በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ደገሌ ጋቲራ ቀበሌ 11 ሰዎች መገደላቸው ተሠማ

0
1376

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ አካባቢ በምትገኘው ደገሌ ጋቲራ ቀበሌ፣ ልዩ ቦታዋ ወዴሳ በተሰኘችው ቦታ 11 አርሶ አደሮች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ በተፈረጀው ኦነግ ሸኔ መገደላቸውን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንዳመላከቱት ከሆነ፣ ግድያው የተፈጸመው ባሳለፍነው ታኅሳስ 11/2014 መሆኑን ነው መረዳት የተቻለው።

ከአዲስ ማለዳ ምንጮች መካካል ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈቀደችው ወጣት፣ ግድያው የተፈጸመው በአርሶ አደሮች ላይ ብቻ ሳይሆን በሕጻናት ልጆቻቸውም ጭምር ላይ ነው ስትል ምስክርነቷን ሰጥታለች፡
የአዲስ ማለዳ ምንጭ እንደምትለው፣ ታጣቂ ቡድኑ በንጹኃን ላይ ጥቃት ያደረሰው ብሔርንና ማንነትን መሠረት አድርጎ ነው።

ወጣቷ አያይዛም፣ አርሶ አደሮቹና ልጆቻቸው በታጣቂዎቹ ግድያ የተፈጸመባቸው ‹‹የአማራ ክልል ተወላጅ ናችሁ›› በሚል ማንነትን መሰረት ያደረገ ምክንያት መሆኑን ነው ያስረዳችው።

ግድያው ከምሽቱ ስድስት ሰዓት ገደማ የተፈጸመ መሆኑን የአዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ሰምታለች። የጋዜጣዋ ምንጮች እንዳመላከቱት ከሆነ፣ ግድያው ከመፈጸሙ አንድ ሳምንት በፊት ከ40 በላይ የሚሆኑ ታጣቂዎች አርሶ አደሮቹን ከቤታቸው አስወጥተው ትዕዛዝ ሰጥተዋቸው እንደነበር ነው።

ትዕዛዙም ‹‹መሣሪያ አላችሁ፤ ስለዚህ ለኛ ታስረክቡናላችሁ። ካልሆነ ግን ተመልሰን መጥተን እንገድላኋለን›› የሚል እንደነበር ነው የአዲስ ማለዳ ምንጮች ያመላከቱት።

ከታጣቂዎቹ ይህ ጥያቄ የቀረበላቸው አርሶ አደሮችም መሣሪያ እንደሌላቸው ለማስረዳት እንደሞከሩ የተመላከተ ሲሆን፣ ታጣቂዎቹም መሣሪያ ከሌላችሁ እያንዳንዳችሁ 200 ሺሕ ብር ሰብስባችሁ ጠብቁን፤ ይህን ካላደረጋችሁ ግን ከሳምንት በኋላ ስንመለስ ‹‹እንገድላችኋለን›› ሲሉ አስፈራርተዋቸው ነበር ነው የተባለው።

በታጣቂ ቡድኑ ከተገደሉት ሰዎች መካከል ሰባቱ አርሶ አደሮች እንደሆኑና ቀሪዎቹ አራቱ ሟቾች ደግሞ የአርሶ አደሮቹ ታዳጊ ልጆች መሆናቸውን ነው መረዳት የተቻለው። ከሟቾች መካከል አምሳል አለማየሁ፣መስፍን መኮነን፣ ታረቀኝ አለማዬሁ፣ ወንዳፈራሁ በቀለ፣ ስንቴ ደረሰ፣ ወርቁ አለምነው እና ዘለቀ ሙላው በሥም የተጠቀሱ ናቸው።

ከአባቶቻቸው ጋር የተረሸኑት አራቱ ልጆች ደግሞ አየነው ወርቁ የተባለው የወርቁ አለምነው ልጅ፣ ብዙአየሁ ታረቀኝና ሀብተወልድ ታረቀኝ የተባሉት የታረቀኝ አለማየሁ ልጆች፣ እንዱሁም በአምላኩ ዘለቀ የተባለው የዘለቀ አለሙ ልጅ ናቸው።
የመረጃ ምንጮች እንሚሉት ከሆነ እነዚህ 11 ንጹኃን ዜጎች ግድያው የተሠነዘረባቸው ባሳለፍነው ጥቅምት 11/2014 ከምሽቱ ስድስት ሰዓት ሲሆን፣ የተገደሉትም ወደ ጫካ ታፍነው ተወስደው ነው።

የሟቾቹ ቤተሰቦችም የደረሠባቸውን ለወረዳው አስተዳደር ቢያሳስቡም ‹‹ካቅማችን በላይ ስለሆነ ከፈለጋችሁ እናስታጥቃችሁና ተከላከሉ›› የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ነው መረዳት የተቻለው።

ታጣቂ ቡድኑ ጥቃቱን የፈጸመው አርሶ አደሮቹን መሣሪያ አምጡ ሲላቸው የለንም ብለው ለማስረዳት ሲሞክሩ በቀጣይ ስንመጣ እያንዳንዳች 200 ሺሕ ብር ይዛችሁ ካልጠበቃሁን እንገድላችኋለን ባሉት ዛቻ መሠረት መሆኑ ተመላክቷል።
በመሆኑም የሟቾች የቀብር ሥነ-ስርዓት ባሳለፍነው ታኅሳስ 12/2014 በአምቦ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል ነው የተባለው።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ከኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ እና ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም።


ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here