ወዳጅ ሲከዳ…!

0
788

ሰው ወዳጅና ጠላቱን የሚለየው በችግሩ ጊዜ ነው ይባላል። ምርጥ ጓደኛ ወይም ወዳጅ ችግሩን አብሮ ይጋፈጣል። ጥሩ የሚባል ዓይነት ወዳጅ ችግርን አብሮ ባይጋፈጥ እንኳ <አይዞን! ከጎንህ ነኝ፤ ከአጠገብሽ አልለይም> ይላል። እንደው ወዳጅነቱ የለብ ለብ የሆነ እንደሆነ ችግር ሲገጥም አልሰማሁም አላየሁም ብሎ ይሸሻል። ሲከዳ ግን ከራሱ ጥቅም አንፃር ብቻ መዝኖ ወዳጄ ያለውን ይሸጣል።

ካለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ ሰሞኑን በማኅበራዊ የብዙኅን መገናኛ ገጾች ሲነሳ ከነበረ ጉዳይ መካከል የዛምቢያው ፕሬዝዳንት ሀካይንዴ ሂቺሌማ <ወገኖቼ ከአዲስ አበባ ነቅላችሁ ውጡ፤ ደኅንነታችሁ ያሳስበኛል> ማለታቸው ነበር። ዛምቢያ በዚህ ውሳኔ ከአሜሪካ ቀጥሎ እንዲሁም ከአፍሪካ አገራት የመጀመሪያ በመሆን ነው አምባሳደሯንና ዲፕሎማቶቿን ሳታስቀር 31 ዜጎቿን የጠራችው።

<የተሳፈሩትና ቤታቸው ያደረሳቸውኮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው> ብለው ነጥቡ እንዲያዝ ብዙዎች አመላክተዋል። ታድያ ፕሬዝዳንቱ ዜጎቻቸው ከአዲስ አበባ እንዲወጡ መወሰናቸውን ይፋ ባደረጉበት የትዊተር መልዕክታቸው ስር ተግሳፅ ሰፍሮላቸዋል። አንዳንዶችም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያላትን ዋጋ ዘንግተዋልና ግንዛቤ ማስጨበጫ የመሰለ ዘለግ ያለ ጽሑፍ አኑረውላቸዋል።

ዛምቢያ ለዜጎቿ መጨነቋ አይደለም ጥፋቱ። እንደውም ዜጎቿ የመሪያቸውን ውሳኔ <አርበኝነት> እያሉ ጠርተውታል። ነገር ግን፣ ችግርን አብሮ የማይጋፈጥ ወዳጅ ባይሆኑ እንኳ፣ የነበሩ ሐሰተኛ ዜናዎችን ተከትለው፣ የፎከረችው አሜሪካ እንኳ በቅጡ ያልተገበረችውን ዜጎችን ከኢትዮጵያ የማስወጣት ውሳኔ ስላጣደፉት ነው።

<ይህም ያልፍና እንተዛዘባለን!> ያሰኘውና ነገሩን ያባሰው ደግሞ የሠላሳው ዲናር ጉዳይ ነው። <የአስቆሮቱ ይሁዳ ጌታ እየሱስን በ30 ዲናር አሳልፎ እንደሸጠው፣ የዛምቢያውም ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ ላይ በፈጸሙት ክህደት አማካይነት በነጋታው በዩ.ኤስ.ኤይድ በኩል በሳምናታ ፓወር ፊታውራሪነት ከአሜሪካ አስተዳደር 30 ሚሊዮን ዶላር ተበርክቶላቸዋል> ሲሉ ጦማሪያን በማኅበራዊ ድረ-ገጽ ዜናውን ይፋ አደረጉ።

እውነት ነበር! ዛምቢያ <ውሳኔሽን ወደነዋል> ተብሎ በግልጽ አደባባይ አይሁን እንጂ በእጅ አዙር ሸጣ ዋጋውን ተቀብላለች። እናም የኢትዮጵያ የልብ ወዳጅ የነበሩት ፓን አፍሪካኒስቱ የዶክተር ኬኔት ካውንዳ አገር ዛምቢያ፣ የእርሳቸው መንፈስ ይታዘብሻል ሲሉ ብዙዎች እንዲወቅሷት ግድ ብላለች። የአሁኑ የዛምቢያ ፕሬዝዳንት የፈጸሙት የአስቆሮቱ ይሁዳ ተግባርንም መቼም አይረሳውም ያሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

እንግዲህ ክፉ ቀን እያስተዛዘበ ይገኛል። በእርግጥ ኢትዮጵያ በታሪኳ በተከሰቱ ጦርነቶችና ትግሎች ውስጥ ብዙ ጊዜ የዓለም መንግሥታት ሲሆን ጀርባቸውን ሰጥተዋታል፤ ሲከፋ ደግሞ የጠላቶቿ ወዳጅ ነው የሆኑት። ይህም በውስጥ ግጭቶቿም ይሁን በተደረገባት የውጪ ኃይል ወረራ ሁሉ የተስተዋለ ነው።

እንደውም፣ ይህ የውስጥ ግጭት ባይኖር ኖሮ የጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ሆኖት የቆየውን የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ከፍተው የጎረቤት ጠላት ሳያዘምቱብን አይቀሩም ነበር። ለዛም ይሆናል ለአፍታ የግድቡን ነገር ይቆየን ያሉት። ማን ያውቃል? ጊዜ እንጂ! ጊዜ የማያሳየን የለ።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here