የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖቹን ወደ በረራ ሊመልስ ነው

0
575

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖቹን ከአንድ ወር በኋላ ወደ በረራ ለመመለስ በመጨረሻው የዝግጅት ደረጃ ላይ መሆኑን ገለጸ።
ከአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ መጋቢት 01 ቀን 2011 ጠዋት ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ ዋና ናይሮቢ 149 ሰዎችን ይዞ ይበር የነበረ፣ የበረራ ቁጥር ET302 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን መከስከሱን ተከትሎ ያሉትን ዘመናዊ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖቹን ከበረራ ውጭ ካደረገ ኹለት ዓመት አልፎት ነበር።
አየር መንገዱ አውሮፕላኑን የመመለስ ውሳኔ ላይ የደረሠው፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ የበረራ ደኅንነት ተቆጣጠሪ አካላት ቦይንግ 737 ማክስ ለበረራ ብቁ ነው ብለው አስፈላጊውን ፈቃድ በመስጠታቸው እና በዓለም ዙሪያ ያሉ ሌሎች 34 አየር መንገዶች አውሮፕላኑን ወደ በረራ መመለሳቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኑን ወደ ሥራ ለመመለስ ከመወሰኑ በፊት ኹለት ዓመት ለሚሆን ጊዜ በአውሮፕላኑ ላይ የተደረጉ የዲዛይን ማሻሻያዎችን ሲፈትሽ እና ጥብቅ በሆነ የፈቃድ ሒደት ውስጥ እስኪያልፍ ድረስ ሲጠብቅ መቆየቱን አመልክቷል።
በተጨማሪም የአየር መንገዱ አብራሪዎች፣ መሐንዲሶች፣ ቴክኒሻኖችና የበረራ ሠራተኞች በሙሉ በአውሮፕላኖቹ ደኅንነት ላይ ያላቸው መተማመን አስፈላጊው ደረጃ ላይ መድረሱንም አየር መንገዱ ገልጿል።
በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላኖቹ ደኅንነት አስተማማኝ ሆኖ ወደ በረራ ለመመለስ እንዲችሉ ኹሉም 737 ማክስ አውሮፕላኖቹ ላይ አስፈላጊው ሥራ ማከናወኑን ነው ያሳወቀው።
ይህንንም መሠረት በማድረግ በየካቲት ወር አውሮፕላኖቹን ወደ ሥራ የሚመልሱ ሲሆን፣ ከዚያ በፊት በጥር ወር ላይ ስለ ሒደቱ ዝርዝር ማብራሪያ እንደሚሠጥ ገልጿል።


ቅጽ 4 ቁጥር 165 ታኅሣሥ 23 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here