቅምት 30/2014 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የቀረበው ጥሪ የማኅበሩን አባላት ያስደሰተ መሆኑን ገልጿል። መግለጫውን የሰጡት የማኅበሩ ፕሬዚደንት ኃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ፣ ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት ችግር እንድትወጣ በሚደረገው ጥረት ማኅበሩ አባላቱን በማስተባበር የበኩሉን እንደሚወጣ ጠቁመዋል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት አባላት ኢትዮጵያን ለማዳን በሚደረገው ጦርነት በቀጥታ በግንባር በመሰለፍ ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው በጦር ሜዳ ፍልሚያ በማድረግ፣ እንዲሁም ሠራዊት በማሰልጠን ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ማኅበሩ ገልጿል።
የቀድሞው የኢትዮጰድያ ጦር ሠራዊት እንደ አገር ኢትዮጵያ ብዙ ሀብት ያፈሰሰችብት እና በወታደራዊ ሳይንስ እና በዲስፕሊን የታነጸ ሠራዊት መሆኑን በመግለጫው ላይ የተገኙ አባላት ገልጸዋል። ሠራዊቱ የኢትዮጵያ ሀብት የፈሰሰበት እንደመሆኑ መጠን አሁንም የኢትዮጵያ ሠራዊት ሆኖ አገሩን ለማገልገል የሚያስችል አቅም እንዳለው ተገልጿል።

የሠራዊቱ ወታደራዊ ብቃት በወታደራዊ ሳይንስና ዲስፕሊን የታነጸ ከመሆኑም በላይ፣ የህወሓትን የውጊያ ስልት ከዚህ ቀደም ስለሚያውቀው ለሠራዊቱ ጥሪ መደረጉ መልካም አጋጣሚ መሆኑን አባላቱ ገልጸዋል። የቀደሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት መከላከለያን ተቀላቅለው አገራቸውን እንዲያገለግሉ ጥሪ መቅረቡ ለህወሓት ሥጋት ለመንግሥት ደግሞ ጥንካሬ እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።

ሠራዊቱ አሁን እየተካሄደ ባለው ጦርነት መሳተፉ በህወሓት በኩል ሥጋት እንደሚፈጥር የሚገልጹት አባላቱ፣ ሠራዊቱ ከመከላከያ ጎን ተሰልፎ ኢትዮጵያን ለማገልግል የሚከፍለው ደም እና አጥንት እንዳለው ተናግረዋል። የማኅበሩ ፕሬዝዳንት በመግለጫቸው እንዳነሱት ሠራዊቱ በሚመደብባቸው ቦታዎች በወታደራዊ ሳይንስ የተደገፈ ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል። ለዚህም ማኅበሩ አባላቱን በማስተባበር እና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከአገር መከላከያ ሚኒስቴር ጋር በጋራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

“መንግሥት ጥያቄያችንን መቀበሉ የወደቀን የማንሳት ያክል ደስታ ተስምቶናል” ያሉት ኃምሳ አለቃ ብርሃኑ፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት ለኢትዮጵያ ብዙ መሰዋዕትነት የከፈለ ቢሆንም፣ እንደ ጠላት ተፈርጆ መሬት ላይ የተጣለ ነበር ብለዋል። አሁን ላይ የማኅበሩ አባላት ስለ አገር እና ስለ ሕዝብ ብለው ለመንግሥት ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱ በአባላቱ ዘንድ ከፍተኛ ደስታ መፍጠሩ ተገልጿል።

የአገር መከላከያ ሚኒስቴር የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊትን ለመመልመል ባወጣው መስፈርት ያስቀመጠው የዕድሜ ገደብ፣ ሰራዊቱ የቀድሞ እንደመሆኑ መጠን ከተቀመጠው ዕድሜ ገደብ በላይ የሚሆኑ አባላት ቁጥር ቀላል የማይባል መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ማኅበሩ ከተጠቀሰው ዕድሜ በላይ የሆኑ አባላት በሌሎች ማገልገል በሚችሉባቸው የሥራ ሁኔታዎች ላይ መሳተፍ የሚችሉበትን መንገድ ለማመቻቸት ከመንግሥት ጋር እንደሚነጋገር ተጠቁሟል።


ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here