ይልመድባችሁ!

Views: 315

ከአንድ/ኹለት ወር በፊት ጀምሮ ታገቱ የተባሉ ሴት ተማሪዎች ነገር ብዙዎቻችንን እንዳሳሰብን ግልጽ ነው። በሐሳባችን ላይ የቤተሰቦቻቸው ሐዘን እና እንባ ተጨምሮ እንደ ሰው ከሚያስበው ውጪ ፖለቲከኞችም ለየገዛ ፍላጎታቸው ግብዓትና መሣሪያ እንዳደረጉትም ይታያል። ግን እንደው ይሄ የፖለቲካ ሆነ እንጂ! የሴቶች መታገት አዲስ ነገር ነው?

አትቀየሙኝ! እንደ ሰው የሆነው በእጅጉ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነው። በእጅጉም ያሳስባል። ነገሩን ብዙዎች ትኩረት የሰጡት ግን አንድም የፖለቲካ ጉዳይ ወይም የእገታቸው ሰበብ ነገረ ፖለቲካ ስለሆነ ነው። አልፎም የብሔር ሥም በመሃል ስለተጠቀሰ ነው። ፖለቲካ`ኮ ብዙ ድራማ ይሠራል፤ ደግሞም ተመልካችም ተዋናይም በሚገባ ያገኛል፤ ይሳካለታልም¡

ግን ተመኘሁ! በማይታወቁ ‹አካላት› ሳይሆን በጥቂት ልባቸው ያበጠ ጎረምሶች ትብብር አንዲት ሴት ተጠልፋ፣ ተደፍራና ተጎሳቁላ፣ ሕይወቷ አልፎ ስትገኝ እንዲህ በጮኽን! ምንም የማታውቅ ሕጻን ከመደፈር አልፎ አሲድ ተደፍቶባት እንደማቀቀች ሕይወቷ ሲያልፍ እንዲህ እሪ ብለን ድምጻችንን ዓለም በሰማው!

እነዛ ልጆች፣ የነዛ ሴቶች ቤተሰቦች እንባ እንዲህ በየአደባባይ በታየ ኖሮ! ሐሰብ ሰቀቀናቸው በየሰዉ ልብ ገብቶ ‹እህቶቼን ጠብቁ› ብሎ ወደ ሕግና ፍትህ የሚጮኽ ቢገኝ! ምንአልባት ያ ቢሆን አሲድን በተመለከተ እንዲወጣ በሴት ማኅበራት የቀረበው የሕግ ሐሳብ በፍጥነት ይጸድቅ ከሆነ! እንደዛ በመትመም ለታገቱት ሴቶች ድምጹን ያሰማ ወገን ለዛች ትንሽ ልጅ፣ ለነዛ ምንም ሳያጠፉ ሴትነት ብቻ ድክመት ተደርጎ ለተቆጠረባቸው እልፍ ሴቶች ድምጹን አሰምቶ ቢሆን የሚለወጥ ነገር ሊኖር አይችልም ነበር?

እመኑኝ! ይህኛው ሕመም ሳይሰማኝ ቀርቶ አይደለም። ነገሩን ከሴቶች መብት ጋር ብቻ ላነጻጽረውም አይደለም። አዎን! የሴቶች መብት ሰብአዊ መብት ነው። ይህም ነውና እገታውን ‹በሴቶች ላይ የደረሰ ጥቃት› ብለን እንዳናስቀምጥ ትዝብት ላይ ሊጥለን ይችላል። ከኋላው ፖለቲካ ስላለ።

ግን እንደቀደሙ ያሉ ጥቃቶችን ይያዝልንና! እንደው ቢከሰት እንኳ ወገኔን ይልመድባችሁ ልል ፈለግሁ። ይህ ‹አህቴን መልሱ› ቤተሰባዊ ንቅናቄ ያለፍትህ አንገታቸውን እንዲደፉ ለተገደዱ ሴቶችም ይደረግላቸው። ይሄ ሥልጣንን የማግኘትና ሃምሳ ሃምሳ ወንበር የመያዝ ጉዳይ አይደለም። በየቀኑ እየታገቱ ያሉ ሴቶች፣ ጥቃት እየተፈጸመባቸው የሚገኙ ልጆች እንዳሉም ለመንገር ነው።

ለታገቱት ወጣቶች ሰዉ እንዲህ የተጨነቀው በቁጥራቸው ብዛት ነው? አይደለም። ማኅበራዊ ሚድያው፣ መደበኛ መገናኛ ብዙኀን፣ የጥበብ ሰዎች፣ ተጽእኖ ፈጣሪ የተባሉ ግለሰቦች ከአገር ውስጥ እንዲሁም ከውጪ በጉልህ ድምጻቸውን ያሰሙት ሴቶቹ ብዙ ስለሆኑ ነው? የታገተችው አንዲት ሴት ብትሆን ችላ ይሉ ነበር? በእርግጠኝነት አይሉም። ይህ የሆነው ግን የፖለቲካ ፍላጎት ስላለበት እንደሆነ እየመረረን የምንውጠው እውነት ነው።

እህቶቻችን እንዲሁም ከታጋቾች መካከል አሉ የተባሉት ወንድሞቻችንም በደኅና ቤተሰባቸውን እንዲያገኙ፣ ይሄ አሁን ያለው ጭንቀት እንዲጠፋና ወደፊትም እንዲህ ያለ ሐዘን እንዳይኖር ምኞትና ጸሎታችን ነው። ይህ እንቅስቃሴ ግን አንድ ነገር ይነግረናል። በጋራ ስንሆን ያለንን አቅም። በጋራ ለእህቶቹ መቆም የሚችል ማኅበረሰብ እንዳለን። ነገር ግን በምናውቀውም በማናውቀውም ምክንያት ዝምታን መርጦ እንደኖረ።

ሕግ ባለማክበር ብቻ ሳይሆን ሕግ ባለማከበር መንግሥትን መጠየቅ ይቻላልና፤ ይልመድብን ለእህቶቻችን እንቁም! ይልመድብን የአንድ ሰሞን ወሬ ብቻ ሆኖ እንዳያልፍ እንከታተል! ለዛሬውም መፍትሔ እስኪሰማ ድምጻችን አይቀንስ! ‹እህቶቻችንን መልሱ!›
ሊድያ ተስፋዬ

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com