ቀን የተቆረጠለት አገር አቀፍ ምርጫ ዝግጅት እጅ ከምን

Views: 1223

በኢትዮጵያ ታሪክ ከመደበኛ ምርጫነት በዘለለ አዲስ ዴሞክራሲ በር ይከፍታል ተብሎ በብዙዎች በጉገት በመጠበቅ ላይ ያለው የ2012 አገር አቀፍ ምርጫ የመጨረሻው ቀን ተቆርጦለታል። ቦርዱ የካቲት 6/2012 በስካይ ላይት ሆቴል በመቶዎች የሚቆጠሩ የምርጫው ባለድርሻ አካላትን በመሰብሰብ፣ በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው ላይ ከቀረበው የ13 ቀን ልዩነት በማድረግ የመጨረሻውን የጊዜ ሰሌዳ ይፋ አድርጓል።

በዚህም መሰረት የምርጫ ቀኑን ነሐሴ 23 ያደረገው ቦርዱ፣ ጳጉሜ ሦስት ቀን የተረጋገጠ ውጤት ይፋ ለማድረግ የጊዜ ሰሌዳውን አሰናድቷል። ለውጡ የምርጫ ክልል ካርታ መጋቢት ይፋ የሚያደርግ ሲሆን፣ ነገር ግን አዲስ የምርጫ ክልል አያደራጅም። የመራጮች ምዝገባ ከኹለት ወር በኋላ ሚያዚያ 14 ተጀምሮ ግንቦት 13 ቀን እንደሚጠናቀቅም ይፋ አድርጓል። ግንቦት አምስት የእጩ ምዝገባ ተጀምሮ እስከ ግንቦት 19 ይቆያል። ሌላው ዋናው የምርጫው ክፍል የሆነው የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻ ግንቦት 21 ተጀምሮ እስከ ነሐሴ 18/2012 የሚቆይ ይሆናል።

ሎጂስቲክ
ቦርዱ ለምርጫው የሚያስፈለጉ ቁሳቁሶችን አዘጋጅቶ ማጠናቀቁን ገልፆ፣ ምርጫውን ለማጭበርበር በሮችን ለመዝጋት ይረዳል ያለውን ተግባራት ማከናወኑን አስታውቋል።

ከውጪ አገርም ሆነ ከአገር ውስጥ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስፈለጉ ዋና ዋና ግብአቶችን ጨርሶ መጋዘን ማስቀመጡን በቪዲዮ አስደግፎ አሳይቷል። ቦርዱ ከዚህ ውስጥም የመራጮችን የምዝገባ ካርድ እንደ አዲስ መዘጋጀቱን፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ገልፀዋል።

ምርጫ ከሚጭበረበርባቸው ሂደቶች መካከልም አንድ ሰው ብዙ የምርጫ ካርድ በመያዝ የሚያካሂደው ሲሆን፣ ይህንን ለማስቀረትም ለመጀመሪያ ጊዜ የምስጢር ህትመት እንዲካሄድ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በራሪ እና ቀሪ የተባሉ ኹለት ክፍሎች ያሉት ይህ ካርድ፣ አንዱ መራጭ ጋር፣ ሌላው ጣቢያው ጋር ቀሪ ይሆናል። አንድ ሰው ሕገ ወጥ ካርድ ቢያዘጋጅ እንኳን ጣቢያው ጋር ቀሪ ስለማይኖር፣ ለማጭበርበር የሚኖረውን በር ይዘጋል ሲሉ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል። ካርዱ ሌላ ቦታ የማይታተም እና ምርጫ ቦርድ የሚያውቀው የማመሳከሪያ ቁጥር የያዘ ካርድ እንደሆነም ተገልጿል።

የምርጫ ቁሳቁሶችም በትግርኛ፣ በአማርኛ፣ በሶማሊኛ እና ኦሮምኛን ጨምሮ በተለያዩ ቋንቋዎች ተዘጋጅተዋል።
ሌላው ቦርዱ ለውጥ ያደረገው የጂ.አይ.ኤስ.ን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የምርጫ ጣቢያ መረጃዎችን በዲጂታል ሥነ ስርዓት የማደራጀት ሥራን ነው። ይህም እንደ ብርቱካን ገለጻ፣ ከቦርዱ ባሻገርም ለተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም የሚያግዝ ይሆናል ተብሏል። የምርጫ ጣቢዎች የት እንዳሉ፣ መራጮች የት እንደሚገኙ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚያሳይ እንደሆነም ተገልጿል። ይህ ጂ.አይ.ኤስ. ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የሚወስዱ መንገዶችን ዓይነት እና አመቺነት መዘርዘሩ በተለይም ለአካል ጉዳተኞች ጠቀሜታውን ከፍተኛ ያደርገዋል ተብሏል።

የፓርቲዎች ነባራዊ ሁኔታ
ቦርዱ በ106 ፓርቲዎች ላይ ባደረገው ማጣራት 10 የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ በየዓመቱ ጠቅላላ ጉባኤ ያካሂዳሉ። በየኹለት ዓመቱ ጠቅላላ ጉባኤ የሚያካሂዱት ፓርቲዎች ቁጥር 44 ሲሆን፣ 22ቱ ደግሞ በየሦስት ዓመቱ ብቻ ነው ጉባኤ የሚያካሂዱት። በተመሳሳይም 10 የፖለቲካ ፓርቲዎች በየአራት ዓመቱ የጠቅላላ ጉባኤአቸውን ይጠራሉ።

ሌላ በጥናት የተለየው የሴት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ቁጥር ሲሆን፣ ዐስር በመቶው ብቻ ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ናቸው። በአዲሱ አዋጅ መሰረት የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ኹለት ሲሆን፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚወዳደው ቦሮ ፓርቲ እና ብልፅግና ናቸው። ሕወሃት፣ አረና እና ትዴፓ በአዲስ አዋጅ መሰረት ለመመዝገብ ቦርዱ እንዲያሟሉ የጠየቀውን መስፈርቶች አሟልተው የቀረቡ ናቸው።

ታዲያ ከ 100 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሰሌዳው ይፋ እስከሆነበት ቀን ድረስ ያለመመዝገባቸው አሳሳቢ እንደሆነ የሚገልጹት የቀድሞው ፖለቲከኛ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር)፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጅት ማነስ የመጪው ምርጫ ዋነኛ ተግዳሮት እንደሚሆን ይናገራሉ። እነዚህ መንግሥት ለመሆን የሚወዳደሩ ፓርቲዎች በቂ ዝግጅት ከሌላቸው እንዴት መንግሥት ይሆናሉ የሚለው ጥያቄ ያሳስበኛል ሲሉም ይናገራሉ።

‹‹ሌላው የሚያሳስበኝ እነዚህ ፓርቲዎች ተመዝግበው፣ ተወዳድረው፣ ተመርጠው ምክር ቤት ውስጥ የአብላጫ ድምፅ እንዳይጠፋ እሰጋለሁ። ጥምረት ለመመሥረትም ማን እና ማን ነው የሚነጋገረው›› ሲሉ ይጠይቃሉ። ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በራሳቸው በጠላትነት ነው የሚተያዩት›› ሲሉም ያስረዳሉ።
እስከ ምርጫው ድረስ ያለው መንገድ አጭር አይደለም የሚሉት ዲማ፣ አሁንም ተሰባስቦ መነጋገር አማራጭ የለውም ባይ ናቸው። አሁን ያሉ የመሰባበሰብ ሙከራዎች ቢሳኩ ኖሮ፣ ከመቶ ባለይ ፓርቲ አይኖርም በማለት ያሉት የመጣመር ሙከራዎች ገና ብዙ ርቀት መሄድ እንዳለባቸው ይናገራሉ። አክለውም ‹‹ምርጫ ከሥሙ እንደሚታወቀው የመምረጥ እንጂ የማምታታት እድል መስጠት የለበትም። አሁንም ያሉት ፓርቲዎች ከኻያ በታች ሆነው መሰባሰብ አለባቸው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ ይሄ ምርጫ ከዚህ በፊት ከነበሩት በብዙ መልኩ የተለየ ነው። የሰብአዊ መብት ጉዳይም ለመጨው ምርጫ አስጊ መሆኑ ላይ ስምምነት ላይ መደረሱ አንድ እርምጃ ቢሆንም፣ እነዚህን ለመቀነስ ግን ምን እንሥራ የሚለው ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ይላሉ። የምርጫ ሰሌዳው መጽደቁን ተከትሎ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንም ሰትራቴጂክ እቅድ መያዙንም ጨምረው ገልፀዋል።

የመጀመሪያው በምርጫ እና በሰብአዊ መብት መካከል ያለው ግንኙነት ላይ ሰፊ ግንዛቤ ለመፍጠር ሰፊ ሥራ እንደሚሠራ ዳንኤል ተናግረዋል። የምርጫ ግጭቶችን በመፍታት የሚደርሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል ሰፊ ሥረ ይሠራ ብለዋል።

ዋናው የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ እቅድ ግን ስልታዊ ክትትል በማካሄድ ቅድመ ምርጫ፣ ምርጫ እና ድኅረ ምርጫ ሥራዎችን መሥራት መሆኑን ተናግረዋል። ይህም ምርጫን ለማካሄድ አስፈለጊ እና አንገብጋቢ የሆኑ የሰብአዊ መብቶች እና የፖለቲካ ተሳትፎ መብቶች ላይ ጫናዎች እንዳይደረጉ ኮሚሽኑ ክትትል በማድረግ ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ይደረጋል ሲሉም ጠቅሰዋል። ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ የመሰብሰብ እና የፖለቲካ ተሳትፎ መብቶችን ጨምሮ የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ሥራ ላይ አዋዋል በተመለከት፣ ጥሰት መፈፀም አለመፈፀሙን ተከታትሎ እንዲሁም ከመከሰታቸው በፊት ለመከላከል ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

እንዲሁም ዋናው የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ እና የሴቶች ተሳትፎ ላይ ሰፊ ሥራዎች ለመያዝ መታሰቡን ይናገራሉ።
አሁን ላይ የሚመጡ ቅሬታዎች መኖራቸውን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ‹አባሎቻችን፣ መሪዎቻችን እና ደጋፊዎቻችን አላግባብ ታስረውብናል ወይም ተጉላልተውብናል› የሚሉ ቅሬታዎች ከአሁኑ እየተሰሙ መሆኑን ይናገራሉ። በተለይም መንግሥት አሁን ላይ የጸጥታ እንቅስቃሴ ከሚያደርግባቸው አካበቢዎች ላይ ከሚታሰሩ ሰዎች መካከል፣ የፖለቲካ ሰዎች መኖራቸውን እናውቃለን። ይሄ ሁሉ ክትትል ይፈልጋል ብለዋል።

ኮሚሽኑ እቅዶችን ለመተግበር የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ከዚህ ቀደም ያላቸው መዋቅር ጠቃሚ መሆኑ ገልፀው፤ አሁንም የተለያዩ ጉድለቶች እንዳሉ ተናግረዋል። የስልታዊ የሰብአዊ መብት ክትትል የሚያደርግ ቡደን አሠልጥሎ በየክልሉ መላክ አልጀመርንም ብለዋል። ይህንን ለማድረግም ሥልጠናን ጨምሮ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ዳንኤል ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ከመንግሥት ለሚመጡ ወይም ገዢው ፓርቲ የመንግሥትን መዋቅር ተጠቅሞ ሰብአዊ መብቶቸን ጥሰት እንዳያደርጉ ሰፊ ውይይቶች እንዳደረጉ እና ፈቃደኝነቱ ቢኖርም ብቃቱ አለ ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል። ‹‹ያው ሆስፒታልም፣ ትምህርት ቤትም ሆነ የራሳችንን ኮሚሽን ጨምሮ፣ ያለው የአቅም ውስንነት ሰብአዊ መብቶችን ለማረጋገጥ ችግር ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የሲቪል ማኅበራት
መጪውን ምርጫ ልዩ ከሚያደርጉት ምክንቶች መካከል ከዚህ ቀደም እንደሚኖረው ዓይነት የሕዝብ ታዛቢ የማይኖር ሲሆን፣ የሲቪል ማኅበራትም ምርጫን የመታዘብ ክልከላው ከመነሳት ባሻገር ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጎን ሆነው እንዲታዘቡ እድል የሚሰጥ ነው። ይህም በ2011 በፀደቀው የሲቪል ማኅበራት አዋጅ መሰረት፣ እንደ አዲስ ማኅበራት እንዲመዘግቡ የሚጠይቅ ሲሆን፣ ምርጫ ለመታዘብም ይሁን የምርጫ ትምህርት ለመስጠት ዓላማ አድርገው ተቋቁመው ከምርጫ ቦርድም ፈቃድ ያገኙ መሆን ይገባቸዋል።

ታዲያ ከወራት በፊት የተዋቀረው የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ኅብረት ለምርጫ በሚል የተዋቀረው ጥምረት በስሩ 108 የሲቪል ማኅበራትን በመያዝ፣ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔን መታዘቡ የሚታወስ ነው። የኅብረቱ ሰብሳቢ ብሌን አስራት ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ለቀጣዩ ምርጫ መሪ ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቶ በምርጫ ላይ በምን አይነት መልኩ ነዉ የሚሳተፈዉ የሚለውን ከቅድመ ምርጫና በምርጫ ወቅት ስለሚኖሩ የመራጮች ትምህርትና መታዘብን ለማቀላጠፍ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

ከምርጫ ጣቢያዎች ብዛት አንፃርም በቂ የሰው ኃይል እንዳለ የሚናገሩት ብሌንኃ ‹‹ከፌደራል ወርደን አይደለም የምንታዘበው። ነገር ግን በየክልሉ አባላቶች አሉን። እነርሱን ማስተባባር እየተሠራ ነው። ይህንን ለማሳካትም የገንዘብ ድጋፍ እያገኘን ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የሲዳማን ሕዝበ ውሳኔ ጥምረቱ በታዘበበት ወቅት በተለያየ ዝግጅት ማነስ ችግሮች እንደነበሩ የገለጹት ብሌን፣ ስለ ምርጫ ጣቢያዎች አስፈላጊው መረጃ አለመሰብሰቡን ይናገራሉ። ‹‹የግማሽ ሰዓት መንገድ ተብሎ የግማሽ ቀን መንገድ ነበር የምንሄደው። የራሳችን የታዛቢዎች አቅም ደካማ የሆነበትን አይተናል›› ብለው በተጨማሪም የቋንቋ ችግር ሌላው ዋና ችግር እንደነበርም ጠቅሰዋል።

በመጪው ምርጫ በተለይ ቋንቋ ችግር እንዳይሆነ የየምርጫ ጣቢያውን ቋንቋ መናገር የሚችሉ ሰዎችን ለማሰማራት መታሰቡን ተናግረዋል። የሲቪል ማኅበራት ከሚዲያ ጋር አብሮ ለመሥራት ሰፊ እቅድ የያዙ ሲሆን፣ በተለይም በምርጫ ወቅት የሚተላለፉ ዘገባዎች ግጭት እንዳይቀሰቅሱ ለማገዝ ማቀዳቸውን ይናገራሉ። የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል የሚያስተናግድ የፕሪንትም ሆነ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ አንደሚጠቀሙ ብሌን ተናግረዋል።

የመጪው ምርጫ የስጋት ትንበያዎችን ከግምት ውስጥ በመክተት በተለይም የምርጫ ቅስቀሳ የቡድን ሥም በመጥቀስ የጥላቻ ንግግር እንዳይስፋፋ፣ አልፎም ምልክቶች መኖራቸውን ገልፀው፤ በተለይም ሕዝብ እና መንግሥት ላይ አተኩረው እንደሚሠሩ ነው የሚናገሩት። መንግሥት ዋናው ሥራው ሕግ ማስከበር ነው የሚሉት ብሌን፣ ፓርቲዎች የጥላቻ ንግግር ወደ ጎን ብሎ ምክንያታዊ ውይይት ማድረግ ላይ እንዲያተኩሩ እናስተምራለን ብለዋል።

ሚዲያ
የመገናኛ ብዙኀን ወይም የሚድያ ተሳትፎ ላይ በሰፊው እሠራለሁ ያለው ቦርዱ፣ ሚዲያዎች በኹለት ዙር የሚገለገሉበት የሚዲያ ማእከል እያቋቋመ መሆኑን የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ተናግረዋል። የቦታ መረጣ እንዲሁም የሚዲያ ማእከሉ የት ይሁን የሚለው ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሚደረግ ውይይት እንደሚወሰንም ገልጸዋል።

የዘመቻ ሂደት ላይ የሚነሱ ችግሮችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስርአት መዘርጋቱንም ሶልያና ጠቅሰዋል። ሚዲያዎችን የሚከታተል እና የሚቆጣጠር ስርአት መዘረጋቱን የተናገሩት አማካሪዋ፣ የቦርዱ ድረ ገጽ ጥብቅ የደኅንነት መከታተያ ተደርጎለት በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን እና ከምርጫው ጋር የተያያዙ መረጃዎችን እንደሚሰጥበትም ተናግረዋል።

ቦርዱ የመራጮች ትምህርትን የማድረስ ግዴታ ስላለበት እና የሥነ ምግባር ጥሰቶች ካሉ፣ ቦርዱ በቅርበት ይከታተላል ተብሏል። ቀሪ የሥነ ምግባር ጉዳዮች ግን የብሮድካስት ባለሥልጣን ሆኖ ይቆያል ሲሉ ሶሊያና ገልፀዋል።

ቦርዱ ይፋ ያደረገው አዲስ ሎጎ አሻራ፣ የድምፅ መስጫ ሳጥን እና የድምፅ መስጫ ወረቀትን አካትቶ እንደ አዲስ መዘጋጀቱን ሶሊያና አስታውቀዋል።
በአጠቃላይም ምርጫ ቦርድ ታማኝነት፣ ገለልተኝነት እና ግልፅነትን ከማምጣት ባሻገር ዘመናዊ አሰራርን ለመተግበር የሚያስችል ተቋም ሆኖ እንዲዋቀር ለማድረግ ታስቦ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ተናግረዋል። የምርጫ ሂደቱን እውነተኝነት የሚጠብቁ የአሰራር ብቻ ሳይሆን የቁሳቁስ ለውጥ ማድረግ ማስፈለጉንም ብርቱካን አያይዘው ያነሱት ነጥብ ነው።

ምርጫ ቦርድ እስከ አሁን ያካሄደው ተቋማዊ ማሻሻያ የሚፈተንበት ወቅት ነው ያሉት ብርቱካን፣ ይህ ግን እንደ አገር የሚደረጉ ሙከራዎችም በአጠቃላይ የሚታዩበት ነው ብለዋል።

ቦርዱ ያደረገው ማሻሻያ የቱንም ያክል የተሳካ ቢሆን አንኳን፣ ይሄ ምርጫ ዜጎች እንደሚፈልጉት መሆን አለበት ሲሉ ብርቱካን አጽንዖት ሰጥተዋል።
‹‹ይህም ዜጎች የሚፈልጉትን መንግሥት መምረጥ ብቻ ሳይሆን ከመረጡት በኋላ ባይስማማቸው እንኳን ልናወርደው እንችላለን። ያንን የሚያስፈፅምልን ተቋም እና ስርዓት አለ ብለው እንዲተማመኑ ሥራው ምርጫ ቦርድ ብቻ ሳይሆን ዛሬ በዚህ ኮንፈረንስ ላይ የተገኛችሁ ሁሉ ነው›› ብለዋል።

በኮንፈረንሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣኖች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እንዲሁም የጥበቡ ቤተሰቦች ተገኝተዋል። የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል እንዳሻው ጣሰው ከተገኙት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች መካከል ናቸው።

የፋይናንስ እና መሰል ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማት ተወካዮችም በጉባኤው ተሳትፈዋል። ከእነዚህም መካከል የአውሮፓ፣ የአሜሪካ ተቋማት ሰፊውን ድርሻ የሚይዙ ሲሆን፣ በአጠቃለይም ስድስት የምርጫ ድጋፍ ፕሮግራሞች እና 27 ተዋናዮች መኖራቸው ቦርዱ ይፋ አድርጓል። ቦርዱ ከተለያዩ አጋሮች ያገኘውን ድጋፍ በአግባቡ ለመደገፍም የተለያዩ ሥራዎች እየሠራ መሆኑ ተገልጿል።

የመንቀሳቀስ መብቶችን በተመለከተ ስጋቶች መኖራቸውን መመልከቱን የገለፀው ቦርዱ፣ እነዚህን ለማሻሻል የመንግሥት የፀጥታ ተቋማት የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 67 የካቲት 7 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com