የስድስት ወር የጨርቃጨርቅ የወጪ ንግድ የ 900 ሚሊዮን ብር ጭማሪ አሳየ

Views: 168

በ2012 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ወደ ውጪ ከተላከው የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ምርት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ903 ሚሊዮን ብር ብልጫ አሳየ።
በዘርፉ ከተሰማሩ የውጪ እና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በአጠቃላይ 99.86 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ ይህም ከእቅዱ ከ23 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ያነሰ ነው። ከዚህ ውስጥም የአገር ውስጥ ባለሀብቶች 6.55 ሚሊዮን የሚሆነውን ድርሻ ይይዛሉ።

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ምንጭ ሲታይ አገራዊ ባለሀብቶች እንዲፈጽሙት ከተያዘላቸው 6.9 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዕቅድ ውስጥ 93.79 በመቶውን በማሳካት 6.55 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያህል ፈጽመዋል። በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ተቋቁመው የሚገኙ የውጭ ባለሀብቶች በስድስት ወር ውስጥ 92.2 ሚሊዮን ዶላር ይልካሉ ተብሎ ቢጠበቅም 79.9 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ማግኘት ችለዋል። ከኢንዱስትሪ ፓርከች ውጪ ያሉ የውጪ አገር ባለሀብቶች ደግሞ 13.4 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን ምርት ልከዋል።
በአጠቃላይ በስድስት ወራት ውስጥ ከዘርፉ ከተገኘው የውጪ ምንዛሬ ገቢ ውስጥ 93 በመቶው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ካሉ አምራቾች የተገኘ ሲሆን፣ ቀሪው ሰባት በመቶ ደግሞ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች የተገኘ ነው። ለዚህም በምክንያትነት የተጠቀሰው አካባቢያዊ ገበያ ላይ በማተኮራቸዉ እና የውጭ ገበያ ላይ በትኩረት ያለመሥረታቸው እንደሆነ የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ባንቲሁን ገሰሰ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ገቢው ካለፈው ዓመት ለውጥ የማሳየቱ ምክንትም በተያዘው ዓመት አዳዲስ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ሥራ በመግባታቸው እና በዘርፉም ልምድ እየዳበረ በመምጣቱ መሆኑን ባንቲሁን ይናገራሉ። የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ሙያተኞችን በዉጭ አገራት በኹለተኛ ዲግሪ እና ክዚያ በላይ እንዲማሩ በማድረግ ከ60 በላይ ሙያተኞች ሠልጥነው ወደ ሥራ መግባታቸውንም ጠቅሰዋል።

ከዘርፉ የሚገኘው ገቢም ከዚህ በላይ እንዳይጨምር አሁንም አብዛኛው ጥሬ እቃ ከውጪ አገር የሚገባ መሆኑ ጫና ማሳደሩን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል። ኢንዱስትሪዎቹ በአብዛኛው የሠራተኛ የጉልበት ዋጋ ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸዉ የሚገኘው የተጣራ የዉጭ ንግድ ገቢ ከዚህ በላይ እንዳይሆን እንዳደረገውም ባንቲሁን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከመቶ ሺሕ በላይ የሥራ እድል ተፈጥሯል። በዘርፉ ተሰማርተዉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችም ወደ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ አሜሪካ፣ አዉሮፓ፣ ቻይና እና ወደ አፍሪካ ገበያዎች ምርታቸውን ይልካሉ።

በዘርፉ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች በስድሰት ወራት ዉስጥ 633 ስዓታት የኃይል መቆራረጥ ስላጋጠማቸው የምርት ሂደትን ከማስተጓጎል ባለፈ በማምረቻ ማሽኖች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ኢኒስቲትዩቱ አስታውቋል።

ፋብሪካዎች ከአቅም በታች እንዲያመርቱ መገደዳቸውን እና በአዳማ ኢንዱሰትሪ ፓርክ ለሰንሻይን ፋብሪካ፣ በመቀሌ ለዲቢ ኤል ፋብሪካና በኮምቦልቻ ኢንዱሰትሪ ፓርክ ለከሪቪኮ ፋብሪካ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመቅረቡ ከአቅማቸው እጅግ ባነሰ መልኩ እንዳያመርቱ ማድረጉን ኢኒስቲትዩቱ ገልጿል።

የኢትዮጽያ ኤሌክትሪክ አገልገሎት በበኩሉ የኃይል መቆራረጡ በመላው አገሪቱ ያለ ነው ይላል። ለሃይል ለመቆራረጡ ዋነኛ ምክንያት የሆነዉ የማሰራጫ መስመሮች በማርጀታቸው የኃይል ጭነት ያለመቋቋም መሆኑን የአገልግሎቱ የህዝብ ግንኙት ሃላፊ መላኩ ታዬ ተናግረዋል። ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ እና የመስመር ዝርጋታ መጀመሩንም አክለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com