የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ መቼ እንደሚደረግ እስካሁን ውሳኔ አልተሰጠበትም ተባለ

0
951

በሕዝብ እንደራሴዎች ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከተካሄደ ከአንድ ዓመት በኋላ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ቤት ቆጠራ፣ በታቀደለት ጊዜ የሚካሄድ መሆን እና አለመሆኑን የሚገልጽ ውሳኔ እስካሁን እንዳልተሰጠ አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ሕዝብና ቤት ቆጠራ ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳይ መሆኑን ተከትሎ፣ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 103 መሠረት ይህን የሚወስን፣ በዋናነት የኹሉም ክልል ፕሬዝዳንቶችን በአባልነት የያዘ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር የሚመራ፣ የአገሪቱን የሕዝብ ቁጥር የሚያጠናና ቆጠራ የሚያካሂድ ኮሚሽን ቢኖርም፣ ኮሚሽኑ እስካሁን ዘንድሮ ይካሄዳል ተብሎ ስለነበረው ሕዝብና ቤት ቆጠራ ውሳኔ እንዳላስተላለፈ ነው የተነገረው።
ሕዝብና ቤት ቆጠራ የሠላም ጊዜ ሥራ ነው፤ ለዚህም በኹሉም ቦታ ሠላም መኖር አለበት። እንደ ምርጫው በየጊዜው አይካሄድም። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ አለ፤ በዚህ ኹኔታ ውስጥ ቆጠራ ይካሄዳል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶ የሚንቀሳቀሰው በዋናነት ለጸጥታ ጉዳዮች ነው የሚል ሐሳብም ተሰንዝሯል ።

በኮሚሽኑ እስካሁን በዚህ ጊዜ ሕዝብ እና ቤት ቆጠራው ይካሄዳል ተብሎ አለመነገሩ ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊትም በጉዳዩ ላይ መቼ ውሳኔ እንደሚሰጥ አይታወቅም ሲሉ በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ውስጥ የሚሠሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ባለሙያ ተናግረዋል።

ቢሆንም ግን፣ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ኮሚሽኑ በተያዘለት ዕቅድ ዘንድሮ ይካሄድ ብሎ ውሳኔ ቢያሳልፍ፣ ዝግጅቶች ሠፊ በመሆናቸው በዚህ ዓመት ማካሄድ ከባድ እንደሚሆን ነው የተመላከተው። ምናልባትም መካሄድ አለበት ከተባለ ለቆጠራው ትልቅ ግብዓት ያላቸው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን መሠራታቸውን ባለሙያው ገልጸዋል።

በዚህም፣ በአገሪቱ ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ የካርታ ማካለል ሥራ፣ እንዲሁም የአዳዲስ ክልሎች ካርታ ሥራ ቅድሚያ የተሠሩ መሆናቸው ተመላክቷል። እነዚህ ተግባራትም የአገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ በፍጥነት የሚስተካከል ከሆነና ይካሄድ የሚል ውሳኔ ከተሰጠ ጉዳዩን ለማፋጠን ይረዳል ነው የተባለው።

ከምርጫ በፊት ሊካሄድ ለነበረው ሕዝብና ቤት ቆጠራ ተመድቦ የነበረው በጀትም ወደ ሌላ በጀት ዞሮ አግልግሎት ላይ እንደሚውል ተጠቁሟል። ለአንድ ሥራ የተመደበ የመንግሥት በጀት ኹልጊዜም ሥራው ሲታጠፍ ወደ ሌላ አገልግሎት ሊዞር ይችላል ተብሏል። በቀጣይ ለሚካሄደው ሕዝብና ቤት ቆጠራ ግን ለአዲሱ ፓርላማ በጀት ቀርቦ እንዳልተያዘለት ነው የተጠቆመው።

እንዲሁም፣ የቆጠራ ሥራውን ለማከናወን በውሰት እንዲያገለግሉ መምህራንን የተወሰነ ዙር ሥልጠና ማሠልጠን ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ የሚካሄድበት ወቅት ባለመታወቁና ከመንግሥት አቅጣጫ ባለመቀመጡ ሠልጣኞች ሥልጠናውን አቋርጠው ወደ መደበኛ ሥራቸው መመለሳቸው ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ሕዝብና ቤት ቆጠራ ከተደረገ ረዥም ጊዜ ያለፈው በመሆኑ፣ በሕዝብ ቁጥር መረጃ ላይ ተመርኩዘው ለሚሠሩ የፖሊሲ ዝግጅቶች፣ በጀት ምደባ፣ እንዲሁም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በአሁኑ ሰዓት ሕዝብና ቤት ቆጠራን የሚመለከት የዝግጅት ሥራ እየሠራ አለመሆኑ ተገልጾ፣ የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽኑ ቆጠራ የሚካሄድበተን ጊዜ ወስኖ በዚህ ጊዜ ታካሂዳላችሁ ሲል ሥራ ይጀመራል ተብሏል።

ለመጨረሻ ጊዜ በ2000 የተካሄደው የኢትዮጵያ ሕዝብና ቤት ቆጠራ፣ በዐስር ዓመት መርሃ-ግብር ሊካሄድ ከታቀደበት 2010 ወዲህ፣ ለሦስት ጊዜያት መራዘሙ ይታወቃል። ለዚህም የተከናወነው የመንግሥት አመራር ለውጥ፣ ምርጫ እና የጸጥታ ጉዳዮች እንደ መንስኤ ይቀርባሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here