የአሜሪካ ጩኸትና ኢትዮ-ቻይና ወዳጅነት

0
801

ኢትዮጵያ በገጠማት ችግር ላይ አባባሽ ኹኔታዎችን ለmፍጠር፣ መሬት ላይ ካለው በተቃራኒ ቆመው ውሸትን በማራገብ ፍላጎታቸውን ለማሳካት በሚፈልጉ አካላት በየአቅጣጫው ጫና በሚደረስባት በዚህ ወቀት፣ የሰሞኑ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ተግኝተው መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መመስከራቸውና ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸውን ማረጋጋጣቸው የሰሞኑ መነጋጋሪያ አጀንዳ ሆኗል።

ኢትዮጵያ የገጠማትን ጦርነት በራሴ መንገድ እፈታለሁ ብትልም፣ እንደ እነ አሜሪካ ያሉ አገራት ችግርሽን በራስሽ አትፈችም የሚል ሐሳባቸውን በተደጋጋሚ ከማንጸባረቃቸው በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ኹኔታ አሳሳቢ መሆኑንና የሽብር ጥቃት ይፈጻማል እስከማለት የደረስ በአገሪቱ ላይ መጥፎ ዕይታ የሚፈጥር አጀንዳ ሲያራግቡ ከርመዋል።

አሜሪካ በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ኹኔታ አሳሳቢ መሆኑን ስትገልጽ እና ዜጎቿ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ በየቀኑ ስትወተውት ወራት ተቆጥረዋል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ምንም እንኳን ጦርነት ላይ ብትሆንም፣ አሜሪካና መስል አገሮች እንደሚሉት እስከ አዲስ አበባ የደረሰ አሳሳቢ ነገር አልተፈጠረም።

ታዲያ አሜሪካ ይህንን መሰል አቋም በኢትዮጵያ ላይ በምታራምድበት እና ዜጎቿ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ በየቀኑ በምትወተውትበት በዚህ ወቅት፣ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ አዲስ አበባ ተገኝተው ከኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር መወያየታቸው የኹለቱን አገራት ግንኙነት የጎላ መሆኑን ከማሳየት ባሻገር፣ አሜሪካ በየቀኑ የምታሟርትባት አዲስ አበባ የተረጋጋች የሠላም ከተማ መሆኗን ያስመሰከረ ሆኗል።

ጉዳዩ ቻይና ለኢትዮጵያ በከፉ ቀን ከጎኗ የቆመች ወዳጅ መሆኗን ከማሳያቱ በላይ፣ የአሜሪካ የቀን ተቀን ጩኸት መሳለቂያ ሆኗል። በዚህም የኢትዮ ቻይና ጉዳይ፣ አሜሪካ ላይ ፌዝ የሚፈጥር ቀልድ እስከ መቀለድ የተደረሰበት ነው። የቻይናውን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ መገኘት እና የአሜሪካን ጉዳይ ቀልድ በሚመስል ቁምነገር ከገለጹት ሰዎች መካከል የቻይና ዓለም ዓቀፍ ጥቅሞች ተንታኝ ሽን ሺዌይ በኦፊሻል ትዊተር ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ “የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመምከር ኬኒያ ሄዱ፤ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመምከር ወደ አዲስ አበባ ሔዱ” ሲል አሜሪካን ተሳልቆባታል።

አሜሪካ “በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እየተባባሰ ነው” በማለት በየቀኑ ዜጓቿ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ትዕዛዝ በምትስጥበት ሁኔታ፣ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የአሜሪካን ጩኸት ውድቅ ያደረገ ሆኗል።

ዋንግ ይ ቻይና በኢትዮጵያ ላይ እምነት እንዳላት እና በኢትዮጵያውያንን እና በኢትዮጵያ ያሉ ቻይናውያንን የመጠበቅ ብቃት ሕዝቦቿ እንዳላቸው ገልፀዋል። ይ “አስጠንቃቂ” ባሏቸው አካላት ዜጎችን ከአዲስ አበባ አስወጡ በሚል የሚቀርብ ጥሪን ቻይና እንደማትቀበል አሳውቀዋል።
የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አዲስ አበባ በአሸባሪዎች እንደተከበበች ተደርጎ በሐሰተኛ መረጃ የሚራገበውን ወደ ጎን ትተው ከተማዋን በመጉብኘታቸው በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ መንግሥት ምስጋና ተቸሯቸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here