የታኅሳስ ወር የቡና ወጪ ንግድ ቅናሽ ተመዝግቦበታል

Views: 246

በታኅሳስ ወር ወደ ውጪ አገራት የተላከው የቡና መጠን ቢጨምርም የተሰበሰበው ገንዘብ መጠን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ4 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ማሳየቱ ተገለፀ።
ባሳለፍነው ወር ቡናን ወደ ውጪ አገራት በመላክ 14 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት መቻሉ የተገለፀ ሲሆን፣ የወሩ የቡና የወጪ ንግድ መጠን ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በገቢ ቅናሽ ሲመዘገብበት በመጠን ጭማሪ አሳይቷል።

በ 2012 የታኅሳስ ወር 16 ሺሕ ቶን ቡና በመላክ 57 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ 14 ሺሕ 187 ቶን ቡና ወደ ውጪ አገራት ተልኮ 33 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የቡናና ሻይ ልማት ግብይት ባለሥልጣን አስታውቋል።

ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወር ከተላከው ጋር ሲነጻጸር በመጠን 1 ሺሕ 195.66 ቶን ጭማሪ ቢኖረውም፣ በገቢ ግን የ4 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ተመዝግቦበታል።
በዚህ ጊዜ ውስጥም 130 ሺሕ ቶን ቡና በመላክ 457 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ 133 ሺሕ ቶን ቡና በመላክ 365 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተላከው ጋር ሲነጻጸር በመጠን 30 ሺሕ ቶን በገቢ ደግሞ 30 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ተመዝግቧል።

የኢትዮጵያን ቡና ለዓለም አቀፍ ገበያ ማስተዋወቅን ዓላማው ያደረገ ኤግዚቢሽን እና ኮንፍረንስ በሚሊኒየም አዳራሽ ከጥር 28 የጀመረ ሲሆን እስከ ጥር 30/2012 ይዘልቃል ተብሏል። በኮንፈርንሱም የገበያ ማፈላለጊያ መድረኮች እንደሚኖሩ የተገለፀ ሲሆን፣ ኮንፍረንሱ በኢትዮጵያ ሲደረግ ለኹለተኛ ጊዜ ነው።

በሚሊኒየም አዳራሽም ከ 200 በላይ ዓለም ዐቀፍ የቡና ገዢዎች መገኘታቸው ተገልጿል። 400 በቡና ንግድ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች እና 56 ቡና አምራች እና አብቃይ ማኅበራት እና ምኁራንም እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በኤግዚቢሺኑም የገበያ ማፈላለጊያ መድረኮች እንደሚኖሩ የሚጠበቅ ሲሆን፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ቡና ዓለማቀፋዊ መለያ የሆነ ምልክት ተዘጋጅቶ ለእይታ እንደሚቀርብ ተነግሯል።
ምርት ገበያ ወደ ውጪ አገራት ከሚልካቸው የግብርና ውጤቶች መካከል 48 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍነው የቡና ምርት መሆኑም በኤግዚቢሽኑ ላይ ተጠቅሷል። የቡና ዓለማቀፋዊ ዋጋ በዓለም ዐቀፉ የገበያ ዋጋ መወሰኑ ኢትዮጵያ እንደ አምራች አገር የገበያ ዋጋውን መወሰን አለመቻሏ፣ ምርቱን ለዓለም አቀፍ ገበያ በስፋት ባለማስተዋወቋ እንዲሁም የራሱ የሆነ መለያ ምልክት ባለመኖሩ ነው ተብሏል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነ የቡና ፓርክ ለመገንባት የመሰረተ ድንጋይ እንደሚቀመጥ ይጠበቃል።

የቡና ሻይ እና ቅመማ ቅመም ምርት ደግሞ በስድስት ወራት 141 ሺሕ ቶን ምርት በመላክ 468 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ፣ 135 ሺሕ ቶን የቡና ሻይ እና ቅመማ ቅመም ምርት ወደ ውጪ አገራት መላክ ተችሏል። ከዚህም 372 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት መቻሉን ባለሥልጣኑ አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com