የኢትዮጵያ ቡና መሸጫ ዋጋ ከባለፈው ዓመት የ58 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገለጸ

0
1926

የኢትዮጵያ ቡና መሸጫ ዋጋ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ58 በመቶ ዕድገት ማሳየቱ ተገለጸ።
ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ቡና የመሸጫ ዋጋው አንድ ኪሎ 3.3 ዶላር የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት የጥቅምት ወር የተሸጠበት ዋጋ ደግሞ ወደ 5.3 ዶላር ከፍ ማለቱ ተጠቁሟል። የመሸጫ ዋጋው ጭማሪ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የኹለት ዶላር ዕድገት አሳይቷል።

‹ዋይ ቻርት የፋይናንስ ሶፍትዌር እና መዋዕለ ንዋይ ጥናት ተቋም› ባወጣው ጥናት፣ የኢትዮጵያ ቡና (ኮፊ አረቢካ) ባለፈው የጥቅምት ወር የመሸጫ ዋጋው በኪሎ 5.3 ዶላር መድረሱን ጥናቱ አስቀምጧል።
ጥናቱ እንደሚያሳየው፣ በ2012 የአንድ ኪሎ የኢትዮጵያ ቡና የመሸጫ ዋጋ 2.8 ዶላር የነበረ ሲሆን፣ በኹለት ዓመት ውስጥ የመሸጫ ዋጋ የ2.5 ዶላር ጭማሪ አሳይቷል።

ቡናን ወደ ውጪ በመላክ ንግድ ላይ የተሰማሩት ጥበቡ አሰፋ ለአዲስ ማለደ እንደሚናገሩት፣ የኢትዮጵያ ቡና ወይንም ኮፊ አረቢካ ከተቀረው የቡና ዓይነት ማለትም ኮፊ ሮቡስታ በጣዕሙም ሆነ በቃናው የላቀ ስለሆነ የዓለም ገበያም ምርጫ እየሆነ መምጣቱን ነው።

ጥበቡ አክለውም “የኢትዮጵያ ገበሬ ከቡና ምርቱ ተጠቃሚ አየደለም፤ ለዚህም ያለደላላ እና ጣልቃ ገብነት ገበሬው ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ የሚችልበት መንገድ መከፈት መቻል አለበት” ሲሉ ሐሳባቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪ፣ ቀጥተኛ የንግድ መሠረት መጣል የሚያስችል እና የገበሬውን ቀጥተኛ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የ6 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ከሜሪላንድ ግዛት አስተዳደር ጋር በመተባበር ለመጀመር ዕቅድ ይዘው እንደመጡ ለአዲስ ማለዳ ጥበቡ አሰፋ ገልጸዋል።

ኢብራሂም አብዱል ሰመድ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ከቤተሰብ ባገኙት እርሻ ላይ ቡና እያመረቱ የሚገኙ ናቸው። ከዚህ ቀደም ከነበረው አሁን የንግድ ሥርዓቱ የተሻሻለ ቢመስልም፣ አሁንም ገበሬው የሚገባውን ሳያገኝ፣ የወጪ ንግድ ላይ የተሠማሩ ነጋዴዎችን ከገበሬው ጋር በማገናኘት ሥራ ላይ የተሠማሩ ደላሎች ይበልጥ እየተጠቀሙበት መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ተግባራዊ ያደረገው የቀጥተኛ ንግድ ጥምረት ለውጥ እያሳየ ቢሆንም፣ ትኩረት ተሰጥቶበት ቢሠራ ለገበሬው እና ከገበሬው ሰበስቦ ለዓለም ገበያ ለሚያቀርበው አካል መልካም ዕድል እንደሚፈጥር ኢብራሂም ጠቁመዋል።

ቡናን ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ከሚወስደው ጊዜ፣ ጉልበት እና ወጪ አንጻር፣ በአገር ውስጥ ገበያ በአሁኑ ሰዓት አንድ ኪሎ ቡና እስከ 280 ብር እየተሸጠ ስለሆነ፣ ለገበሬው የተሻለ ጥቅም ካልቀረበለት በስተቀር የአገር ውስጥ ገበያን እንደሚመርጥ ተናግረው፣ በዚህም ምክንያት የኮንትሮባንድ ገበያው ለውጪ ገበያ የሚቀርበውን ቡና ሊሻማ እንደሚችል ኢብራሂም ሥጋታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ከስምንት ዓመት በላይ የተቆላ ቡናን ለውጪ ገበያ በመላክ ሥራ ላይ የተሰማሩት ኢብራሂም ጥሩነህ የቡና ቆይ ሲሆኑ፣ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ቡና ተፈላጊነት የጨመረው፣ በኮፊ አረቢካ ምርት የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ የሆነችው ብራዚል በአየር ንብረት ለውጥ እና በኮቪድ 19 ምክንያት፣ ከአላት አቅሟ ከ30 በመቶ በላይ ማምረት ባለመቻሏ የተገኘ ዕድል ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

አክለውም፣ የአንድ ኪሎ የታጠበ የቡና ዋጋ 5.3 ዶላር መድረሱ፣ አንድ ኪሎ ሰፔሻሊቲ የሚባል ቡና እስከ 15 ሺሕ ብር በሚሸጥባት ዓለም ላይ ትልቅ ዋጋ አይደለም ሲሉ ለአዲስ ማለደ ኢብራሂም ገልጸዋል።
ቡና በተፈጥሮው ጥንቃቄ እና እንክብካቤን የሚፈልግ በመሆኑ ቢቻል ኹሉም የውጪ ንግድ ላይ የተሠማራ ባለሀብት የሚልከውን ቡና ወደ ስፔሻሊቲ ቡና ከፍ ማደረግ፣ ካልሆነም ቡናውን ቆልቶ ወይም ፈጭቶ ወደ ዓለም ገበያ በመላክ እስከ 21 ዶላር ማግኘት ይቻላል ተብሏል።

ባለፉት አራት ወራት የጥቅምት ወርን ጨምሮ ኢትዮጵያ 430 ሚሊዮን ዶላር ከቡና ወጪ ንግድ ያገኘች ሲሆን፣ ጀርመን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ቤልጂየም 160 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነውን ግዢ በመፈጸም ከ 1 እስከ 3 ያለውን ተርታ ሲይዙ፣ ጃፓን፣ ኮሪያ፣ ታይዋን እና አሜሪካ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይይዛሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here