መድኃኒት አጠቃቀማችን እንዴት ነው?

0
1578

‹‹አያቴ በርከት ያሉ ቁሶችን በሳንቲም ቦርሳዋ ውስጥ ትይዛለች። መርፌና ክር፣ ቁልፍ እና ሳንቲሞች ከቦርሳዋ ከማይጠፉት ነገሮች መካከል ናቸው። ከእነዚህ ኹሉ የሚገርመኝ ረዘም ላሉ ዓመታት የያዘቻቸው መድኃኒቶቿ ናቸው። ሳያልቁ በፍጥነት ትተካቸዋለች። ዋነኞቹ ‹ፓራሲታሞል› እና ‹ዳይክሎፊናክ› የሚባሉት ናቸው። አንዳንዴም ‹አሞክሳሲሊን› አታጣም።››

ይህን ያሉን በጳውሎስ ሆሰፒታል ከዐስር ዓመት በላይ በጤና መኮንንነት ያገለገሉት ሰውነት በየነ ናቸው። ሰውነት ይህን በቅርብ የሚያውቁትን እውነት መነሻ አድርገው የመድኃኒት አወሳሰድንና በማኅበረሰባችን ያለውን ኹናቴ በሚመለከት ከአዲስ ማለዳ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገዋል።

በአገራችን በ‹ልምድ ዕውቀት›፣ እንዲሁም ከግንዛቤ ዕጥረትና የሐኪም ትዕዛዝን በአግባብ ካለመከተል የተነሳ የሚስተዋሉ የመድኃኒት አወሳሰድ ክፍተቶች ይታያሉ። ሰውነት እንደሚሉት በእርግጥ ያለሐኪም ትዕዛዝ ሊወሰዱ የሚችሉ መድኃኒቶች አሉ። እነዚህ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ሊሰጡ የሚችሉ (Over-the-counter Drug) መድኃኒቶች በማንኛውም መድኃኒት ቤት የሐኪም የትዕዛዝ ወረቀት ሳያስፈልግ ሰዎች በቀጥታ ገዝተው ሊጠቀሟቸው የሚችሉ ናቸው።

ከእነዚህ መካከል የሕመም ማስታገሻ፣ የተለያዩ ዓይነት ቫይታሚኖች፣ የወሊድ መከላከያዎች፣ የሳል ሽሮፖች፣ ወዘተ. የመሳሰሉት ይገኛሉ። ታዲያ እነዚህም ቢሆኑ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ነው ሰውነት የሚናገሩት። ስለዚህም ያለትዕዛዝ ሊወሰዱ የሚችሉ መድኃኒቶችን የሚጠቀሙ ሰዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

መድኃኒቶችና አወሳሰዳቸው?
‹‹መድኃኒቶች በተረጋገጠ የሕክምና ባለሙያ ብቻ ይታዘዛሉ። እንዲሁም በመድኃኒት ቤት ለደንበኞች በሚቀርቡበት ጊዜ የመድኃኒት ቤት ባለሙያ ተገቢ የሆነ ማብራሪያ የመስጠት ግዴታ አለባት/በት›› ይላሉ-ምሥራቅ አበበ። ምሥራቅ ለበርካታ ዓመታት በመድኃኒት ቤት (Pharmacy) ባለሙያነት ሠርተዋል። አሁን ላይ በቤተ ዛታ ሆሰፒታል የፋርማሲ ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

ምሥራቅ በሥራ ቆይታቸው እንዲሁም በዙሪያቸው ከሚታዘቡት በመነሳት ሲናገሩ፣ አብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል መድኃኒቶችን ለራሱ የማዘዝ፣ ብሎም ለአንዱ ታዞ በጎ ምላሽ የነበረውን መድኃኒት ለሌላው የመጠቀም የተሳሳተ ልምድ አለ ይላሉ። ምናልባትም ለዚህ ልምድ መበራከት የመድኃኒት ቤት ባለሙያዎችም የራሳቸው የሚባል አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ነው የተናገሩት።

‹‹አንዳንድ መድኃኒቶች ያለ ሐኪም ማዘዣ ይሰጣሉ። እንደምሳሌም ቀላል የሚባሉ የሕመም ማስታገሻዎች እንደ ፓራሲታሞል እና ዳይክሎፊናክን ያጠቃልላል። ነገር ግን፣ መድኃኒት ቤቶች በተደጋጋሚ ለግለሰቦች ከሕመም ማስታገሻዎች በተጨማሪም ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ‹አንቲ-ባዮቲክስ› ሲሸጡ ይታያል። ድርጊታቸው ከሙያዊ ሥነ-ምግባርም ሆነ ከሕግ አንጻር ስህተት ነው›› ሲሉ ምሥራቅ ያስረዳሉ።

ከዚህ ጋር አያይዘው ይሠሩበት በነበረ መድኃኒት ቤት የተከሰተ አንድ ገጠመኛቸውን አውስተዋል። ይህም ሐኪም የሰጠውን የመድኃኒት ትዕዛዝና አወሳሰዱን በተመለከተ የተፈጠረ ነው። የሆነው እንዲህ ነው፤ አንድ ታማሚ ወደ ሕክምና ማዕከል ሔደው በሐኪሙ ‹ሰፖዚተሪ› (በፊንጢጣ የሚወሰድ መድኃኒት) ይታዘዝላቸዋል። እርሳቸውም የሐኪሙን ትዕዛዝ ይዘው ምሥራቅ ወደሚሠሩበት መድኃኒት ቤት ያቀናሉ። በዛም ምሥራቅ መድኃኒቱ እንዴት መወሰድ እንዳለበት ለታካሚው ያስረዳሉ። ታካሚውም ‹በሚገባ ገብቶኛል› ብለው አመስግነው ይሄዳሉ።

ይህ በሆነ በሦስተኛው ቀን ታካሚው ምሥራቅ ወደሚሠሩበት የመድኃኒት ቤት ይመለሳሉ። ‹‹መድኃኒቱ ወደ ሰውነቴ ውስጥ አልገባም፤ ጤናዬም ምንም ለውጥ ሊያሳይ አልቻለም›› በማለት ይናገራሉ። ምሥራቅ ይሄኔ ጥርጣሬ ገብቷቸው ‹‹እንዴት ነው መድኃኒቱን እየወሰዱ ያሉት?›› በማለት ታካሚውን ይጠይቃሉ። ታካሚውም መድኃኒቱን በፊንጢጣ ሳይሆን በአፍንጫቸው ለመውሰድ ሲሞክሩ እንደነበር ያስረዳሉ።

‹‹እንደዚህ ዓይነት የተባሉትን በአግባቡ ባለመስማታቸው ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎች ብዙዎች ናቸው። ማንኛውም መድኃኒት ከመወሰዱ በፊት በሕክምና ባለሙያ የሚመከር መሆኑ መረጋገጥ፣ አወሳሰዱንም በሚገባ መረዳት መሠረታዊ ጉዳይ መሆን አለበት›› ሲሉ ነው ምሥራቅ አስተማሪ ይሆናል ያሉትን ገጠመኝ በማንሳት የመከሩት።

የጎንዮሽ ጉዳቶች
ያለትዕዛዝ የሚወሰዱ ብቻ ሳይሆን በድምሩ መድኃኒቶች በሚወሰዱበት ጊዜ ኹለት ውጤቶች ይኖራቸዋል። የመጀመሪያው የታሰበው በጎ የሆነውና የሚፈለገው ውጤት ሲሆን፣ ኹለተኛው የጎንዮሽ ጉዳቱ ነው። የጤና መኮንኑ ሰውነት በየነ ኹሉም መድኃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳቶች አሏቸው ይላሉ። ነገር ግን የሚያሳድሩት ተጽዕኖ በዕድሜ፣ በሰውነት የመቋቋም ኹናቴ፣ እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ሊባባስ ወይም ቀላል ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።

‹‹አብዛኞቹ [የጎንዮሽ ጉዳቶች] ጊዜያዊ ናቸው። ረዘም ላለ ጊዜ ከቀጠሉ ግን ሐኪም ማማከር ይገባል። የጎንዮሽ ጉዳቱ ታይቶ በሐኪም ትዕዛዝ መሠረት የሚወሰደው የመድኃኒት መጠን ሊቀነስ ወይም ሊቀየር ይችላል›› ብለዋል።

ቀላል ከሚባሉት የጎንዮሽ ጉዳቶች መካከል ትውከት፣ የድካም ስሜት፣ ራስ ምታት፣ ተቅማጥ እንዲሁም ቆዳን ማሳከክና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። አንዳንድ መድኃኒቶች ደግሞ እስከ ሞት ሊያደርሱ የሚችሉ ከባድ የሆኑ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ፤ እንደ ሰውነት ገለጻ።

መድኃኒቶችና ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች
ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ባለሙያዎች ማንኛውንም ዓይነት መድኃኒት በመውሰድ ጊዜ ሊደረጉ ይገባሉ ያሏቸውን ጥንቃቄዎች አንስተው አሳስበዋል። ይህም ከመድኃኒት አቀማመጥ የሚጀምር ነው። ባለሙያዎቹ እንዳሉት መድኃኒቶች የራሳቸው የሆነ የአቀማመጥ ሥርዓት እንዲኖራቸው ይጠበቃል። ምክንያቱ ደግሞ ከአቀማመጥ ስህተት የተነሳ መድኃኒቶች ሊሰጡ የሚገባቸው ጥቅም ሊቀንስ ወይም ጨርሶ ሊታጣ ይችላልና ነው። አልፎም መድኃኒቶቹ ወደ ጎጂነት ሊቀየሩም ይችላሉ።

ለምሳሌ መድኃኒቶች ለፀሐይ ብርሃን ሲጋለጡ ወይም ከፍተኛ የሆነ ሙቀት ባለበት ቦታ ሲቀመጡ ባህሪያቸውን ይቀይራሉ። ስለዚህም ኹሉም መድኃኒቶች በማሸጊያቸው ላይ የአቀማመጥ መመሪያ በመኖሩ ያንን መከተል፣ አልያም የመድኃኒት ቤት ባለሙያን መጠየቅና ማማከር ተገቢ ነው። የመድኃኒት ቤት ባለሙያዎችም ይህን ጉዳይ ለተጠቃሚ እንዲያስረዱ ያሻል።

ከዚህ በተጓዳኝ በተለምዶ ለሕመም ማስታገሻነት ተብለው የሚወሰዱ መድኃኒቶች መጠንና ድግግሞሽ በበዛ ቁጥር ተያያዥ ጉዳትና ኩላሊትን ጨምሮ በተለያየ አካል ክፍል ላይ ጫና ሊፈጠር ይችላል። ስለዚህም መድኃኒቶች ተወስደው የሚጠበቀው ለውጥ ካልታየ ሐኪምን ማማከር ተገቢ ነው።

ታድያ ያለሐኪም ትዕዛዝ የሚወሰዱ መድኃኒቶች አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ የማስፈለጉን ያህል፣ ሐኪም ያዘዛቸው መድኃኒቶች አወሳሰድ ላይም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ነው ባለሙያዎቹ የሚናገሩት። ብዙ ጊዜ ግን በዚህም ላይ ክፍተቶች በብዛት ይስተዋላሉ። መድኃቶችን ማቋረጥ፣ በተገቢው ሰዓት አለመውሰድ፣ መድኃኒቱ የሚፈልገውን ያህል በቂ ፈሳሽ አለመጠቀም ከሚታዩ ክፍተቶች መካከል ናቸው።

ከጉዳዩ ሳንርቅ፣ ከእርግዝና ጋር በተገናኘ ነፍሰ ጡር የሆኑ ሴቶች ብዙ መድኃኒት እንዲወስዱ አይመከርም። በተያያዘም መድኃኒቶች ለሕፃናት በሚሰጡ ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የግድ ይላል። ከኹሉም ቀዳሚው መድኃኒቶችን ሕፃናት ከማይደርሱበት ቦታ ማስቀመጥ ሲሆን፣ በተያያዘ ለሕፃናት መድኃኒት በሚያስፈልግ ጊዜ በሐኪም ትዕዛዝ መሠረት ለሕፃናት የሚሆኑ መድኃኒቶችን ብቻ መጠቀም፤ የአጠቃቀም መመሪያዎችን በሚገባ ከመድኃኒት ቤት ባለሙያ መረዳት፤ ጊዜ ያለፈባቸውን መድኃኒቶች በፍጹም አለመጠቀም ይመከራል።

የዓለም የ‹አንቲባዮቲክ› ግንዛቤ ሳምንት
የተለያዩ ጥናቶችም እንደሚያመላክቱት መድኃኒቶች ያለ ሐኪም ትዕዛዝና በብዛት በሚወሰዱ ጊዜ፣ ከላይ ከተነሱ ነጥቦች ባሻገር ከሰውነት ጋር የመላመድ ጠባይ ያመጣሉ። ይህም በሽታን ያስከተሉ ተዋኅስያን መድኃኒትን መቋቋም እንዲችሉ ሲያደርጋቸው፣ በአንጻሩ መድኃኒቱ ለታማሚው ውጤታማ የመሆን ዕድሉን ይቀንሳል።

የዓለም የጤና ድርጅት ታድያ በየዓመቱ ኅዳር ወር መጨረሻ ላይ ‹የዓለም የአንቲባዮቲክ ግንዛቤ ሳምንት› በሚል ይህን ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችለውን ሰሞን አስቦ ያሳልፋል። ይህ በየዓመቱ የሚከበር ግንዛቤ መፍጠሪያ ሳምንት መከበር የጀመረው ከስድስት ዓመት ገደማ በፊት በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2015 ነው።

የድርጅቱ ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው ዘገባ እንደሚያስረዳው፣ በወቅቱ በሰውነት ውስጥ ተገኝተው ሕመም የሚያስከትሉ ተዋኅስያን ‹አንቲባዮቲክ› የሚባሉ መድኃኒቶችን የመቋቋማቸው መጠን እየጨመረ መምጣቱ እጅግ አሳሳቢ መሆኑ የታወቀበት ነበር። እናም ይህን የሰውነት መድኃኒትን መላመድ ወይም የተዋኅስያን መድኃኒትን የመቋቋም አቅም ለመቀነስ የሚያስችል ግንዛቤን ለመፍጠር በሚል ነው በየዓመቱ ኅዳር ወር ማጠናቀቂያ ላይ የ‹አንቲባዮቲክ› ሳምንት መከበር የጀመረው።

በዛው በዘገባው ላይ ታድያ ጠቃሚ የሚባሉ ነጥቦችን ያጋራ ሲሆን፣ በተለይም የሰውነት መድኃኒትን መቋቋም ጉዳዩ ዓለም አቀፋዊ መሆኑን ያስረዳል። ከዚህም በተጓዳኝ ጉዳዮ አንድም የተፈጥሮ ሒደት ውጤት መሆኑን ያስረዳል። ይህንንም ሲተነትን፣ መድኃኒት የሚወሰድባቸው ጥቃቅን ተዋኅስያን መካከል ደካማዎቹ በመድኃኒቱ ምክንያት መወገድ ሲችሉ የበረቱት እንደሚቆዩ ይጠቁማል። እናም እነዚህ የበረቱት የሚወሰድባቸውን መድኃኒት የመቋቋም ኃይልን በማዳበር ዝርያቸው የተሻለ የመቋቋም አቅም እንዲኖረው ያስችሉታል።

ከዚህም ባለፈ ከላይ እንደተነሳው በመድኃኒት አጠቃቀም ችግርና ስህተት የተነሳ ይህ የሰውነት መድኃኒትን መላመድ ይፈጠራል። እናም መድኃኒት መውሰድ ያለባቸው ሰዎች የመድኃኒቱን አጠቃቀም በሚመለከት ሐኪም እንዲያማክሩ ይመክራል። በተያያዘም የመድኃኒቶች የጥራት ድክመትም ከዚህ አውድ የሚመደብ ነው። ድርጅቱ እንዳለው ከሆነ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመድኃኒት ጥራት ቁጥጥር ጉዳይ እየቀነሰ ነው። በዚህም የተነሳ የሚወሰዱ መድኃኒቶች የታለመውን ውጤት ባላመጡ ቁጥር መድኃኒቶች ከሰውነት ጋር የመላመድና ተዋኅስያንም የመቋቋም አቅማቸውን እየጨመሩ እንዲሄዱ እንደሚያደርጋቸው ያስረዳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here