የአባይ ወንዝ ፖለቲካ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና አሜሪካ፡ ወዴት?

Views: 2599

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ውሀ አሞላል አስመልክቶ ባለፉት ዐስር ቀናት ውስጥ ለኹለተኛ ጊዜ የኢትዮጵያ፣ የግብጽ እና የሱዳን ቡድኖች በአሜሪካ ንግግር ማድረጋቸው ይታወቃል። ምንም እንኳን ስብሰባዎቹ በአጭር ጊዜ ለውጥ እየተደረጉ የመጡ ቢሆንም የሚፈለገው ስምምነት ግን በአመርቂ ሁኔታ ሊገኝ አልቻለም። አሜሪካ እና የዓለም ባንክም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሦስቱ አገሮች አደራዳሪ ሆነው ብቅ ብለዋል። ንፍታሌም ወልደሳባ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በናይል ወንዝ ዙሪያ የነበረውን ፍላጎት እና የአገሮቹን መሠረታዊ ልዩነቶች አስመልክቶ ያላቸውን ሐሳብ እንደሚከተለው አስቀምጠዋል።    

 

ቅድመ-ታሪክ

ጣሊያን እና እንግሊዝ ኢትዮጵያን ያስጨንቁ በነበረበት እና የጣና ሐይቅን የእንግሊዝ ቅኝ ለማድረግ በሙሉ ኢትዮጵያን ደግሞ ለጣሊያን አሳልፎ ለመስጠት በሚያሴሩበት እ.ኤ.አ. በ1920ዎቹ መጨረሻ ገደማ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ሚኒስትር የነበሩት ሐኪም ወርቅነህ/ዶክተር ማርቲን የአሜሪካ ኩባንያዎች በጣና ሐይቅ ላይ ግድብ እንዲሠሩ እንዲያግባቡ ወደ ኒው ዮርክ ተልከው ነበር። ሐኪም ወርቅነህም እ.ኤ.አ. በኖቬምበር 3 ቀን 1927 G. J. White Engineering Corporation የተባለው ድርጅት በጣና ሐይቅ ላይ ግድብ በራሱ ገንዘብ እንዲሠራ እና በሱዳን የጥጥ ማሳ ባለቤት ለሆነችው እንግሊዝ ውሃውን እየሸጠ ትርፍ እንዲያገኝ ስምምነት አደረጉ።

ድርጅቱም እ.ኤ.አ. በ1930 እና 1934 ሁለት የመስክ ምልከታዎችን በማድረግ በጣና ሐይቅ ላይ ስለሚሠራው ግድብ ጥናት አደረገ። በወቅቱም ግድቡን ለመሥራት ከ10 እስከ 15 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስወጣ ይፋ አደረገ። ግድቡን ለመገንባት የተጀመረው ጥረትም በወቅቱ በእንግሊዝ በተሠራ ተንኮል እና ደባ ምክንያት ወደፊት ሳይራመድ ቀረ። እንግዲህ አሜሪካ በአባይ የውሃ ፖለቲካ ላይ በይፋ መግባት የጀመረችው በዚህ ጊዜ ነበር። እንደገና ለመመለስ ግን ሩብ ክፍለ ዘመንን ወሰደባት።

ጊዜው እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ1950ዎቹ መጀመሪያ እና በ1960ዎቹ መጀመሪያ ነበር። ዓለምን በሁለት ጎራ የከፈለው የሶቭየት ህብረት እና የአሜሪካ ፍጥጫ ያየለበት እና ሳተላይት ሀገሮችም በአንደኛው ልዕለ-ኃያል ኪስ ውስጥ ለመደበቅ፣ አንድም ለገንዘብ ወይም ለርዕዮተ-ዓለም ወይም ለደህንነት፣ የሚራወጡበት እና የሚሻሙበት ጊዜ ነበር። ይህ የቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ወላፈን አፍሪካን በተለይ የአባይ ተፋሰስንም አዳርሶ ነበር።

በእርግጥ የአባይ/ናይል ታችኛውን ክፍል ከሜቄዶንያ ታላቁ እስክንድር እስከ ዐረቢያው ካሊፍ ኡመር፣ ከኦቶማን አጼዎች እስከ ናፖሊዮን ቦናፓርቲ፣ በስተመጨረሻም እስከ እንግሊዝ ድርስ እየተፈራረቁ ጎብኝተውታል፤ ወርረውታል፤ አስገብረውታል። የታላቆቹ እና ኃያላን ነን የሚሉት ሁሉ መናሐሪያ እና ጫማ መለካኪያ ሆኖ ኖሯል። በቀዝቃዝ ጦርነት ልዩ የሆነው ሁለት ባላንጣዎች የመካከለኛውን ምስራቅ ለመቆጣጠር ከነበራቸው ፍላጎት አንጻር ከፍተኛ ፉክክር ማድረጋቸው ነበር።

ነገሩ እንዲህ ነው። ግብጽ በራሷ ዜጎች የተዳደረችው በትክክል በፈርኦኖቹ ጊዜ ነበር። ከዚያ በኋላ ያለውን ጊዜ ወራሪ እና የወራሪ ቅሪት ነበር የሚያስተዳድራት። ከእነዚህ የወራሪ ቅሪቶች አንዱ የንጉስ ፉአድ ዳግማዊ አስተዳደር ነበር። የዚህ ንጉስ ቤተሰብ ከአልባኒያ የመጣው የኦቶማን አስተዳዳሪ የነበረው እና በኋላም ራሱን የግብጽ መሪ አድርጎ የሰየመው የሞሐመድ ዓሊ ቤት ነው። ምንም እንኳን እ.ኤ.አ. በ1922 ግብጽ ከእንግሊዞች ነጻ ወጣች ቢባልም ንጉስ ፉአድ ዳግማዊ ለእንግሊዝ መንግሥት ታዛዥ ከመሆን የዘለለ ሚና አልነበረውም። በመሆኑም ራሳቸውን “ነጻ መኮንኖች/free officers” ብለው የሚጠሩ የወታደሩ ክፍል አባላት እ.ኤ.አ. በ1952 ጋማል አብድል ናስር በተባለ ኮሎኔል መሪነት በሲዕረ-መንግሥት ገልብጠው ስልጣን ያዙ።

ወዲያውም ወታደሮቹ ለሕዝብ ማረጋጊያ፣ ለሥልጣናቸው ማደላደያ፣ ለስማቸው መካቢያ ሥራ ፈለጉ። አገኙም። በአስዋን ከተማ በደቡብ ግብጽም በአባይ/ናይል ወንዝ ላይ ግድብ እንገንባ ተባባሉ። እንቅስቃሴም ጀመሩ። ነገር ግን መገንቢያ ገንዘብም ሆነ እውቀት አልነበራቸውም። ወደ ውጭው ዓለምም አማተሩ። እ.ኤ.አ. በ1953 የዓለም ባንክን ገንዘብ እንዲሰጥ እና አሜሪካም እንድታግዝ ጥያቄ ቀረበ። ነገር ግን የታሰበው አልሆነም። አሜሪካ ገንዘቡን መስጠት አልፈለገችም። ጋማል አብድል ናስርም አኮረፉ። ግድቡን ለመገንባትም ገንዘብ አልለምንም ያሉት ናስር የስዊዝ ካናልን እ.ኤ.አ. በጁላይ 1956 ወረሱ። ጦርነትም ተገባ። ቀሪው ሌላ ታሪክ ነው።

የአስዋንን ግድብ ለመገንባት ግን የግብጽ እውቀት እና ገንዘብ በቂ አልነበረም። በአሜሪካ መራሹ ምዕራባውያን የተበሳጩት ናስር ፊታቸውን ወደ ምስራቅ አዞሩ። የሶቭየት ህብረትንም ድጋፍ ሻቱ። አገኙም። ሶቪየት ህብረትም በአስዋን ግድብ ግንባታ ላይ አሻራዋን አሳረፈች። እስከ 1970ዎቹ መጨረሻ የቆየው የግብጽ እና የሶቭየት ፍቅርም በዚህ ተጸነሰሰ። ግብጽም የአስዋን ግድብ በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ፖለቲካዊ ቁማር ተሳታፊነቷ ተገነባላት።

ይህን ያስተዋለችው አሜሪካም በአባይ ላይ አሻራዋን ለማኖር መንቀሳቀስ ጀመረች። ከ1956-1964 ድረስ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የጠፍ መሬት ልማት ቢሮ/United States Bureau of Reclamation-USBR በኢትዮጵያ በአባይ ሸለቆ ጥናት አደረገ። የሚሠሩ ሥራዎችንም ለየ። የኃይል ማመንጫ እና የመስኖ ቦታዎችም ተለዩ። 32 ፕሮጄክቶች ተለዩ።

ከእነዚህ ፕሮጄክቶች ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተተግብሮ የቆየው የፊንጭኣ ፕሮጄክት ብቻ ነበር። ይህ እንግዲህ የሆነው በ34ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ድዋይት ኤይዘንሐወር እና በ35ኛው ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ዘመን ነበር። በUSBR ከተለዩ ፕሮጄክቶች መካከል አንደኛው አሁን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገነባበት ቦታ ነበር። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ አንድም በአላዋቂ ፖለቲከኞቿ የውስጥ ግብግብ እና የእርስበርስ ጦርነት እና ኢኮኖሚያዊ ድቀት ሰበብ ሁለትም በግብጽ ጋሻ ጃግሬነት በተከፈተባት ተደጋጋሚ የውክልና ጦርነቶች (ከሶማሊያ እና ከኤርትራ) እንዲሁም ዓለምአቀፋዊ አሻጥር ለምሳሌ የዓለም ባንክ ብድር መከልከልን ይጨምራል ምክንያት ይህ ነው የሚባል ልማት በአባይ ላይ ሳታከናውን በርካታ ዐስርት ዓመታት አለፉ።

ድኅረ-ካምፕ ዴቪድ አሜሪካ እና የናይል ውሃ ጉዳይ

ዘመነ ጂሚ ካርተር

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1978 የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር በመካከለኛው ምስራቅ “ሰላም ለማስፈን” በሚል ግብጽ እና እስራኤልን የማስታረቅ ሥራ ጀመሩ። የነበረው የሰላም ሒደትም በሜሪላንድ ግዛት በሚገኘው እና የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች የእረፍት ጊዜም ሆነ ለሥራ ጉዳይ የጥሞና ጊዜ ማከናወኛ በሆነው እና በጫካ በተሸፈነው ተራራ በሚገኘው ካምፕ ዴቪድ ጋር የተቆራኘ ሆነ። የሰላም ስምምነቱም “የካምፕ ዴቪድ ስምምነት” በመባል ይታወቃል። በዚህ ጊዜ እንግዲህ በወቅቱ የግብጽ መሪ ለነበሩት አንዋር ሳዳት የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር ግብጽ በአባይ ላይ የበላይነቷ የተጠበቀ እንዲሆን እንደምታግዝ በሚስጢር ከሰላም ስምምነቱ አካል የሆነ የምስጢር ስምምነት እንደተገባላቸው በተደጋጋሚ ይነገራል።

ከዚሁ በተጨማሪ በግብጽ አጋፋሪነት ኢትዮጵያ በዚያድ ባሬ ሶማሊያ ለሁለተኛ ጊዜ ስትወረር የጂሚ ካርተር አስተዳደር ኢትዮጵያ ከአሜሪካ የገዛቻቸውን መሳሪያዎች በመከልከል የወረራው አጫፋሪ እና ደጋፊ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ የከፈለችው መሰዋዕትነት እንዲህ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም። የጂሚ ካርተር ሁለት ጠባሶችም አብረው ይታወሳሉ።

ድህረ-የቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት አሜሪካ እና ናይል

የቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ማክተምን ተከትሎ የሶቭዬት ሪፐብሊክ ስትበታተን አሜሪካ ብቸኛዋ ልዕለ ኃይል ሆነች። ከምዕራብ – ምስራቅ ጎራ የወጣው የዓለም ፖለቲካ ሌሎች አጀንዳዎች ላይ ተጠመደ። አዳዲስ “ስጋቶችን” ማለትም የእርበርስ ጦርነት፣ ሽብርተኝነት፣ ስደት፣ ርሐብ፣ የዴሞክራሲ እጦት ወዘተን “በመታገል” እና “ለማስተካከል” በሚል “አሜሪካ ግንባር ቀደም የዓለም ተዋናይ” ሆነች። በዚህ ጊዜ ትኩረት ከተደረገባቸው ቀጠናዎች አንዱ የአባይ ተፋሰስ ነበር።

የአባይ ወንዝ ተፋሰስ ወደ አንዳች ትብብር እንዲያመራ በሚል እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ አጋማሽ የተጀመሩ የምርምር ሥራ ውይይቶች እና የሀገራቱ “Track-II” ዲፕሎማሲ አድጎ የናይል ተፋሰስ ተነሳሽነት ወይም ጅማሮ/Nile Basin Initiative-NBI ተቋቋመ። በዚህ ጊዜ የዓለም ባንክ መሪ ተዋናይ ሆኖ መጣ። ከጀርባውም የእነ አሜሪካ ድጋፍ ነበር። ከዚሁ ጎን ለጎን ሲካሄድ የነበረውን የናይል ወንዝ አጠቃቀምን የተመለከተ የሕግ መስመር በኋላም የኢንቴቤ ስምምነት ተብሎ ለሚጠራው ውል የነበረውን ድርድር አሜሪካ ከፍተኛ ክትትል ታደርግ ነበር።

ይሁን እንጂ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2010 የአባይ ተፋሰስ አገራት የኢንቴቤ ስምምነትን በእንግሊዝኛ አጠራሩ Agreement on the Nile Basin Cooperative Framework-CFA ለመፈራረም ወሰኑ። ይሁን እንጂ ግብጽ ሱዳንን አስከትላ ዐስራ ሶስት/13 ዓመት ሙሉ የተደራደሩበትን ስምምነት በአንድ ንዑሰ-አንቀጽ (አንቀጽ 14/ለ/) ላይ ባለ አለመግባባት ብቻ ተቃወሙት።

ይህን ተከትሎ በዓለም ባንክ ዙሪያ ተሰባስበው NBIን ያግዙ የነበሩ “የልማት አጋሮች” አሜሪካኖችን ጨምሮ CFAን ለመፈራረም የወሰኑትን አገራት የሚቃወም መግለጫ አወጡ። በአጭሩ የመግለጫው ይዘት ትርጓሜ “የግብጽን በቅኝ ግዛት ዘመን እና በኋላም በአግላይ የሁለትዮሽ የግብጽ-ሱዳን ስምምነት የተገኘ ታሪካዊ መብት የማትቀበሉ ከሆነ ከNBI ጋር ተባብረን አንሠራም” የሚል ነበር። ይህ አካሄድ ከሰሐራ በታች የሚገኙትን የአፍሪካ አገራት እንደሌሉ የሚቆጥር እና ልማታቸው እና እድገታቸው እንዲሁም ከምንም በላይ በናይል ውሃቸው የመጠቀም መብታቸውን የሻረ እና ለአንዲት አገር ግብጽ አሳልፎ ለመስጠት ያለመ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነበር።

ነገር ግን የተፋሰሱ አገራት በዚህ መግለጫ ሳይደናገጡ ስምምነቱን እ.ኤ.አ. በሜይ 14 ቀን 2010 ፈረሙ። አሁንም በአገራቱ የተለያየ የመጽደቅ ደረጃ ላይ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳ ደግሞ አጽድቀውታል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና አሜሪካ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እንደተበሰረ በአሜሪካ በኩል ጉዳዩን በተለየ ሁኔታ መከታተል ተጀመረ። በተለይ በዋናነት የጉዳዩ ባለቤት ሆኖ የሚከታተለው የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት/State Department ነበር። በዚሁ መሥሪያ ቤት ስር ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶችን ጉዳይ የሚከታተሉ ግለሰብም በልዩ አስተባባሪነት/Special Coordinator ተሰይመው ጉዳዩን በንቃት ይከታተሉ ነበር።

በግብጽ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳንም ብዙ ምልልሶች እንዳደረጉ በተለይ በግብጽ እና ሱዳን ከወጡ የዜና ማሰራጫዎች ለመረዳት ይቻላል። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሦስቱ አገራት ባደረጓቸው እንቅስቃሴዎች ምን እንደተወያዩ በይፋ ከኢትዮጵያ በኩል የተባለ ነገር ባይኖርም በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ገብቶ የመፈትፈት ፍላጎት ግን እንዳልነበረ በድፍረት መናገር ይቻላል። በተለይ የቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሴክሬታሪ ሒላሪ ክሊንተን ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንደነበራቸው እና አሮን ሳልዝበርግ የተባሉ ግለሰብ ጉዳዩን በአንክሮ አንዲከታተሉ አድርገው እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በዘመነ ኦባማ የአሜሪካ መንግሥት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ጉዳዩን በአንክሮ ከመከታተል እና ገለልተኛ ሆኖ አገራቱ እንዲተባበሩ ከማበረታታት የዘለለ ሚና ነበረው ማለት አይቻልም።

 

ዘመነ ዶናልድ ትራምፕ እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ

ባራክ ኦባማ የሠሩትን ሁሉ ማፍረስ የሚቀናቸው 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ላይ የአሜሪካን ቀደም ሲል የነበረ “የገለልተኛ” አቋም እና አካሄድ እንደቀየሩ ማየት ይቻላል። በተለይ የትራምፕ አስተዳደር እ.ኤ.አ. በኦክቶበር 3 ቀን 2019 ለግብጽ ያደላ መግለጫ በማውጣት ከግብጽ ጎን መሰለፉን በገሀድ አሳይቷል። ከዚህ ሲያልፍም እ.ኤ.አ. በኖቬምበር የአሜሪካ የገንዘብ ሴክሬታሪ ስቴቨን ሙንሽን ግድቡን በተመለከተ የግብጽ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን በጽህፈት ቤታቸው ጋብዘው አነጋግረዋል። ይህን ተከትሎም የሦስቱ አገራት ሚኒስትሮች ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የተገናኙ ሲሆን በመግለጫቸውም አሜሪካ እና የዓለም ባንክ “በታዛቢነት በሦስቱ አገራት የቴክኒክ ስብሰባዎች እንዲገኙ” ሲሉ ተስማምተዋል።

ይህን ተከትሎም በአዲስ አበባ፣ በካርቱም እና ካይሮ እንዲሁም በዋሽንግተን ዲሲ በተደረጉ ስብሰባዎች “በታዛቢነት” እየተገኙ ናቸው። ስብሰባዎችም በጥድፊያ እና በችኮላ እየተደረጉ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል። ባለፉት ስምንት ዓመታት ሦስቱ አገራት ተወያይተው ያልፈቱትን ነገር በአንድ ጀምበር ስብሰባ የሚፈታ ይመስል ሩጫው በርክቷል። ጥያቄው “በሦስቱ አገራት መካከል አልፈታ ያለው ይህ ችግር ምንድን ነው?” የሚል ነው።

መሰረታዊው ልዩነት!

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል ያለው ልዩነት በተለይ በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት “ቅኝ ግዛትን ማስቀጠል ወይም አለማስቀጠል” ወይም “በናይል ውሃ የመጠቀም መብትን አሳልፎ በመስጠት እና ባለመስጠት መካከል” ያለ ነው። ግብጽ በአባይ ውሃ አለኝ የምትለውን “የብቻ ተጠቃሚነት” በማስቀጠል የቅኝ ግዛት እና አግላይ የ1959 የግብጽ-ሱዳን ውልን በኢትዮጵያ ላይ በግድቡ ውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ ሰበብ ለመጫን ሃሳብ አላት። ይህን በማድረግም ኢትዮጵያን እንደ ቅኝ ግዛቷ ለማድረግ ይዳዳታል።

ከዚሁ በተጨማሪ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ የግብጽ ግድብ እንዲሆን እና ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ጥቅም ወደ ጎን ተብሎ የግብጽ የድርቅ ጊዜ የውሃ ማጠራቀሚያ እንዲሆን ለማድረግ ያለመ ነው።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ አካሄዷ የናይል ውሃ ድንበር ተሻጋሪ እንደመሆኑ ሁሉም የተፋሰሱ አገራት በጋራ እንዲጠቀሙበት እና ኢትዮጵያም እንደ ውሃ ምንጭነቷ እና 86 በመቶ የሚሆነውን ውሃ እንደሚያበረክት አገር ሉዓላዊ እና የተፈጥሮ መብቷን በመጠቀም ለህልውናዋ መሰረት የሆነውን የናይልን/አባይን ውሃ ማልማት ነው። በመሆኑም አደገኛ የሆነውን የግብጽን ቅኝ ግዛታዊ አካሄድ አትቀበልም። በመሆኑም ግብጽ እና ሱዳን በማናለብኝነት እና አግላይ በሆነ ከዚህ ሲያልፍም በስግብግብነት ሌሎቹን የናይል ተፋሰስ አገራት ጥቅም ወደ ጎን ብለው እና መብት እንደሌላቸው ቆጥረው “ናይልን ውሃ ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም” ሲሉ እ.ኤ.አ. በ1959 የተፈራረሙትን “ውል” ወይም “ስምምነት” አትቀበልም።

እንግዲህ ፉክክሩ በኹለት ተቃራኒ ሐሳቦች መካከል ነወ። ኢትዮጵያ ፍትሐዊነት ይስፈን ስትል፣ ግብጽ ኢፍትሐዊነት ይጽና ትላለች። ኢትዮጵያ በጋራ እንጠቀም ስትል ግብጽ የለም ብቻዬን ልብላው ትላለች። በዚህ መሐል ታዲያ በዓለም ዙሪያ ለሰዎች እኩልነት እና ፍትሕ መስፈን እሠራለሁ የምትለው የወቅቱ የአሜሪካ መሪ ዶናልድ ትራምፕ እና አስተዳደራቸው የት ቆመዋል?

 

የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር መንገድ

የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከግብጽ ጋር ተሰልፏል። ለዚህ ደግሞ ልዩ ልዩ ምክንያቶች አሉት። አንደኛው ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ የናይል ተፋሰስ አገራት የናይል ጥቅም የትራምፕ አስተዳደር ለመካከለኛው ምስራቅ ሰላም ዕቅዴ ለሚለው ሃሳብ ስጦታ ወይም ጥሎሽ ወይም የመሰዋዕት በግ እያደረገ ነው። የትራምፕ አስተዳደር አሳካዋለሁ ለሚለው የመካከለኛው ምስራቅ ሰላም ሂደት እውን መሆን የግብጽ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

እናም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከአማቻቸው እና አማካሪያቸው ጃሬድ ኩሽነር ጋር በመሆን ኢትዮጵያን እየወጉ እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ሆኗል። ዓለም ባንክን በመጠቀም ኢትዮጵያን በማሳቀቅ እና በማስፈራራት እንድትንበረከክ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ ያላት የመጠቀም መብት እንዲሸራረፍ እየቴሰረባት ብቻ ሳይሆን በገሃድ ዛቻ እየደረሰባት ይገኛል።

ይህን የእነ ትራምፕ አካሄድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደቀደሙ አባቶቹ እና እናቶቹ በጽናት ሊቋቋመው እና የለም እምቢ ሊለው የሚገባ ነገር ነው። መንግሥትም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ይፋ በማድረግ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን ሆኖ በጋራ ይህን ክፉ ጊዜ መሻገር የግድ ይላል። የእነ ትራምፕ እና ጃሬድ ኩሽነር የማንጓጠጥ፣ የዛቻ እና የማስጠንቀቂያ ቱሪናፋ ከልኩ የሚያልፍ እንዳልሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያሳይ ይገባል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ የአንድ የኃይል ማመንጫ ግድብ ጉዳይ ብቻ አይደለም።

ግድቡ የዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ዶጋሊ፣ ጉንደት፣ ጉራዕ፣ አድዋ እና ካራማራ ነውና ትውልዱ ዮሐንስነትን፣ አሉላነትን፣ ምኒልክነትን፣ ጃጋማ ኬሎነትን፣ አብዲሳ አጋነትን፣ ሞሐመድ ሐንፍሬነትን፣ ዑመር ሰመተርነትን፣ አቡነ ጴጥሮስነትን፣ አርበኝነትን አንግቦ ሊነሳ ይገባል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ያላት የመጠቀም መብት ቢሸራረፍ ይህ ትውልድ ከአባቶቹ የተረከበውን አደራ በማጉደል የመጪውን ትውልድ ጥቅም አሳልፎ ከመስጠት ባሻገር መጪውን ትውልድ ባለዕዳ እና በሀፍረት የሚሸማቀቅ እና በቀደመው ትውልድም የሚያፍር ያደርገዋል። ታሪክም ይህን ይፋረዳል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com