በምሥራቅ ወለጋ አንገር ጉትን ከተማ 400 ኩንታል እህል በኦነግ ሸኔ ተወርሷል ተባለ

0
1793

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን፣ ሊሙ ወረዳ አንገር ጉትን ከተማ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ኦነግ ሸኔ ተፈናቃዮች ለቀለብ ብለው ሲያጓጉዙት የነበረውን 400 ኩንታል እህል መቀማቱን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ያገኘቸው መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ፣ ባሳለፍነው ታኅሳስ 11/2014 አንገር ጉትን መንደር ስድስት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች፣ ለቀለብ የሚሆን እህላቸውን ጭነው ሠላም ወዳለበት የጉትን ከተማ ሲያጓጉዙ የሸኔ ታጣቂ ቡድን እንደቀማቸው ነው መረዳት የተቻለው።

የሸኔ ታጣቂ ቡድን አካባቢውን ለቋል ብለው በማሰብ፣ የነበረውን ክፍተት ተጠቅመው ለቀለብ የሚሆን እህል ከመንደር ስድስት ጭነው ሊያሸሹ ሲሉ፣ ቡድኑ ከየት እንደመጣ ሳይታወቅ “አራግፉ” ብሎ እህሉን እንደወረሳቸው ነው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።
60 በሚሆኑ የበቅሎ ጋሪዎች ተጭኖ በመጓጓዝ ላይ የነበረው 400 ኩንታል የተፈናቃዮች እህል፣ ‹‹አሮየ ከተማ›› ሲደርስ እንደተወረሰ የጥቃቱ ሠለባ የሆኑት ሰዎች ገልጸዋል።

ከቅሬታ አቅራቢ ምንጮች መካከል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ግለሰብ፣ ተፈናቃዮች እንደመሆናችን መጠን ዕርዳታ ሊደረግልን ሲገባ፣ ከአካባቢያችን ጭነን ለቀለብ እያሸሸነው የነበረውን 400 ኩንታል እህል የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ወስደውብናል ሲሉ ገልጸዋል።
ግለሰቡ አክለውም፣ እህሉን ካራገፉ በኋላ ወደ ጉተን ከተማ መጋዝን አስገብተውታል ያሉ ሲሆን፣ ቤታችንን መልቀቃችን በቂ ሆኖ ሳለ፣ ለምግብ ፍጆታ ይሆነናል ያልነውንም ተቀማን። መንግሥት ግን የት ነው ያለው? ሲሉ ጠይቀዋል።

አያይዘውም፣ ድረሱልን ብለን መጮህ ከጀመርን ከዓመት በላይ ቢሆነንም፣ እስካሁን (ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ) ድረስ ታጣቂ ቡድኑ መግደልና መዝረፍ አላቆመም። ወደ ሌላ አካባቢ ለመውጣት ያሰቡ ብዙ ዜጎችም ሲታገቱና በግፍ ሲገደሉ ኑረዋል ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

በተመሳሳይ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠቀሱ የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ ታጣቂ ቡድኑ እህሉን ከተፈናቃዮቹ የቀማቸው “ሠርቃችሁ ነው ያመጣችሁት” በሚል ሠበብ መሆኑን አመላክተዋል።
በተያያዘም፣ ከዚህ በፊትም ሕይወታቸውን ለማትረፍ ቤታቸውን ለቀው ወጥተው የነበሩ ሰዎች ታጣቂ ቡድኑ የሚሠነዝረው ጥቃት ቀነስ ባደረገበት ክፍተት ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው ለቀለብ የሚሆን እህል ጭነው ሲመለሱ የተቀሙ መኖራቸውን ነው አስተያየት ሰጭው ያነሱት።

አያይዘውም፣ ከኹለት ሳምንታት በፊት 200 ኩንታል እህል በጋሪ ጭነው የሚጓጓዙ ሰዎች እህላቸውን ተዘርፈዋል የሚሉት ግለሰቡ፣ እህሉን ጭነው የነበሩ ከ30 በላይ ሰዎችና 30 በቅሎዎች ጭምር በሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ታግተው ተወስደዋል በማለት ይገልጻሉ።
በተጨማሪም አስተያየት ሰጭዎቹ፣ በዚሁ በአንገር ጉትን እህል ከመዘረፉ በፊት ታጣቂ ቡድኑ ኹለት ሰዎችን እንደገደለ ያመላከቱ ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪ ንብረት እስካሁን ከመዘረፍ ሊታደገው የሚችል አካል ማግኘት አልቻልንም ብለዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ከቤታችን እንዳንቀመጥ ግድያ እየተፈጸመብን ነው። ሠላም ወዳለባቸው አካባቢዎች ለመሄድ ስንሞክርም መንገድ ማግኘት አልቻልንም። ከዚህም በተጨማሪ ንብረታችንን እንኳ ለምግብ የመጠቀም ነጻነት ተነፍጎን ርሃብ ተጋርጦብናል ነው ያሉት።
አያይዘውም፣ አሁንም ቢሆን ተስፋ ባለመቁረጥ የመንግሥትን መፍትሔ እየተጠባበቅን ነውና የመንግሥትን አፋጣኝ ዕርዳታ እንሻለን ሲሉ አሳስበዋል።

አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ የደረሳት መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ፣ ‹‹አንዶዴ›› በተባለው አካባቢ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል በንጹኃን ሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸም ጀምሮ በመከላከያ አጋዥነት ሊቆም መቻሉን ነው።
አዲስ ማለዳ ስለ ጉዳዩ ምላሽ ለማግኘት ወደ ዞኑ ፖሊስ አዛዥ ኮማንድር ታሪኩ ግርባባ ስልክ ብትደውልም ስልክ ሊያነሱ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ሐሳባቸውን ማካተት አልቻለችም።
አዲስ ማለዳ ባሳለፍነው ኅዳር 24/2014 በዚሁ ወረዳ 19 ንጹኃን ዜጎች መገደላቸውንና 20 የቀን ሠራተኞች መታገታቸውን መዘገቧ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here