ጁነዲን ሳዶ ሸገር የተሰኘ አዲስ ባንክ ሊመሠርቱ ነው

Views: 580

የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጁነዲን ሳዶ ‹ሸገር› የተሰኘ አዲስ ባንክ ከሌሎች አጋሮቻቸው ጋር በመሆን በማቋቋም ላይ መሆናቸውን አስታወቁ።
የባንኩ መሥራች ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ጁነዲን ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ድርሻ የመሸጥ ፈቃድ ከብሔራዊ ባንክ አግኝተው ከየካቲት ሰባት ጀምሮ በይፋ አክስዮን መሸጥ ይጀምራሉ። የባንኩ የምሥረታ አስተባባሪ ኮሚቴ በአጠቃላይ 150 ግለሰቦች ያሉበት ሲሆን፣ ከአገር ውስጥ እንዲሁም ከዳያስፖራው ሀብት በማሰባሰብ ካፒታሉን እንደሚያሟላም ጁነዲን ተናግረዋል።

ጁነዲን የቀድሞ የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራር እና የመገናኛ እና ትራንስፖርት ሚኒስትር፣ የሳይበር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ሆነው በመንግሥት የሥራ ኃላፊነቶች አገልግለዋል። የነበረው የፖለቲካ አምድ የተመቻቸ አደለም በማለት ሥልጣናቸውን በማስረከብ ወደ አሜሪካን አገር ከነ ቤተሰባቸው ኮብልልው የነበረ ሲሆን፣ ለውጡን ምክንያት በማድረግ ከአንድ ዓመት በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መምጣታቻውን ተከትሎ ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል።

የቦርዱ ሰብሳቢ ባንኩ አሁን ካሉት ባንኮች በተለይ ከአገር ውጪ ያለውን ገበያ በማጥናት ‹‹በውጪ አገር ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ባዳ የሚሆኑበትን ስርዓት የመያጠፋ ነው›› ብለዋል።

በዚህም ሎስ አንጀለስ፣ ሚኒሶታ፣ ዲሲ፣ ሂውስተን፣ አትላንታ ከአሜሪካ በቅድሚያ ሰፊ የአክሲዮን ሽያጭ የሚደረግባቸው ሲሆኑ፣ ከካናዳም ካልጋሪ እና ቶሮንቶ ከፍተኛ ተሳትፎ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚገመትም ጠቅሰዋል።

ባንኩ የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ በአግባቡ ያላሳተፈውን የገጠሩን ኅብረተሰብ እና ዲያስፖራውን በመያዝ 80 በመቶ የሆነው የገጠሩ ከፍል ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ታውቋል። በዐስር ባንኮች አክሲዮኑ እየተሸጠ ሲሆን እነዚህም ንግድ ባንክ፣ አቢሲኒያ፣ ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ፣ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል፣ አዋሽ፣ ንብ፣ ቡና፣ ወጋገን፣ አንበሳ እና ብርሃን ባንክ ናቸው።

ምሁራንን እና ባለሀብቶችን ያካተተው ይህ ባንክ፣ ይፋዊ የሽያጭ መርሃግብር ባይደረግም ከአንድ ሳምንት በፊት ሽያጭ ጀምሯል። ከዚህ በኋላም በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል በሰፊው እንደሚሸጥ ጁነዲን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መስፈርት መሰረት ኹለት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል። ከዚህ ውስጥም አንድ አራተኛውን ለመክፈል ታስቦ እየተሠራ መሆኑን የባንኩ መሥራች ኮሚቴ አስታውቋል። የአንድ አክሲዮን ዋጋ አንድ ሺሕ ብር ሲሆን፣ አንድ ሰው አስር አክሲዮኖች መግዛት ይችላል።
የባንክ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት አብዱልመናን መሃመድ እንደሚሉት ባንኮች ዲያስፖራው በፋይናንስ ዘርፍ አንዲሰማራ መፍቀዱን መልሰው ያመኑት ይመስላል። ነገር ግን ዲያስፖራው በፋይናንስ ዘርፉ ሃብቱን ሲያፈስ በውጪ ምንዛሬ ማፍሰስን ጨምሮ አዲሱ የባንክ ስራ አዋጅ ዲያስፖራው ላይ የሚያስቀምጣቸው የማያበረታቱ አንቀፆችም አሉ ይላሉ።

‹‹ባንኮቹም የሚሰበስቡትን የውጪ ምንዛሬ ለበሔራዊ ባንክ በቀጥታ መክፈል ይገባቸዋል›› ያሉት ተንታኙ ‹‹ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የኢኮኖሚ ቀውስ ዲያስፖራውንም ሆነ ሌሎች ባለሃብቶችን በኢትዮጵያ መዋእለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚጋብዝ አይደለም›› ይላሉ።
በተጨማሪም የባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለው የባንክ ቁጥር እና አሁን እየገቡ ያሉት አዳዲስ ባንኮች ብዛት ኢንዱስሪው እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ አልጋ ባልጋ አያደርገውም ሲሉም ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 67 የካቲት 7 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com