የጦርነቱ ተለዋዋጭ ኹነቶች እና የማኅበረሰቡ ሥጋት

0
1117

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተጀመረው ጦርነት ኹለተኛ ዓመቱን ከጀመረ ኹለት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ በተራዘመው ጦርነት የተለያዩ ተለዋዋጭ ኹነቶ ተከስተዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የታዩ ተለዋዋጭ የጦርነቱ ኹነቶች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው፡፡
በዚህ ጦርነት ከታዩ ተለዋዋጭ ኹነቶች መካከል ሳይጠበቅ የመከላከያ ከትግራይ ክልል መውጣት፣ የመከላከያን ከትግራይ መውጣት ተከትሎ የህወሓት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ጥቃት መክፈት፣ ህወሓት የከፈተው ጥቃት በአጭር ይቀለበሳል ተብሎ ቢታሰብም ለአምስት ወራት እስከ ሰሜን ሽዋ የደረሰ ውድመት ማስከተሉ፣ እና የህወሓት ወደ ትግራይ ማፈግፈግን ተከትሎ መከላከያ ቡድኑን ተክትሎ ወደ ትግራይ እንዳይገባ በመንግሥት መገታቱ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

የጦርነቱ እነዚህ ተለዋዋጭ ኹኔተዎች፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ መደናገር ሲፈጥሩ ይታያል፡፡ መከላከያ ወደ ትግራይ ይገባል ብለው የጠበቁ የማኅበረሰብ ክፍሎች መከላከያ በያዛቸው አካባቢዎች ጸንቶ እንዲቆይ ከሰሞኑ መወሰኑን ለምን የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ አስገድዷቸዋል፡፡
ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረውን ጦርነት ተለዋዋጭ ኹነቶች እና መከላከያ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ መታገዱን በተመለከተ የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ የፖለቲካ ሳይንስ እና ወታደራዊ ባለሙያዎችን አነጋግሮ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል፡፡

በትግራይ ክልል ጀምሮ የሰሜኑ የአማራና አፋር ክልልን ያዳረሰው ጦርነት አንደኛ ዓመቱን አጠናቆ ኹለተኛ ዓመቱን ጀምሯል። አንድ ዓመት በዘለቀው ጦርነት የተለያዩ ተለዋዋጭ ተከስተዋል። ጦርነቱ እንደተጀመረ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ የብዙዎች ፍላጎት የነበረ ቢሆንም፣ የተራዘመ ጦርነት መሆኑ አልቀረም።

ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ጦርነት እስካሁን የተለያዩ ተለዋዋጭ ኹኔታዎችን እያስተናገደ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ህወሓት መቀመጫውን መቀሌ ባደረገው የአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቅምት 24/2013 ባደረሰው ጥቃት የተጀመረው ጦርነት፣ እስካሁን ካስተናገዳቸው ተለዋዋጭ ኹኔታዎች መካከል፣ የፌዴራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ መከላከያን ከትግራይ ማስወጣቱ፣ ይህንኑ ተከትሎ ህወሓት እራሱን አደራጅቶ በአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ ጥቃት ማድረሱ፣ ከሰሞኑ መንግሥት ባደረገው የማጥቃት ወጊያ ህወሓት ወደ ትግራይ እንዲያፈገፍግ መደረጉ እና መከላከያ ወደ ትግራይ እንዳይገባ መንግሥት ውሳኔ መስጠቱ ይገኙበታል።

የጦርነቱ ተለዋዋጭ ጉዞ
በሽብርተኝነት በተፈረጀው በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) እና በፌዴራል መንግሥት መካከል በትግራይ ክልል ውስጥ የተደረገውን ጦርነት፣ መንግሥት በበላይነት ማጠናቀቁን ጦርነቱ በተጀመረ በሦስተኛው ሳምንት ማብሠሩ የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጅ በፌዴራል መንግሥት የበላይነት ተጠናቋል የተባለው ከጥቅምት 24/2013 እስከ ኅዳር አጋማሽ ድርስ የተካሄደው ውጊያ የጦርነቱ መቋጫ መሆን አልቻለም። የፌዴራል መንግሥት ህወሓትን ማሸነፉን ተከትሎ በወቅቱ በክልሉ በተደረገው ጦርነት የፈረሰውን የመንግሥት መዋቅር የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን መሥርቶ በመተካት ለስምንት ወራት በክልሉ “በሕግ ማስከበር ዘመቻ” ቆይቷል።

የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የአገር መከላከያ ሠራዊት አሰማርቶ ለስምንት ወራት ከቆዬ በኋላ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ክልሉን ለቆ መውጣቱ የሚታወስ ነው። በወቅቱ መከላከያ ከክልሉ የወጣው አርሶ አደሩ የግብርና ሥራ የሚከውንበት ፋታ እንዲያገኝ ለማድረግ እና ለሕዝቡ የጥሞና ጊዜ ለመስጠት ነው መባሉ ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪም፣ የፌዴራል መንግሥት መከላከያን ከትግራይ ክልል እንዲያስወጣ ካስገደዱት ምክንያቶች መካከል አንዳንድ የክልሉ የማኅበረሰብ አካላት ሠራዊቱን ከኋላ በመውጋታቸው እና ዓለም አቀፍ ጫናዎች እየበረቱ መምጣታቸው የሚሉት ተጠቃሽ ምክንያቶች ነበሩ። በወቅቱ መከላከያ ከትግራይ መውጣቱ ለጦርነቱ መቋጫ የሠላም መንገድ ይከፈታል ተብሎ ተስፋ ቢጣልበትም የሆነው ግን በተቃራኒው ነበር።

የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ክልል መውጣቱን ተከትሎ ህወሓት ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ እራሱን አደራጅቶ በአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ ጥቃት መጀመሩን፣ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የሠላም አማራጭ አዳፍኖታል።

የፌዴራል መንግሥት መከላከያ ሠራዊቱን ከትግራይ ባስወጣበት ጊዜ አዲስ የሠላም አማራጭ ይፈጥራል ከመባሉ ባሻገር፣ ሠራዊቱ ከክልሉ መውጣቱን ተከትሎ የተፈጠረውን ብዥታ ለማጥራት በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጉዳዩ ላይ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሠጡት ማብራሪያ፣ ህወሓት ለኢትዮጵያ ሥጋት የማይሆንበት ደረጃ ላይ መድረሱን እና መከላከያ ጥቅምት 24/2013 በተጠቃበት ወቅት ተወስደውበት የነበሩ ከባድ መሣሪያዎቹን ማስመለሱን ገልጸው ነበር።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የመከላከያ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም፣ “ህወሓት የተበተነ ዱቁት” ሆኗል እስከማለት ደርሰው እንደነበር የሚታወስ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያው መድረክ ላይ መከላከያ ትግራይ መግባት ከፈለገ በሦስት ቀን መግባት እንደሚችል እና እጅን በአፍ ላይ የሚያስጭን ተግባር እንደሚፈጽም ገልጸው ነበር።

ይሁን እንጅ ህወሓት 2013 ሐምሌ መጀመሪያ ላይ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ዘልቆ ሲገባ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የመከላከያ ከፍተኛ ኃላፊዎች እንዳሉት መከለከያው በሦስት ቀን ትግራይ መግባት ቀርቶ ክልሎቹን መታደግ አልቻለም። ይልቁንም ጦርነቱ ቀድሞ ከነበረበት ትግራይ ክልል ወጥቶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መስፋፋቱ የሚታወስ ነው።

ህወሓት በአማራ እና በአፋር ክልሎች ላይ የጀመረው ጥቃት ከቀን ወደ ቀን እየተስፋፋ ለብዙ ወራት ቀጥሏል። በኹለቱ ክልሎች ለአምስት ወራት ባዘለቀው ጦርነት ህወሓት ንጹኃን ዜጎችን በመግደል እና በማፈናቀል፣ በየደረሰበት ከመንግሥት እስከ ግለሰብ ያገኘውን ንብረትና ተቋም በማውደም እና በመዝረፍ ላይ ተጠመዶ መቆየቱን የጦርነቱ ሠላባዎች እየገለጹ ይገኛል።

ህወሓት በኹለቱ ክልሎች ላይ ያደረሰው ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ በመቀጠሉ፣ የጦርነቱ ሠላባ ሆኖ ከሚሞተውና ከሚፈናቀለው የማኅበረሰብ ክፍል በተጨማሪ፣ በመንግሥትና ሕዝብ ዘንድ ቀላል የማይባል ጥርጣሬ መፍጠሩ የሚታወስ ነው። በወቅቱ ለጥርጣሬ መንስዔ የሆነው ህወሓት የማጥቃት አቅሙን እያሰፋ፣ ወደ መሀል አገር ዘልቆ በመግባት የሚያደርሰው ጉዳት እየጨመረ መሔዱ እና መንግሥት ይህን ጥቃት ማስቆም አለመቻሉ ነበር።

ባልተጠበቀ ሁኔታ ከትግራይ ተነስቶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት፣ ካስከተለው ሰብዓዊ ኪሳራ በተጨማሪ፣ በኹለቱ ክልሎች ላይ ለረጅም ዓመታት የሚዘልቅ የኢኮኖሚ ጠባሳ እንደፈጠረ እየተገለጸ ነው። ህወሓት በደረሰባቸው የአማራና አፋር አካባቢዎች ከግለሰብ ንብረት እስከ ግዙፍ ኢንዱስትሪ መንደሮች ድረስ ሙሉ በሙሉ እንዳወደመ እና እንደዘረፈ መንግሥት ይፋ አድርጓል።

ህወሓት ሰሜን እና ደቡብ ወሎን አልፎ ሰሜን ሽዋ መድረሱን ተከትሎ ነበር የፌዴራል መንግሥት መከላከያ የማጥቃት ዕርምጃ እንዲወስድ ማዘዙን ያስታወቀው። ይህንኑ ተከትሎ እስከ ሰሜን ሽዋ ዘልቆ የገባው ህወሓት በመከላከያ፣ በአማራ እና አፋር ክልል የጸጥታ ኃይሎች የተቀናጀ ጥቃት ይዟቸው ከነበሩ ቦታዎች ወጠቶ ወደ ትግራይ ክልል እንዲያፈገፍግ የተደረገው።

የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎቹ በጋራ ባደረጉት የማጥቃት ዕርምጃ ወደ ኋላ የተመለሰውን ህወሓትን ተከትለው ወደ ትግራይ በመግባት ጦርነቱን ያጠናቅቃሉ ተብሎ በብዙዎች ዘንድ ይጠበቅ የነበር ቢሆንም፣ መንግሥት መከላከያ ሠራዊቱ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ ውሳኔ አሳልፎ የጸጥታ ኃይሎቹ ባሉበት ቦታ እንዲቆዩ ተደርጓል።

መከላከያ ወደ ትግራይ እንዳይገባ ለምን ታገደ?
ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ ለአምስት ወራት ባደረገው ወረራና ጥቃት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲፈናቀሉና ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ሠለባ እንዲሆኑ ምክንያት ሆኖ ዘልቋል። ህወሓት በኹለቱ ክልሎች በወረራ በቆየባቸው ጊዜያት የደረሱ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች አስከፊ ነበሩ።

ከአምስት ወር የመከላከል ዘመቻ በኋላ፣ የፌዴራል መንግሥት የተጠናከረ ጥቃት ሠንዝሮ ህወሓት በወረራ ይዟቸው ከነበሩ የክልሎቹ አካባቢዎች እንዲወጣ ማድረግ ቢችልም፣ የሸሸውን ወራሪ ኃይል ተከትሎ መከላከያ ሠራዊቱ ወደ ትግራይ እንዳይገባ በፌዴራል መንግሥት በኩል ውሳኔ ተሰጥቷል።

አንድ አንድ የማኅበረሰብ ክፍሎች መከላከያ ወደ ትግራይ እንዳይገባ የመታገዱን ውሳኔ እንደሥጋት ሲመለከቱት ይታያል። የሥጋታቸውም ምንጭ ህወሓት ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ትግራይ ውስጥ እራሱን እንደገና አደራጅቶ ሌላ ጥቃት ሊፈጽም ይችላል ከሚል በመነጨ እንደሆነም ሲገልጽ ይሰማል።

በሌላ በኩል፣ መከላከያ ህወሓትን ተከትሎ ወደ ትግራይ እንዳይገባ መታገዱ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ደግፈው አንዳንዶች እንደ ማስረጃ የተለያዩ ምክንያቶችን ሲያቀርቡ ይደመጣል። ሠራዊቱ በያዘው ቦታ ጸንቶ መቆሙ መከላከያ ከዚህ ቀደም ትግራይ ውስጥ የገጠመውን ችግር ለማስቀረት ተገቢ ውሳኔ ነው ሲሉ ይደመጣሉ።

መንግሥት፣ ህወሓትን ከአማራ እና አፋር ክልሎች ካስወጣ በኋላ ሠራዊቱ በያዛቸው አካባቢዎች ጸንቶ እንዲቆይ እና ቡድኑን ተከታትሎ ወደ ትግራይ እንዳይገባ ከውሳነባቸው ምክንያቶች መካከል፣ ከዚህ በፊት በትግራይ ክልል ካጋጠሙ ችግሮች መማር አስፈላጊ መሆኑ እና በህወሓት ሴራና ወጥመድ ላለመግባት የሚሉት በዋናነት የተጠቀሱ ናቸው።

የፌዴራል መንግሥት፣ “በሰሜን ዕዝ ላይ የሽብር ቡድኑ ክህደት ፈጽሞ በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ ጥቃትና አጸያፊ ድርጊት ሲፈጸም፣ ይከላከለናልና አይዉጣብን ብለዉ ተማጽኖ ያቀረቡ የትግራይ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሠራዊቱን ለመከላከል መሞከር ቀርቶ ድርጊቱን ያላወገዙ መሆናቸዉ፣ ብሎም ሠራዊታችን የተፈጸመበትን ክህደት ለመቀልበስ፣ ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብና የተዘረፉበትን ንብረቶች ለማስመለስ እንቅስቃሴ ባደረገበት ጊዜ በመጀመሪያ አካባቢ በሕዝቡ ዘንድ ይታይ የነበረው የተባባሪነት መንፈስ ተቀይሮ ሠራዊቱ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከኋላ በመወጋቱ፣ ከእነዚህና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች በመማር ሠራዊቱ ተልዕኮዉን በተጠና ሁኔታ ማሳካት ስላለበት አሁን ባለበት አካባቢ እንዲጸና ታዟል” በማለት ለውሳኔው መነሻ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር የተገኛኙ ማስረጃዎችን ጠቁሟል።

ህወሓት ወደ ትግራይ ከሸሸ በኋላ፣ መከላከያ ወደ ትግራይ ይገባል በሚል የተለያዩ የሴራ ወጥመዶች አዘጋጅቶ የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፍ ጫናዎች እንዲበረቱበት ለማድረግ ማቀዱ ስለተደረሰበት ከዚህ ሴራ መውጣት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጉዳዩ ላይ ባቀረቡት የጽሑፍ ማብራሪያ ላይ መጥቀሳቸው የሚታወስ ነው።

መከላከያ ወደ ትግራይ እንዳይገባ ትዕዛዝ የተሰጠው በጊዜያዊነት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የመከላከያ የአገርን የግዛት አንድነትና ሠላም ለአደጋ የሚዳርግ ሁኔታ ተፈጥሯል ብሎ ሲያምን በየትኛዉም ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ ወደ ትግራይ ክልል በመግባት አስፈላጊዉን ዕርምጃ የመዉሰድ ሕገ-መንግሥታዊ መብትና ግዴታ አለው ተብሏል።

መንግሥት መከላከያ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ በጊዜያዊነት መገደቡን በሲቪሉ ማኅበረሰብ ዘንድ ጥርጣሬን እና ሥጋት የሚፈጥር ጉዳይ የሆነው ከዚህ በፊት በተፈጠሩ ተለዋዋጭ የጦርነት ሁኔታዎች መሆኑን ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቀድሞው ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማኅበር ሥራ አስኪጅ ሻለቃ ታመነ አባተ ይገልጻሉ። ሻለቃ ታመነ እንደሚሉት ውሳኔው በሲቪሉ ማኅበረሰብ ዘንድ ሥጋት ቢፈጥርም ከወታደራዊ ሥልትና ከጦርነቱ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሲታይ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብለው እንደሚያምኑ ጠቁመዋል።

መከላካያ ህወሓትን ተከትሎ ትግራይ ክልል ቢገባ፣ ከዚህ ቀደም ከገጠመው የባሰ ጥቃት ሊገጥመው እንደሚችል የሚገልጹት ወታደራዊ ባለሙያው፣ የመከላከያ ትግራይ መግባት ምናልባትም ጦርነቱ የሚያስከትለውን ሰብዓዊ ኪሳራ እና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ሊያባብስ እንደሚችል ይገልጻሉ። በመሆኑም መንግሥት የወሠነው ውሳኔ ጦርቱን ተመጣጣኝ በሆነ ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ በተጠና መንገድ ለማጠናቀቅ ዕድል እንደሚፈጥር ይገልጻሉ።

“በወታደራዊ ሥልት እና አሁን ባለው የጦርነት ኹኔታ መንግሥት መከላከያ ወደ ትግራይ እንዳይገባ ወሠነ ማለት፣ ህወሓትን የማጥቃት ዕርምጃ ቆሟል ማለት አይደለም። በመከላከያ ውስጥ የተለያዩ ቴክኒካዊ እና ህወሓትን የማዳከም ሥራዎች ይሠራሉ” የሚሉት ሻለቃ ታመነ፣ ማኅበረሰቡ ህወሓትን እንደ ደርጅት የማጥቃት ዕርምጃዎች እንዳልቆሙ መገንዘብ አለበት ብለዋል። ይልቁንም በተጠና ወታደራዊ ሥልት ህወሓትን ማዳከም የሚቻልበት ኹኔታ እንዳለ ጠቁመዋል።

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እና የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ ዳምጠው ተስማ(ረ/ፕ) በበኩላቸው በውሳኔው ተገቢነት ላይ ይስማማሉ። ውሳኔው ጦርነቱን በትንሽ ኪሳራ ለማጠናቀቅ እና ሌላ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ጫና ከማስተናገድ የማምለጥ ዕድል እንደሚፈጥር ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቁመዋል።

በውሳኔው ውስጥ ቴክኒካል ጉዳዮች እና ወታደራዊ ግምገማዎች ይኖራሉ የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ፣ ህወሓት ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች ተሸንፎ መውጣቱን ተከትሎ የትግራይ ሕዝብ በህወሓት ላይ ጥያቄ የሚያነሳበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ጠቁመዋል። ቡድኑ በኹለቱ ክልሎች ያስተናገደው ኪሳራ በሕዝቡ ዘንድ ጥያቄ እንዲነሳ ዕድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ፣ ትግራይ ውስጥ የነበረውን የህወሓትን የአሸናፊነት ፕሮፖጋንዳ ወደ ተሸናፊነት የሚቀይር መሆኑን ይገልጻሉ።

ባለፈው ሳምንት በውሳኔው ላይ፣ “ውሳኔዎቻችን በስሜት የሚወሰኑ ሳይሆን ዘላቂ ጥቅምን ያገናዘቡ ናቸው” በሚል ርዕስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፣ “መንግሥት የመከላከያ ሠራዊቱ አሁን በያዛቸው አካባቢዎች ላይ እንዲቆይ ትዕዛዝ ሰጥቷል፤ ይሄንን ውሳኔ የወሠነው በስሜት ሳይሆን የሚያስገኘውን ዘላቂ ጥቅም ከግምት አስገብተን ነው” ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው “የትግራይ እናቶች ይሄንን ሁሉ ምስቅልቅል ያመጣባቸውንና ልጆቻቸውን ነጥቆ ያስጨረሰባቸውን አሸባሪ ኃይል መጠየቅ አለባቸው። ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሄንን አሸባሪ ከጫንቃው ላይ ያስወገደው በመራራ ትግሉ ነው። የትግራይ ሕዝብም እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ይሄንን አሸባሪ ታግሎ የማስወገድ አቅምና ችሎታው አለው። ድጋፍና ዕርዳታ በአስፈለገ ጊዜም የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ከክልሉ ሕዝብ ጎን ይቆማል” ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ሳይንስ እና የወታደራዊ ጉዳይ ባለሙያዎች፣ የህወሓት ወደ ትግራይ መመለስ በትግራይ ሕዝብ ዘንድ ጥያቄ እንዲፈጠር እና ሕዝቡ በቡድኑ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ስለሚያሳልፈው የችግር ጊዜ ህወሓትን ለመጠየቅ ዕድል የሚፈጥርለት መሆኑን ይስማማሉ።

የቡድኑን ወደ ትግራይ መመለስ ሕዝቡ በህወሓት ላይ ጥያቄ እንዲያነሳ ምክንያት ይሆናል የሚሉት ሻለቃ ታመነ፣ ሁኔታው የክልሉን ሕዝብ ዝንባሌ ለማጥናት ዕድል ይፈጥራል፣ጊዜም ይሠጣል ብለዋል። “ህወሓት መቀሌ ገብቶ መዘጋጀቱ የማይቀር ነው፤ መከላከያ ወደ ትግራይ የሚገባ ከሆነ መቀሌን በቦንብ ያጥራል” የሚሉት ሻለቃ፣ ወደ ትግራይ ይዞት የተመለሰውን ኃይል ሲቪል አስመስሎ በተለያዩ ቦታዎች በማሠራጨት ኪሳራ ለማድረስ መዘጋጀቱ ስለማይቀር አሁን ባለው ሁኔታ የመከላከያ ትግራይ መግባት በመከላከያ ላይ ኪሳራ ያስከትላል ብለዋል።

የትግራይ ሕዝብ እንደታሰበው ህወሓትን አሳልፎ ለመስጠት የመንግሥት ተባባሪ ሊሆን ይችላል ወይስ ከቡድኑ ጋር ጸንቶ ይቆያል ለሚለው ጉዳይ ምላሽ ማግኘት ጊዜ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። በጦርነቱ ምክንያት ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እያስተናገደ የሚገኘው የትግራይ ሕዝብ በጊዜ ሒደት ከህወሓት ጋር ቅራኔ ውስጥ የሚገባበት እና የሚዋጋበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ዳምጠው ይገልጻሉ።

የፌዴራል መንግሥት ተስፋ እንዳደረገው የትግራይ ሕዝብ በጊዜ ሒደት ህወሓትን ለመዋጋት እና አሳልፎ ለመስጠት ፍላጎት ከሳየ ጦርነቱ በሠላማዊ መንገድ የሚፈታበት ዕድል እንደሚፈጠር የሚጠቁሙት ዳምጠው፣ የፌዴራል መንግሥቱ የውሳኔውን አጋጣሚ ተጠቅሞ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ማሳመንና ዝንባሌው መሳብ እንዳለበት ጠቁመዋል። የፌዴራል መንግሥት የዲፕሎማሲ አካሄዱን ከዚህ ቀደም እንደነበረው አልደራደርም ከማለት ይልቅ “ለሠላም ቅድሚያ እሰጣሁ” በማለት የውጭ ጫናዎችን ማቃለል እንዳለበት ገልጸዋል። መንግሥት ለድርድር እና ለሠላም ቅድሚያ እንደሚሰጥ ለዓለም አቀፉ ማኅበረብ በተጠናከረ መልኩ በማስረዳት የዲፕሎማሲ ሥራውን መሥራትና ህወሓት ትጥቅ እንዲፈታ የሚያደርጉ ተግባራትን መከወን እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል።

“ከማኅበረሰቡ ጋር የግድ ድርድር ያስፈልጋል” የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ፣ እንደ ድርጅት ከህወሓት ጋር ድርድር ባይደረግም እንኳን ውጊያው ከቀዘቀዘ የሠላም አማራጮች እንደሚፈጠሩ ጠቁመዋል። ይሁን እንጅ መንግሥት በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያሉበትን ከፍተቶች በማረም የተጠናከረ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

መንግሥት የዲፕሎማሲ ሥራዎቹን ከማጠናከር በተጨማሪ፣ ህወሓት ትግራይ ውስጥ እንደገና ለመደራጀት የሚያደርጋቸውን ዝግጅቶች መከታትል፣ ዕርምጃ መውሰድና ጦርነት ዳግመኛ እንዳይባባስ ጠንካራ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባም ዳምጠው ጠቁመዋል። ከዚያም ባለፈ፣ ህወሓት ጥቃት ለመፈጸም በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች እንደ አመጣጡ አስፈላጊ የአጸፋ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ በሁሉም ዘርፍ መዘጋጀት እንዳለበት አሳስበዋል።

ወታደራዊ ባለሙው ሻለቃ ታመነ በበኩላቸው፣ የፌዴራል መንግሥት አንድ ዓመት በዘለቀው ጦርነት ካጋጠሙ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ትምህርት መውሰድ እና ጦርነቱን ባልተራዘመ ጊዜ ማጠናቀቅ የሚያስችሉ ዝግጅቶችን ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል። በወታደራዊ ዘርፍ የሕወሓትን እና የሕዝቡን እንቅስቃሴ እና ዝንባሌ በቅርበት መከታተል፣ ወታደራዊ ስለላዎችን እና ጥናቶችን ሳያቋርጥ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 165 ታኅሣሥ 23 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here