የቻይናው ኮሮና ቫይረስ

Views: 382

በቻይና ‹ኮሮና› የተባለ ቫይረስ መነሳቱ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ስጋት መሆኑ ጎልቶ የተሰማው እያለቀ ባለው በዚህ ሳምንት ነው። ጉዳዩ የዓለም ሕዝብ መነጋገሪያ ከመሆኑ በላይ ስጋትም ጭምር ሆኖ ብዙዎችን ማስጨነቁ አልቀረም።

ቫይረሱን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሃ የአፍሪካ አገራት ሊቋቋሙት የሚቻል ባለመሆኑ ስጋቱ ሊጨምር እንደሚችል ግልጽ ነው። በቻይና እንኳ በጥቂት ቀናት ውስጥ በርካቶችን የሚያስተናግድ የሕክምና ማእከል መክፈት የሚያስችል አቅም ቢኖርም፤ የቫይረሱ ስርጭት ከእለት ወደ እለት እየጨመረ ሰንብቷል።

በዚህም ምክንያት የተለያዩ አገራት ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ ለጊዜው አቁመዋል። ማቆም ብቻ አይደለም፤ እንደ ጀርመን እና ቱርክ ያሉ አገራት በወታደራዊ አውሮፕላን ዜጎቻቸውን ለማስመጣት በዝግጅት ላይ እንደሆኑም ዜናዎች ተሰምተዋል። እንደ ሞንጎሊያ ያሉ አገራት ደግሞ ድንበሮቻቸውን ለመዝጋት በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸው ነው የተገለጸው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስከ ጥር 22/2012 ድረስ ወደ ቻይና መብረሩን እንደሚቀጥል አስታውቋል። ይህ ስጋት የሆነባቸው ሰዎች አልጠፉም። አንዳንዶች ደግሞ ፈገግታን ለመፍጠር፤ ‹‹ይሄ በሽታ በቶሎ የሚጠፋ ነው! ምክንያቱም የቻይና ነው›› ብለው ቀልደዋል።

በቻይና በኮሮና ቫይረስ እስከ ትላንት ጥር 22 በነበረው ዘገባ መሠረት 213 ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን ወደ 10 ሺሕ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ መያዛቸው ተነግሯል። ዓለምም ቫይረሱን እንደ ቻይና እቃዎች የማይበረክት አድርጋ አላለፈችውም። ተመራማሪዎቹም ለቫይረሱ ክትባት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሰሞኑም በኢትዮጵያ ቫይረሱ ሊኖርባቸው ይችላል ተብለው የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች ተገኝተዋል። ይህ ዜና መጀመሪያ ሲሰማ የማኅበራዊ ድረ ገጾች ሐሰተኛ ዜና ነው በሚል ቸል ተብሎ ነበር። ጤና ሚኒስቴር መግለጫ መስጠቱን ተከትሎ ግን ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቷል። የአራቱ ግለሰቦች የደም ናሙና ወደ ደቡበ አፍሪካ ተልኮ ምርመራ ተደርጓል።
ውጤቱ ሲመጣም በአራቱ ሰዎች ደም ውስጥ ቫይረሱ እንደሌለ የጤና ሚኒስቴር ያሳወቀ ሲሆን፣ ይህ ዜና እረፍት የሰጠው ለጥቂቶች አይደለም።

በአሁን ወቅት ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ከቅድመ መከላከልና መቆጣጥር ሥራ በተጨማሪ የድንገተኛ አደጋ ምላሽ ለመስጠት እየተሠራ ነው ተብሏል። ከዚህም መካከል አንዱ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚደረገው የሰውነት የሙቀት መለኪያ ልየታ ሥራ እና የለይቶ መከታተያ ክፍል ዝግጅት መደረጉ ነው።

ታድያ በዚሁ ሰሞን የቫይረሱ ምልክቶች ምን ያሉ ናቸው፣ ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎችስ ምን ምን ናቸው፣ ምልክቶች ያየ ሰው ምን ማድረግ አለበት ወዘተ የሚሉ ነጥቦች ላይ ዝርዝር መረጃ ያለው መልእክትም በማኅበራዊ ድረ ገጽ ብዙዎች የተጋሩት ነው። ከታገቱት ሴት ተማሪዎችና ከወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ጎን ለጎን፣ የቻይናው ኮሮና ቫይረስ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 65 ጥር 23 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com