“ከፊ ሚኒራልስ” 800 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ሀብት ከባለአክሲዎኖች ማግኘቱን አስታወቀ

0
765

ከፊ ሚኒራልስ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሚሠራቸው የፕሮጀክት ልማቶች 800 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ሀብት ከባለአክሲዎኖች ማግኘቱን አስታወቀ።

ከፊ ሚኒራልስ የተሰኘው በኢትዮጵያ ወርቅ በማውጣት የተሠማራ የእንግሊዝ ኩባንያ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሚያከናወንቸው የልማት ፕሮጀክቶች ከባለአክሲዎኖቹ 800 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ሀብት ማግኘቱን ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ ገልጿል።
ከፊ ሚኒራልስ በ2007 በኢትዮጵያ ወርቅ ለማውጣት በማዕድን ሚኒስቴር ፈቃድ የተሰጠው የእንግሊዝ ኩባንያ ሲሆን፣ ኩባንያው በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ቱሉ ካፒ በተባለ አካባቢ የወርቅ ልማት ፕሮጀክት አለው።

ኩባንያው ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ፣ ከቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት ፕሮጀክት በተጨማሪ፣ በሳዑዲ አረቢያ “ሃዋዊ ኮፐር” እና “ጎልድ ኤንድ ጂባል ቋተማን ጎልድ” የተሰኙ የወርቅ ልማት ፕሮጀክቶች አሉኝ ብሏል። ከባለክሲዎኖች የተገኘው 800 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ሀብት በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙትን ኹለት ፕሮጀክቶችና በኢትዮጵያ የሚገኘውን ‹‹ቱሉ ካፒ›› የወርቅ ልማት ፕሮጀክቶች ለማሳደግ ይውላል ተብሏል።

ኩባንያው በኢትዮጵያ የወርቅ ልማት ፕሮጀክቱን የሚያናውነት “ከፊ ሚኒራልስ ኢትዮጵያ ሊሚትድ” በተባለው እህት ድርጅቱ አማካይነት ሲሆን፣ በኦሮሚያ ክልል ለሚገኘው ለቱሉ ካፒ ጎልድ ማዕድን አክሲዮን ማኅበር 70 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ማፍሰሱ በመግለጫው ተጠቁሟል። ኩባንያው ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ለሚያከናነው የቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት ፕሮጀክት 13 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ለማፍሰስ ማቀዱን የከፊ ሚኒራልስ ኢትዮጵያ ሊሚትድ ሊቀመንበር እና የቱሉ ካፒ የወርቅ ማዕድን ምክትል ሊቀመንበር ከበደ በለጠ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ኩባንያው ለቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት ፕሮጀክት 13 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ለማፍሰስ ዕቅድ እንዳለው የገለጹት የከፊ ሚኒራልስ ኢትዮጵያ ሊምትድ ሊቀመንበሩ ሲሆኑ፣ ከፊ ጎልድ ኤንድ ኮፐር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እና ከፊ ሚኒራልስ ኢትዮጵያ ሊሚትድ በለንደን በተካሄደው የካፒታል ማሰባሰቢያ፣ የከፊ ዳይሬክተሮች እና ማኔጅመንቶች 100 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ፈሰስ (ኢንቨስት) አድርገዋል ብለዋል።

የቱሉ ካፒ ጎልድ ፕሮጀክት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ለሚኖሩ አንድ ሺሕ ለሚጠጉ ሰዎች ቀጥታ የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ በተዘዋዋሪም ከአምስት እስከ 10 ዕጥፍ ለሚሆኑ ዜጎች ሥራ ይፈጥራል ተብሎለታል።
በመግለጫው ላይ እንደተገለጸው ከሆነ፣ በቱሉ ካፒ የሚገኘው የወርቅ ክምችት ግኝት በዘመናዊ የወርቅ ፍለጋ ጥናት የተረጋገጠው የዛሬ 15 ዓመት ገደማ ነው ተብሏል።

ኩባንያው የቱሉ ካፒ የወርቅ ክምችትን ለማልማት በ2007 ላይ ፈቃድ ቢያገኝም፣ የወርቅ ልማት ሥራውን ባለመጀመሩ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባቱ የሚታወስ ነው።

ኩባንያው የወርቅ ልማት ፕሮጀክቱ በሚገኝበት በምሥራቅ ወለጋ ቱሉ ካፒ የጸጥታ ችግር መከሰቱን ተከትሎ፣ ኩባንያው የፕሮጀክት ትግበራውን በተሰጠው የጊዜ ገደብ ሳይጀምር አካባቢውን ለቆ መውጣቱን መግለጹ የሚታወስ ነው። የኩባንያው ሠራተኞች በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ታግተው የነበረ ሲሆን፣ ሠራተኞቹ ከዕገታ ቢለቀቁም፣ በአከባቢው ያለው የጸጥታ ችግር አስጊ መሆኑን መግለጹ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here