“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
አንዲት አፍጋኒስታን ውስጥ የምትኖር ሴት ኮቪድ በመታመሟ፣ ሕክምና ለማግኘት ወደ አቅራቢያ የሚገኝ የኮቪድ ሕክምና መስጫ ተቋም በመሄድ፣ ለ 15 ቀን ቆይታ ወደቤቷ ተመለሰች። ለባለቤቷ ሐኪም ያዘዘላትን መድኃኒት እንዲገዛላት፣ የመድኃኒት ትዕዛዙን የያዘ ወረቀት ሰጠችው። ባሏ ወረቀቱን ሲያነበው ሥሟ ተጽፎበታል። በንዴት እንዴት ለማታውቀው ሰው ሥሟን ትሰጣለች ብሎ፣ እሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ አንባረቀባት። ይህ ምናልባት ለሌሎች እንግዳ ሊሆን ይችላል፣ በአፍጋኒስታን በህል ግን ባል ብቻ ሳይሆን ሌሎች የቤተሰቧ ወንድ አባላት ጭምር፣ ሴቶች ለውጪ ሰዎች ሥማቸውን እንዳይናገሩ ያስገድዷቸዋል። ሥማቸውን ተናግረው ከተገኙ ክፉኛ ድብደባ ይደርስባቸዋል።
ይሄን ክፉ ባህል አንቀበልም ካሉት ሴቶች መሀል አንዷ ሳራህ ሳሜት ትባላለች። “ሥሜ የት አለ?” ዘመቻ ዋና መሥራች ነች። እንቅስቃሴውን በሚፈለገው ደረጃ ለማስኬድ አዳጋች ቢሆንም፣ ትግሉ ግን ግቡን እስኪመታ እንቅልፍ እንደማትተኛ ትናገራለች። እንቅስቃሴው በበርካታ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ዘንድ ከፍተኛ ንቅናቄ በመፍጠሩ ምክንያት ብዙዎች ዘመቻውን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።
ሴቶች ላይ የሚደርሰው ግፍ ጅማሮው ከተወለዱ ጊዜ አንስቶ እንደሆነ ሳራህ ሳሜት ትናገራለች። የችግሩ ምንጭ ሴት መሆንን በወጉ ካልተቀበለው ማኅበረሰብ ጋር በጽኑ የተቆራኘ ነው።ሴት ልጅ ተወልዳ ሥም እስኪወጣላት ድረስ ዓመታት ይቆጠራሉ። ስታገባ ሥሟ በፍጹም አይጠራም። የሰርግ መጥሪያ ካርዱ ላይ ሥሟ አይጠቀስም። ሐኪም ቤት ስትሄድ ለሐኪሙ ሥሟን መንገር የለባትም። በዚህ ሳያበቃ ሕይወቷ ቢያልፍ የሞት የምስክር ወረቀት ላይ ሥሟ አይሰፍርም። ሐውልት ቢሠራላትም ሥሟ አይጻፍበትም፤ ባዶ ሥም አልባ ሐውልት ብቻ።
በባህሉም ብቻ ሳይሆን በአፍጋኒስታን ሕግ መሠረት፣ የልደት የምስክር ወረቀት ላይ የሚጻፈው የአባት ሥም ብቻ ነው። የሚጠሩት በምን መልኩ ነው ታዲያ የሚለው ሲነሳ ፣ የእከሌ እህት ፣ የእከሌ ሚስት ፣ የእከሌ ልጅ፣ ወይም የእከሌ እናት ተብለው ነው። ወንዶቹም ይሄንን ባህል ተቀብለው ይኖራሉ። ባህሉንም ጠብቀውና አስጠብቀው ይገኛሉ።
ሴቶች ለአገራቸው ብሎም ለዓለም የሚያበረክቱት አዎንታዊ አስተዋጽዖ በአደባባይ የሚታይ ሐቅ ሆኖ ሳለ፣ በተለያዩ አገራት ሴት ከተፈጠረች በኋላ በዚህ ደረጃ ዕውቅና ተነፍጓት እንድትኖር ስትገደድ ይስተዋላል። በኢትዮጵያ በፖለቲካው፣ እንዲሁም በማኅበራዊው መስክ ሥማቸውን ካስመዘገቡት ውስጥ፣ ሸዋረገድ ገድሌ፣ ጣይቱ ብጡል፣ የመጀመሪያዋ ሴት አውሮፕላን አብራሪ አምሳለ ጉዋሉን ጨምሮ ሌሎች ሴት ጀግኖች የራሳቸውን አሻራ ለአገራቸው ማሳረፋቸው እሙን ነው። ታዲያ አገር የሴቶችን ተሳትፎ ሲነፍግ፣ ለዕድገት በሚደረገው እንቅስቃሴ የሴቶች እጅ ባለመኖሩ ምክንያት የአገር ዕድገት በግማሽ መቀነሱ አይቀሬ እንደሆነ ከላይ የቀረበው የድሀዋ አፍጋኒስታን ባህል ምስክር ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014


