የኢትዮጵያ ትምህርት ሥርዓተ ለውጥ እና የዘርፉ ተግዳሮት

0
2509

የኢትዮጵያ ትምህርት ዘርፍ ከሥርዓት እስከ አፈጻጸሙ ድረስ ከፍተቶች እንዳሉበት የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በዘረፍ የሚታየው የሥርዓት እና የአፈጻጸም ክፍተት ኢትዮጵያ አሁን ለገጠማት ችግር የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝም ብዙዎች ይስማማሉ። በዋናነት በዘርፉ የሚታየው ችግር የትምህርት ሥርዓቱን ለታለመለት ዓላማ በአግባቡ ከመጠቀም ይልቅ፣ ሥርዓቱ በአፈጻጸም ረገድ የፖለቲካ መጠቀሚያ ወይም የፖለቲካ ጥገኛ መሆኑ እንደሆነ በዘርፉ ባለሙያዎች ጭምር ማረጋገጣቸውን ይገልጻሉ።
በትምህርት ሥርዓቱ በኩል የሚታየውን ችግር ይቀርፋል ተብሎ የታሰበው የትምህርት እና ሥልጠኛ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ትግባር ገብቷል። በዚሁ መሠረት ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች አዲስ የትምህርት ሥርዓተ-ትምህርት አዘጋጅተው የሙከራ ትግበራ ጀምረዋል።
የትምህርት ዘርፉ ከዚህ ቀደም በነበረው ሥርዓት የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑን ተከትሎ ሥብራት እንዳጋጠመው የሚገልጹት የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ዘርፉን ካለበት ችግር ለማውጣት ትምህርት ለሙያተኞች መተው እና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አሠራር መከተል እንደሚገባ ይጠቁማሉ።

የትምህርት ዘርፉ ከነበረበት የፖለቲካ ጥገኝነት በአግባቡ ሳይላቀቅ፣ በኮቪድ-19 እና በሰሜን የኢትዮጵያ ጦርነት ሌላ ተግዳሮት ገጥሞታል። በኮቪድ-19 የተዛባው የትምህርት ዘመን በአግባቡ ሳይስተካከል በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በአማራ እና አፋር ክልሎች እስከ አምስት ሽሕ የሚደርሱ የትምህርት ተቋማት በህወሓት ታጣቂዎች ወድመዋል። በዘርፉ የተጀመረውን የማሻሻያ ጅማሮ እና ዘርፉ የገጠመውን ተግዳሮት የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ የትምህርት ባለሙዎችን አነጋግሮ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕስ ጉዳይ አድርጎታል።

ትምህርት በዓለም ላይ ለሚታዩ ለውጦች ጉልህ ሚና የሚጫወት፣ ለዕድገትና ለለውጥ ቀዳሚ መሠረት ነው። ትምህርትን በአግባቡ የተጠቀሙ እና ውጤታማ የትምህርት ሥርዓት የተከተሉ የዓለም አገራት በተለያዩ ዘርፎች ቀዳሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።
የትምህርት ዓላማ ዕውቀትን ማስጨበጥ እና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ኹለንተናዊ ዕድገት ለማምጣት የሚጠቅም የዕውቀት ሽግግር ማድረግ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ። በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ባለሙያዎቹ ሲገልጹ ይደመጣሉ።
የዘርፉ ባለሙዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ እንደሚደመጡት ከሆነ፣ በኢትዮጵያ የትምህርት ዘረፍ ችግር፣ በተለይ የደርግን መንግሥት መውደቅ ተከትሎ ወደ ሥልጣን በመጣው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር(ኢሕአዲግ) የአገዛዝ ዘመን የተስፋፋ ነው። በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ ካመጣው ውጤት ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል ይላሉ።

በኢሕአዲግ የመንግሥትነት ዘመን የትምህርት ዘርፍ የትምህርት ዓላማን ከማሳካት ይልቅ ያስከተለው ጉዳት እንደሚያመዝን የሚገልጹም አሉ። የትምህርት ዘርፉ ዓላማውን እንዲስት አድርገዋል ተብለው ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል፣ ኢሕአዲግ ትምህርትን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ መጠቀሙ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ዘርፉ የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑን ተከተሎ ከዋና ዓላማው በማፈንገጡ፣ በኢትዮጵያ የትምህርት ዋጋ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ኹሉን አቀፍ ዕድገት ማምጣት ሳይችል ቀርቷል የሚል ትችት ይበዛበታል።

በወቅቱ የነበረው የትምህርት ሥርዓት በአግባቡ ተግባራዊ አለመደረጉን ተከትሎ፣ የትምህርት ሥርዓቱ በአፈጻጸሙ የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑ ይነገራል። በዚህም በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ተቋማት ለተማሪዎች የሚሠጡት ትምህርት፣ በተለይም በዩኒቨርስቲዎች የሚቀነቀነው አስተሳሰብ የብሔር ፖለቲካ በትምህርቱ ማኅበረሰብ ላይ እንዲጎለብት ማድረጉን የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።

የትምህርት ዘርፉ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነትና መሣሪያነት ነጻ መሆን እንዳለበት የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይመክራሉ። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፉ የፖለቲካ ጥገኛ ከመሆን አልዳነም። በትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለው ማኅበረሰብ መቅሰም ያለበትን ተገቢ ዕውቀት አግኝቶ መውጣት ሲገባው፣ በትምህርት ተቋማት ቆይታው የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኝ ሆኖ የሚወጣት ሁኔታ ተፈጥሯል። ለዚህም ላለፉት አራትና አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተከሰተው የነበሩ የጸጥታ ችግሮችን መመልከት እንደ አንድ ማስረጃ ይወሰዳል።

የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚመጡ ተማሪዎችን የሚያስተናግዱ እንደመሆናቸው መጠን፣ ብዝኅነትን ማስተናገድ አልቻሉም። ለዚህም ዋናው ማሳያ በትምህርት ተቋማት ሲከሰቱ የነበሩት የጸጥታ ችግሮች ብሔርን ወይም/እና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነትን መሠረት አድርገው የተከሰቱ መሆናቸው ነው።

የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት አፈጻጸም የፖለቲካ ሥርዓት ማስፈጸሚያ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ለትምህርት ጥራት የሚሠጠው ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ ዋጋ እየወረደ መምጣቱ ይገለጻል። የትምህርት ጥራት ዋጋ እየቀነሰ መምጣቱን አጉልተው ከሚያሳዩ ማስረጃዎች መካከል ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በሕገ-ወጥ መንገድ እያሠሩ ወደ ሥራው ዓለም ለመቀላቀል የሚሞክሩ ሰዎች መበራከታቸው አንዱ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ በተለይ ከህወሓት(ኢሕአዲግ) ከሥልጣን መወገድ በኋላ፣ ቀድሞ የነበረውን የትምህርት ዘርፍ ችግር ያስቀራል የተባለ የትምህርት ማሻሻያ ባለፉት ኹለትና ሦስት ዓመታት ሲደረግ ቆይቷል። በዚህም የትምህርት እና የሥልጠና ፍኖተ ካርታ ከማዘጋጀት ጀምሮ አዳዲስ አሠራሮችን እስከማስተዋወቅ የደረሰ ሲሆን፣ የተደረገው ማሻሻያ አሁን ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል።

የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ ካርታው በኢትዮጵያ ለ20 ዓመት ሲሠራበት የቆየውን የትምህርት ሥርዓት ፖሊሲ የቀየረ ሲሆን፣ የተሻሻለው የትምህርት ሥርዓት የመማር ማስተማሩን የጥራት ደረጃ ለማሻሻል፣ እንዲሁም ሙያዊ ግዴታውን በብቃት የሚወጣ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የትምህርት ማኅበረሰብ መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ትምህርት ሚኒስትር በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።

ከዚህ በፊት ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው የኢትዮጵያ ትምህርት ሥርዓት፣ ከአገር በቀል ዕሴቶች እና ዕውቀቶች ይልቅ ለምዕራባውያን አመለካከት እና ፍልሥፍና ትኩረት ሠጥቶ መቆየቱ፣ ኢትዮጵያ በቂ የተማረ እና ለውጥ የሚያመጣ ትውልድን በመቅረጽ ረገድ ያደረገችውን ጥረት በእጅጉ እንደጎዳው የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቅሳሉ።

በኢትዮጵያ አሁን ላይ ለሚታየው ችግር የትምህርት ዘርፉ ብልሽት አስተዋጽዖ ማድረጉን ብዙዎች ይስማማሉ። ይህንኑ ሐሳብ የሚያጠናክር መረጃ በቅርቡ የሠነዘሩት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር)፣ በኢትዮጵያ የተከሰተው የእርስ በእርስ ጦርነት የትምህርት ጥራትና የሞራል ውድቀት የፈጠረው መሆኑን ገልጸው፣ ችግሩን ለመፍታት የትምህርት ጥራት ላይ ሊሠራ እንደሚገባ መጠቆማቸው የሚታወስ ነው።

በአዲሱ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ ዐዋጅ ቁጥር 1263/2014 መሠረት፣ እንደ አዲስ በተቋቋሙት 22 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲከስም በማድረግ በትምህርት ሚኒስቴር ሥር እንዲካተት ተደርጓል። በዚህም መስከረም 24 በተደረገው አዲስ የመንግሥት አመራር ለውጥ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ሮ) የትምህረት ዘርፉን ለውጥ እየመሩ ይገኛሉ።
አዲሱ የትምህርት ሚኒስትርም የትምህርት ሥርዓቱን ለማሻሻል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኃላፊዎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ መጀመራቸውም ተሰምቷል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ የምትከተለው የትምህርት ሥርዓት ያለበትን ደረጃ የሚያሳይ ውይይት በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች እያተከናወነ ሲሆን፣ እስካሁን በአራት መድረኮች ላይ ውይይት መደረጉ ተጠቁሟል።

የትምህርት ሥርዓቱ ምን መምሰል እንዳለበት ከ47 የመንግሥት እና የግል ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች ጋር ውይይት መካሄዱን የትምህርት ሚኒስትሩ በጉዳዩ ላይ ከሰመራ ዩኒቨርስቲ ጋር በመከሩበት ወቅት መግለጻቸው፣ ከሰመራ ዩኒቨርስቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የአጠቃላይ ትምህርት ማሻሻያዎች
በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ግብረ ገብነት፣ አገር በቀል ዕውቀት፣ ሙያና የቀለም ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርትና ተግባር፣ ጥናትና ምርምር ትኩረት የተደረገባቸው ጉዳዮች ሲሆኑ፣ ቅደመ አንደኛ ደረጃ፣ አንደኛ ደረጃ፣ መካከለኛ ደረጃና ኹለተኛ ደረጃ ተከፋፍሏል።
በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ማሻሻያ ተደርጎባቸው ተግባረዊ እየተደረጉ ከሚገኙ መሻሻያዎች መካከል፣ ከ1-6ኛ ክፍል ላሉ ደረጃዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት እንዲሰጥ፣ ከ7-12ኛ ክፍል ኹሉም ተማሪ በእንግሊዘኛ ቋንቋ እንዲማር፣ እና ከ1-12ኛ ክፍል ድረስ እንግሊዘኛ ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንዲሠጥ የሚሉት ይገኙበታል።

በቀድመው የትምህርት ሥርዓት 10ኛ ክፍል ይሰጥ የነበረው አገራዊ የመልቀቂያ ፈተና እንዲቀር የተደረገ ሲሆን፣ አጠቃላይ ፈተና በክልል ደረጃ 6ኛ ክፍል፣ እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ላይ ይሰጣል።
ከዚህ ቀደም ሦስት ዓመት የነበረው የተማሪዎች የዩኒሸርስቲ ቆይታ ዝቅተኛዉ አራት ዓመት እንዲሆን ተደረገ ሲሆን፣ ለኹሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች በመጀመሪያ ዓመት ከሚሠጡ ትምህርቶች ውስጥ እንደ ጂኦግራፊ፣ አንትሮፖሎጂ፣ ሶሺዮሎጂና ሥነ-ምግባር የመሳሰሉት ተካተዋል።

በኢትዮጵያ ቀደምት የትምህርት ሥርዓት በንጉሳዊያን ዘመን ይሰጥ የነበረው የግብረ ገብ ትምህርት መቅረቱ፣ በትምህርት ማኅበረሰቡ ውስጥ ሥነ ምግባርና ሰብዕና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠፋ እንዲሄድ ጉልህ ሚና እንደተጫወተ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥርዓተ ትምህርት መምህር እና በትምህርት አስተዳደር ጥናት ያደረጉ ምሁር ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጠቁመዋል። ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው የትምህርት ሥርዓት የግብረ ገብ ትምህርት መካተቱ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ብዙዎች ይገልጻሉ።

በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሠረት፣ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች አዲስ የማስተማሪያ መጽሐፍና ‹ሞጁል› በማዘጋጀት የሙከራ ተግባር መጀመራቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። አዲስ የትምህርት መጽሐፍና የማስተማሪያ ሞጁል አዘጋጅተው ሙከራ ከጀመሩት መካከል አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ አማራና ደቡብ ክልል፣ እንዲሁም ሌሎች ይገኙበታል።

አዲስ ማለዳ የከተማ አስተዳደሮች እና ክልሎች ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት አዲስ የትምህርት ሥርዓትን እንዴት አገኛችሁት ስትል መምህራንን ጠይቃለች። በአዲስ አበባ ከተማ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው አዲስ የማስተማሪያ ሞጁል ከዚህ ቀደም መምህራን ከሚያስተምሩበት መጽሐፍ የተለየ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው መምህራን ተናግረዋል።

የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ ካርታን ካዘጋጁት ምሁራን መካከል አንዱ የሆኑትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥርዓተ ትምህርት መምህሩ ጥሩሰው ተፈራ(ፕ/ር) ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ የፖለቲካ ጥገኛ መሆኑን ተከትሎ ሥብራት ውስጥ መቆየቱን ያነሳሉ።

ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት፣ የትምህርት ዘርፉ በፖለቲካ ተጽዖኖ ሥር መውደቁን ተከትሎ የትምህርት ተቋማት ሲመሩ የነበሩት በካድሬ ነበር ብለዋል። በዚህም የትምህርቱ ዘርፍ የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆኑን ተከትሎ ዋና ግቡን ሳያሳካ በሥብራት ውስጥ መቆየቱን ጠቁመዋል።
ጥሩሰው በተሳተፉበት የትምህርት እና የሥልጠና ፍኖተ ካርታ ላይ በዘርፉ ለበርካታ ዓመታት ያካበቱት ልምድ ያካፈሉ ሲሆን፣ አሁንም የትምህርት ዘርፉ በሙያተኞች መመራት እንዳለበት ጠቁመዋል። ዘርፉ የመንግሥት ተጽዖኖ የሚበዛበት ቢሆንም፣ በሒደት ከፖለቲካ ጥገኝነት ነጻ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የትምህርት ሥርዓት የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ፣ ከመምህራን እስከ ትምህርት ተቋማት ኃላፊዎች ድረስ ያሉ ሙያተኞች የአገር ፍቅር ወኔ ኖሯቸው ተግባራዊ ሊያደርጉት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ የትምህርት ሥርዓቱ ከፖለቲካ አስተሳሰብ ነጻ እንዲሆን ለማድረግ ይረዳል የተባለው የትምህርት ቋንቋ ሲሆን፣ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አንድ አገር በቀል ቋንቋ በፈቃደኝነት እንዲማሩ በፍኖተ ካርታው መካተቱን ጥሩሰው ያስታውሳሉ።

የተለያዩ አገር በቀል ቋንቋዎች ያሏቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ኹሉንም ቋንቋዎች ማካተት ባይችሉም እንኳን፣ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የተወሰኑ ቋንቋዎች ተማሪዎች እንዲማሩ ያደርጋሉ የሚሉት ጥሩሰው፣ በኢትዮጵያም አገራዊ መግባባት በሚፈጥር ኹኔታ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የቋንቋ ትምህርት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ ቋንቋዎች እንደመኖራቸው መጠን በማንኛውም አካባቢ ቢያንስ አንድ አገር አቀፍ ቋንቋ፣ አንድ የማኀብረሰብ ቋንቋ እና አንድ ኢንተርናሽናል ቋንቋ በትምህርትነት ቢሰጥ፣ አገራዊ መግባባት ከማምጣቱ በላይ፣ የትምህርት ማኅበረሰቡ በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የመሥራት እና የመግባባት ዕድል እንዲያገኝ ያደርጋል ብለዋል።

የቋንቋ ፖሊሲው፣ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ አምስት አገር በቀል ቋንቋዎች የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ሆነው እንዲያገለግሉ መጽደቁ ይታወሳል ያሉ ሲሆን፣ ኦሮሞኛ፣ ትግሪኛ፣ ሱማሊኛ እና አፋርኛ የተመረጡ ቋንቋዎች ናቸው።
ሦስት ሺሕ ዘመን ታሪክ ባላት ኢትዮጵያ የራሱ ፊደል የተቀረጸለት ግዕዝ የመንግሥት እና የቤተክህነት ቋንቋ ኾኖ ለዘመናት አገልግሏል። በኢትዮጵያ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚጠቀሙባቸው ፊደላት አገር በቀል ከሆነው ከግዕዝ ፊደል የተለየ መሆኑን እንደ ችግር የሚያነሱ ሰዎች አሉ። ይሄውም የቋንቋዎቹ ድምጸት ሳይቀየር የሚጻፉበት ፊደል የግዕዙ ቢሆን መልካም መሆኑን ይጠቀሳል።

ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የሥርዓተ ትምህርት መምህሩ፣ በኢትዮጵያ ያለው የቋንቋ ልዩነት የድምጸት ልዩነት ብቻ አለመሆኑን እንደ ምክንያት አንስተው፣ የሚጻፍበት ፊደል ወደ ግዕዙ ፊደል ይምጣ የሚል ሐሳብ የሚያንጸባርቁት፣ ቢያንስ በአንድ አገራዊ ቋንቋ በአግባቡ መግባባት እንዲቻል ካላቸው ጉጉት የተነሳ ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ አማርኛና ትግርኛ ከሚፃፉበት ከግዕዙ ፊደል ውጭ የሚጻፉ ቋንቋዎችን በአገሪቱ ብቸኛ ወደሆነው ግዕዝ ፊደል ማምጣት ቀላል አይደለም።

ለዚህም እንደ ምክንያት የነሱት እንቅፋት በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ ችግር ነው። አሁን ባለው የፖለቲካ ነባራዊ ኹኔታ፣ ጉዳዩን ከአንዳንድ ምሁራን ውጭ ፖለቲከኞችም ኾኑ መንግሥት ይህንን ነገር መንካት አይፈልጉም ይላሉ። ምክንያቱም ቋንቋቸውን በሌላ ፊደል የሚጠቀሙ ሰዎች በግዕዝ ፊደል ተጠቀሙ ቢባሉ፣ ቋንቋቸውን የተቀሙ ያህል ስለሚመስላቸው ነው ይላሉ።

የትምህርት ዘርፉ እክሎች
የኢትዮጵያ ትምህርት ዘርፍ ባለበት ሥብራት ላይ ሌላ ተግዳሮት ከገጠመው ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥሯል። ዘርፉ የገጠመው ችግር የመጀመሪያው ኮቪድ-19 ያስከተለው የትምህርት ዘመን መስተጓጎል ሲሆን፣ ከኮቪድ-19 ተጽዖኖ ሳያገግም ትምህርትን የሚስተጓጉልና የትምህርት ተቋማትን የሚያወድም ጦርነት መከሰቱ ሌላ ተጨማሪ ትኩሳት ነው።

ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ መከሠቱን ተከትሎ የተስተጓጎለው የትምህርት ዘመን በአግባቡ ሳይስተካከል፣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተው ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መስፋፋቱን ተከትሎ በርካታ የትምህርት ተቋማት በህወሓት ታጣቂዎች ወድመዋል።

በአማራ ክልል ብቻ ከአራት ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች መውደማቸው የተገለጸ ሲሆን፣ 1.9 ሚሊዮን ሕፃናት እና ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል ተብሏል። በክልሉ የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና ሥራ ለማስጀመር ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈለግም ተገልጿል።

በአፋር ክልል በህወሓት ታጣቂዎች የወደሙ የትምህርት ተቋማት 455 በላይ መሆናቸው ከሳምንታት በፊት መገለጹ የሚታወስ ነው።
የትምህርት ዘርፉ በዚህ ጦርነት ክፉኛ መጎዳቱን የሚገልጹት ጥሩሰው ተፋራ(ፕ/ር)፣ የትምህርት ዘርፉ ኹሉንም የማኅበረሰብ ክፍል የሚነካ መሆኑን ጠቁመዋል። በአፋር እና በአማራ ክልሎች በህወሓት የወደሙ የትምህርት ተቋማትን በተቻለ ፍጥነት መልሶ መገንባት እና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ መመለስ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የትምህርት ተቋማቱን መልሶ ከመገንባት ባሻገር፣ በጦርቱ ጉዳት ያስተናገደውን የማኅበረሰብ ክፍል፣ ተማሪዎችንና መምህራን በማወያየት ከደረሰባቸወ የሥነ-ልቦና ችግር እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። በጦርነቱ በተጎዱ አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎችንና መምህራንን የሚያግዙ የጤናና የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች፣ እንዲሁም በሥነ ልቦና የጠነከሩ መምህራን እንደሚያስፈልጉ ፕሮፌሰሩ ጠቁመዋል።

በጦርነቱ የተፈናቀሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሲመለሱ የሚኖራቸው የትምህርት አቀባበል ዝግጅትና የሥነ ልቦና ሙሉነት እንደ ቀድሞው ሊሆን ስለማይችል፣ በትብብር የተቀናጀ ሥራ መሥራት እንደሚገባ እና በኹሉም ዘርፍ ወደ ነበሩበት ኑሮ እንዲመለሱ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑም ተነግሯል።


ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here