ሴታዊነትን በዓውዱ

0
672

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

“ልዩነት ቅራኔ አይደለም። ተፈጥሯዊ ልዩነቶች ተፈጥሯዊ የሥራ ድርሻ አመላካቾች እንጂ፣ የበላይነትና የበታችነት ምልክቶች አይደሉም። ተፈጥሯዊ ልዩነትን በጸጋ ከመቀበል ውጪ የማበላለጫ ምክንያት አድርገን ካየነው ችግር ውስጥ እንገባለን። ወንድና ሴት መሆን ተፈጥሯዊ ልዩነት ነው፤ የቅራኔ ምንጭ ያልሆነ ልዩነት፤ ይልቁንስ ጎዶሎነትንና ግማሽነትን የፈጠረ ልዩነት፤ እርስ በርስ የመፈላለግን፣ እርስ በርስ መዋደድን ፣ እርስ በርስ መተሳሰብን የፈጠረ ልዩነት ነው” ፍልስፍና በብሩህ ዓለም በሚል ከተጻፈ ሥራ የተወሰደ ነው።

በተፈጥሮ ላይ ቅሬታም ሆነ አቤቱታ ሊኖረን አይችልም። ይልቅስ በተፈጥሮ ሴት ወይም ወንድ ሆነን ስንፈጠር የየራሳችን የሥራ ድርሻ ይኖረን ዘንድ ታሳቢ በማድረግ ነው። ወንድ ሆኖ ስለተፈጠረ ወንድነቱን ከሴት የመብለጫ መንገድ አደርጎ መውሰድ አግባብ አይደለም። ይልቁንም የወንድ የሥራ ድርሻውን በአግባቡ ለይቶ ማከናውን፣ ከዚያም እሱ ዘንድ የጎደለውን ሴት ጋር ለማግኘት ፍቅሩን ለሴት በማሳየት ጉድለቱን ማሟላት ግድ የለዋል። ሴቷም ሴት ሆና በመፈጠሯ ከወንድ የበታችም ሆነ የበላይ ነኝ ሳትል የሥራ ድርሻዋን በመወጣት እሷ ጋር የጎደለውን ወንዱ ጋር ለማግኘት መፈለግ ይኖርባታል።

ታዲያ በምዕራባውያን የተንሸዋረረው የጾታ እኩልነት ሐሳብ መንገዱን ስቶ ተፈጥሮ ካዋቀረችው ጾታዊ ግንኙነት ዘሎ በወንድና ሴት መካከል ውስጣዊ ቅራኔን ፈጥሯል። ጾታዊ መሳሳብ ላይ መርዛማ ግንዛቤ በመፍጠር ፍቅርን አክስሟል። በትዳር ውስጥ አስገድዶ የመድፈር ጽንሰ ሐሳብን ፈጥሯል። ሴቶች ወንድ መሆን እንችላላን አስከማለት ደርሰው ጾታን እስከማስቀየር ደርሰዋል። ሴት ከሴት፣ እንዲሁም ወንድ ከወንድ ጋብቻ እስከመፈጸምም ደርሰዋል። የፍቺ ቁጥርም በሚያስፈራ ሁኔታ ሲጨምር ይስተዋላል።

የሴታዊነት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ አስፈላጊነቱ፣ አገራችን ለኹለቱም ጾታዎች ምቹ ምህዳር እንዲፈጠር ለማድረግ ሊሆን ይገባል። ሴቶችን ማስተማር፣ በማኅበራዊ፣በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ ወሳኝ ድርሻ እንዲኖራቸው ማድረግ ተገቢ እና ለአገራችን ዕድገት አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ማሳተፍ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው። በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የሴቶች ጫና ይበረታል። ቤት ውስጥ ያለውን ሥራ መቆጣጠር ሙሉ ጊዜዋን ስለሚወስድ፣ በትምህርት ወይም በሥራ ዓለም ውጤታማነቷ ላይ አሉታዊ ተጸዕኖ ያሳድራል። ስለዚህ፣ ሴታዊነት እንቅስቃሴ ድካሟን በመቀነስ እና ውጤታማነቷን ከፍ እንዲል በማድረግ ትልቅ አስተዋጽዖ ማድረግ ይችላል። ነገር ግን፣ የምዕራባውንን እንቅስቃሴ እንደወረደ አገራችን ውስጥ እንዲተገበር ማድረግ እጅግ አደገኛ ማኅበራዊ ቀውስን ይፈጥራል። ለባህላችንና ታሪካችን የሚስማማን መንገድ በመከተል፣ ዕምነትንም በማይጣረስ መልኩ እኛው ለእኛ የሚሆን ዘዴን ያለጾታ ልዩነት በጋራ ልንቀይስ ይገባል።


ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here