የፊታችን ታኅሳስ 29 የሚከበረውን የገና በዓል ምክንያት በማድርግ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ውጭ አገር የሚኖሩ አንድ ሚሊዮን ትውልደ ኢትዮጵያውን ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ እንደተደረገላቸው ይታወቃል፡፡
ጥሪ የተደረገላቸው ዳያስፖራዎችም ባለፉት ጥቂት ቀናት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን ‹ሀ› ብለው ጀምረውታል፡፡
ኢትዮጵያውን ወደ አገር ቤት በመምጣት ላይ በመሆናቸው ገና ቁጥራቸው በውል ባይታወቅም፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ባሳለፍነው ሳምንት (የታኅሳስ ሦስተኛ ሳምንት) ወደ አገር ለመጡት ትውልደ ኢትዮጵያዊየን አቀባበል እንዳደረገ በድረ-ገጹ ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ በተለይም በመዲናዋ የሚገኙ ከታች እስከ ላይ ያሉ የመንግሥት አካላት ለዳያስፖራውን አቀባባል ለማድረግ ሲራወጡ ይስተዋላሉ፡፡ በዓለም ዙሪያ ያሉ አገራት ቁጥሩ ከፍና ዝቅ ቢልም የየራሳቸው የሆነ ከአገሩ ውጭ የሚኖር ዜጎች እንዳሏቸው ጥናቶች ይጠቆማሉ፡፡
በመሆኑም የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ ሳዑዲ አራቢያ እና አሜሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዳያስፖራዎችን እንደሚያስተናግዱና በዓለም ላይ ካሉት አገራት መካካል ሕንድ 18 ሚሊዮን በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎች እንዳሏ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት ያመላክታል፡፡
በተያያዘ አገራችን ኢትዮጵያም በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዳያስፖራዎች እንዳሏት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክትር ወንድወሰን ግርማ በተለያዩ መግለጫዎች ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡
የማንኛውም አገር ተወላጅ ዳያስፖራዎች አገራቸውን ለቀው ወደ ሌሎች አጎራባች አጋራት ቢተሙም፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊና በዲፖሎማሲያዊ ሥራዎች ለአገራቸው ቀላል የማይባል ሚና እንሚጫወቱ ይነገራል፡፡
ኃያላን የሚባሉ አገሮች ከዕድገት ጣሪያ እንዲደርሱ ካደረጓቸው ምንያቶች አንዱ ከዳያስፖራው የሚገኝ የዶላር ገቢ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡
አሁን ላይ በኢኮኖሚ የዕድገት ጣሪያ ላይ እንደደረሰች የሚነገርላት ቻይና፣ ዳያስፖራዎቿ በየዓመቱ 80 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገቡ ጥናቶች ያመላክታሉ የሚሉት ወንድወሰን ግርማ ናቸው፡፡
የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክትሩ፤ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራዎችን አስተዋጽዖ ባነሱበት ወቅት፣ ባሳለፍነው ሳምንት 2014፣ ሦስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ከዳያስፖራው ማግኘት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ አገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ችግር በመገንዘብ እስካሁን በውጭ አገር የሚያደርጉት የ‹‹#በቃ›› ድጋፍና የአገሪቱን ጥሪ ተቀብለው ለመምጣት ያሳዩት ፈቃደኝነት አገር ለመርዳት በቂ አቅም እንዳላቸው የሚያሳይ ተግባር ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ዳያስፖራዎች ለምን ጥሪ ተደረገላቸው?
ዳያስፖራዎች ጥሪ የተደረገላቸው በዋናነት አገሪቱ የገጠማትንና አንገት ያስደፋትን ወቅታዊ ችግር በመገንዘብ የደረሳባትን ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ማኅበራዊ ኪሳራ በተቻላቸው መጠን ለመቅረፍ የዜግነት ድሻቸውን ለመወጣት መሆኑ ይታወቃል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶም ከመንግሥት የሚስተዋሉ እንቅስቃሴዎች እንደሚያመለክቱት፣ ዳያስፖራው ከመጣ በኋላ ምን አስተዋጽኦ ማበርክት እንዳለበት የተለያዩ ፕሮግራሞችን መንግሥት በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ነው፡፡
እያንዳንዱ ጉዞ ዓላማን ያነገበ እንደመሆኑ መጠን፣ የዳያስፖራዎች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣትም አገሪቱን ከገጠማት ችግር ለማስመለጥ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ብዙዎች ተስፋ አድርገዋል፡፡
የተደረገላቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ዳያስፖራዎችም በበኩላቸው ጥሪውን ተቀብለው የመጡት የኢትዮጵያን ምድር ለመርገጥ ብቻ ሳይሆን፣ የተጫናትን ወቅታዊ ችግር አብሮ ለመካፈልና ጫናውን ለመቀነስ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
ዳያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ለመዝናናት ወይም በየሆቴሉ ሒዶ ለመጨፈር ሳይሆን፣ አገሪቱ አጥብቆ የተገዳደራትን ችግር ተረድቶ በተቻለው መጠን መፍትሔ ለማበርከት ነው የሚሉት የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር በለንደን መሥራችና ሊቀመንበር ሬዳዋን ከድር ናቸው፡፡
ከሌሎች ዳያስራዎች ቀድመን የመጣነው ጥሪ የተደረገለት አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ ከመጣ በኋላ ምን ማድረግ እንዳለበት አውቆ ዓላውን ለመከወን ይችል ዘንድ ከሚመለከተው አካል ለመመካከር ነው ያሉት ሬዳዋን፣ ፋታ የማይሰጠው የአገሪቱ ችግር ምን እንደሆነ ለመለየት ከመጣን ጀምሮ በውውይይት ላይ ነን ብለዋል፡፡
ዳያስፖራው የመጣበትን ዓላማ ለማሳካት ለምን እንደተጠራ ማወቁ ብቻ በቂ አይደለም የሚሉት ሬዳዋን፣ በቅድሚያ እልባት የሚያስፈልገውን ጉዳይ ማወቁ ተገቢ እንደሆነ ለሁሉም ዳያስፖራዎች ለማሳሰብ ወደዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከዳያስፖራው ምን ትጠብቃለች?
በመንግሥት በኩል ጥሪ የተደረገላቸው አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች፣ አገሪቱ የደረሰባትን ወቅታዊ ችግር እንዲካፈሏትና መፍትሔ እንዲለግሷት እጆችዋን ዘርግታ በመቀበል ላይ ናት፡፡ ኢትዮጵያም ከመጡት ልጆቿ በርካታ ነገሮች እንደምትፈልግ ምሁራን አስቀድመው እያሳሰቡ ይገኛሉ፡፡
ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የዘረፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ ዳያስፖራው አበክሮ በልቡ ሊያትመውና ወደ ተግባር ጥግ ሊያደርሰው የሚገባው ግንባር ቀደሙ ጉዳይ፣ አገሪቱ በጦርነቱ ምክንያት የደረሰባትን ውድመት በመገንዘብ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፖሎማሲያዊ ሥራዎች በኩሉ የራሱን ድርሻ ማበርከት እንዳለበት ነው፡፡
ለየትኛውም አገር ዕድገት ከሌሎች ጥረቶች በተጨማሪ ዳያስፖራዎች ለአገራቸው የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ሚዛን የደፋ ነው የሚሉም አሉ፡፡
እንኳን በችግር ጊዜ በማንኛውም ወቅት እንኳ ቢሆን፣ ዳያስፖራ ለአገር ዕድገት ቀዳሚ ተሰላፊ ነው ይላሉ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ ወንድወሰን ግርማ፡፡
ቻይና ለዕድገቷ መሳካት ከረዷት ነገሮች መካካል በአንድ ወቅት ከዳያስፖራው የተደረገላት ድጋፍ ነው የሚሉት ወንድወሰን፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎችም ቆርጠው ከተነሱ ተመሳሳይ ተግባር ማድረግ ይችላሉ ነው ያሉት፡፡
በዘርፉ ዕውቀት ያላቸው የኢኮኖሚስት ባለሙያዎች በበኩላቸው፣ ዳያስፖራው በኢትትዮጵያ ውስጥ በሚኖረው ቆይታ የሚያደርጋቸውን ዋነኛ ጉዳዮች መንግሥት ከሚያመላክተው አቅጣጫ ጋር ሰንሰለቱን ጠብቆ እንዲያከናወን ለማድረግ በየፈርጁ ለዳያስፖራው ምክር እየሰጡ ነው፡፡
ጥሪ የተደረገለት አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ ወደ ኢትዮጵያ የመምጣቱን ዓላማ ለመረዳት በግንባር ቀደምነት አገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ይጠይቃል የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ደምስ ጫንያለው ናቸው፡፡
እንደ ደምስ ገለጻ ከሆነ፣ ዳያስፖራው በመጀመሪያ ደረጃ ተደራሽ ሊያደርገውና አትኩሮት ሊቸረው የሚገባው ነገር ወቅታዊው ችግር (የኢመርጀንሲ) ጉዳይ መሆኑን ያስረዱት፡፡
በአገሪቱ በተከሰተው ጦርነት በአማራና በአፋር ክልል በርካታ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚናገሩት ደምስ፣ ይህ የማኅበረሰብ ክፍል በቅድሚያ የዳያስፖራውን ትኩረት ይሻል ባይ ናቸው፡፡
ዳያስፖራው የያዘውን ዶላር በባንክ በመመንዘር የውጭ ምንዛሬን ከፍ ማድረግ፣ በጦርነቱ ምክንያት ውድመት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች በመገንባት የበኩሉን ከመወጣት በተጨማሪ፣ በዋናነት በጦርነቱ ምክንያት መጠለያ ያጣው፣ የታረዘው፣ እንዲሁም የተፈናቀለው የማኅበረሰብ ክፍል ከእስካሁኑ ለባሰ ርሀብ እንዳይጋለጥ የድርሻውን ቢወጣ መልካም ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት በርካታ ዜጎች አካባቢያቸውን ለቀው እንደተፈናቀሉ ይነገራል፡፡ አብዛኛዎቹ ዜጎችም በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ በነበሩት የአማራ አፋር ክልል ነዋሪ የነበሩ ናቸው፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስት ኮሚሽን እንደገለጸው፣ በአማራ ክልል ብቻ ኹለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዜጎች ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፣ 328 ሺሕ ተፈናቃዮች በመንግሥት ድጋፍ ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ተመላሾች ከፍተኛ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያሻቸው መገለጹ የሚታወስ ነው፡፡
ምግብ ድጋፉ ጋር በተያያዝ፣ ክልሉ ለ11 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሕዝብ አንድ ነጥብ ኹለት ሚሊዮን ኩንታል የእህል ድጋፍ በየወሩ እንደሚያስፈል በአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስት ኮሚሽን በኩል ታኅሳስ 19/2014 ያወጣው መረጃ ይጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል፣ እን ደምስ ጫን ያለው አስተያያት ከሆነ ዳያስፖራው ትኩረት ሊሰጠው የሚሻው ሌላው ጉዳይ ውድመት የደረሰበት የትምህርትና የጤና ተቋማት ጉዳይ ነው፡፡
ጥሪ ከተደረገላቸው አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች መካካል ከለንደን የመጡት ሬዳዋን ከድር በበኩላቸው፣ ዳያስፖራው የምግብ ዕርዳታ ከማድርግ ጀምሮ የወደሙ ተቋማትን እስከመገንባት የሚደረስ የቤት ሥራ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የህወሓት ቡድን በኢትዮጵያ ላይ በከፈተው ጦርነት በርካታ ንጹኃን ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡ በወረራው አያሌ የግልና የመንግሥት ንብረቶች ከመዘረፋቸው በተጨማሪ፣ የተለያዩ ተቋማት መውደማቸውን መንግስት እየገለጸ ነው፡፡
በኢትዮጵያ በቅርቡ ከአምስት ወር ለበለጠ ጊዜ በተከናወነው ጦርነት በአማራ ክልል ከአራት ሺሕ በላይ፣ በአፋር ክልል ደግሞ 759 የትምህርት ተቋማት አስከፊ ውድመት እንደደረሰባቸው ይነጋራል፡፡
በዚህም የኢኮኖሚ ውድመት ከመከሰቱም ባሻገር፣ ወደፊት ለአገር ዕድገት የተሸለ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው ዕምነት የተጣለባቸው ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች፣ እንዲሁም ከ11ሺሕ በላይ መምህራን ከትምህርት ገበታቸው ውጭ እደሆኑ የኢፌዴሪ ትምህር ሚኒስቴር መግለጫ ያመላክታል፡፡
በሌላ በኩል ዳያስፖራው ሊያተኩርበት ይገባዋል የተባለው በተለይም በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ የነበሩ ዜጎች የገጠማቸው የመድኃኒት ዕጥረትና የጤና ተቋማትን ውድመት መገንዘብ ነው፡፡
በጦርነቱ ምክንያት እስካሁን ስንት ሰዎች በመድኃኒት ዕጥረት ሕይወታቸው እንዳለፈ ትክክለኛ ቁጥሩ ባይታወቅም፣ በርካታ ሰዎች በስኳር፣ በደም ግፊትና በመሳሰሉት በሽታዎች ለሞት መዳረጋቸው ይታመናል፡፡
የጤና ተቋማትም በተመለከተ እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት፣ ከኹለት ሺሕ 700 በላይ የጤና ተቋማት በጦርነቱ ውድመት እንደደረሰባቸው የጤና ሚኒስቴር መግለጫ ይጠቁማል፡፡
በመሆኑም ኢትዮዮጵያ ዳያስፖራው እንዲገነዘባቸውና ትኩረት እንዲሰጣቸው ከምትጠብቃቸው ጉዳዮች መካከል፣ የወደሙ ተቋማት ተጠቃሽ መሆናቸውን ነው ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ባለሙያዎች ያስረዱት፡፡
ከ‹‹አመርጀንሲ›› ጉዳይ በተጨማሪ ዳያስፖራው በኹለተኛ ደረጃ አገሪቱ የዶላር ምንዛሬ ዕንድታገኝ ታላቅ ሚናን የመጫወት የቤት ሥራ እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡
የዳያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በዶላር ምንዛሬም ታላቅ ሚናን ይጫወታል የሚሉት ደምስ፣ የተጠራው አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ ቢመጣና ቢያንስ እንኳን እያንዳንዱ ዳያስፖራ አንድ ሺሕ ዶላር ወጭ ቢያደርግ በቀላሉ አንድ ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ይቻላል ይላሉ፡፡
በመሆኑም ዳያስፖራው የራሳቸውን አካውንት በመክፈት ዶላራቸውን እንዲመነዝሩ የብሔራዊ ባንክ እያሳሰበ ሰምቻለሁ ያሉት ደምስ፣ ዳያስፖራው የተመላከተውን አቅጣጫ በተግባር ላይ ካዋለው ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ቀላል የማይባል ሚና በመጫዎት የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ያስችላል ሲሉ ሙያዊ ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡ የዳያስፖራውን መምጣት ተከትሎ የመንግስት የቤት ሥራዎች ምን መሆን አለባቸው በሚለው ሀሳብ ላይ ደምስ አስተያየት አላቸው፡፡
በመንግሥት በኩል በርካታ ነገሮች በቅድሚ አቅጣጫ እየተሰጣቸው ስለመሆኑ ሚዲያዎችን መከታተል በቂ ነው የሚሉት ደምስ፣ አሁን ከመንግሥት የሚያስፈልገው ዕያደረገው ያለውን ውይይትና ዳያስፖራው በምን መልኩ መጓዝ እንዳለበት ያመላከታቸውን አቅጣጫዎች ከንግግር በዘለለ ተግባር ላይ እንዲውሉ ማድረግ ነው ሲሉ ምክር ለግሰዋል፡፡
በሌከላ በኩል ዳያስፖራውም እንዲሁ ‹‹ተሰበሰብን፤ አየን፤ መጣን.›› ከማለት በዘለለ፣ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የአገሪቱን ችግር በቅድሚያ ተገንዝቦ መሥራት አለበት ሲሉ ከወዲሁ አሳስበዋል፡፡
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው በሦስተኛ ደረጃ ያነሱት ነጥብ፣ ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት ማበርከት የሚጠነቅበትን የቤት ሥራ ነው፡፡ ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት በኩልም እንዲሠራ ይገጠበቃል የሚሉት ደምስ፣ በዕርዳታ ከሚያቀርበው ዶላር በላቀ ደረጃ አገሪቱን ካለችበት ችግር ሊያወጣት የሚችለው በኢንቨስትመንት በኩል የሚሠራው ሥራ ነው ሲሉ የግል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ባለሙያው በመጨረሻም ዳያስፖራው አንቨስት በማድረጉ ላይ አትኩሮ ቢሠራ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሊያደርጋት የሚችል ዕድል ይፈጠራል፡፡ ወደ አገር በመግባት ላይ ያሉት ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚያውቁትን የፈጠራ ሥራም ጭምር ለማኅበረሰቡ በማካፈል የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡
ከለንደን የመጡት ሬድዋን ከድር በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ከዳያስፖራው በርካታ ነገሮች ትጠብቃለች ያሉ ሲሆን፣ በዋናነትም ኹለት ነገሮች ላይ ማተኮር ተገቢነው ሲሉ ያሳስባሉ፡፡
ሬዳዋን እንደገለጹት፣ ለዳያስፖራው መምጣት ዋነኛ ምክንያት አገሪቱን በወቅቱ የፈተናት ጦርነት ያስከተለውን ጉዳት በመገንዘብ ችግር ለደረሰበት ማኅበረሰብና ወድመት ለደረሰበት ተቋም ድጋፍ በማድረግና አለኝታነቱን ለማሳየት ነው፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ችግር የደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በመጀመሪያ ደረጃ የምግብና የመጠለያ ድጋፍ ማድረግ ቀዳሚው ድርሻ እንደሆነ ኹሉም ዳያስፖራዎች አሳስበዋል፡፡
በጦርነቱ በደረሰው ጉዳት በአገሪቱ የተከሠተውን ችግር ለመፍታት ሠፋ ያለ ጊዜ ቢያስፈልግም፣ ዳያስፖራው በተቻለው መጠን በጦርነቱ ቀጠና አካባቢ የነበሩ አካባቢዎችን ተከፋፍሎ በመያዝ የበኩሉን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡
አያይዘውም፣ እስካሁን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተደረገውና እየተደረገ ባለው ውይይት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፣ ዳያስፖራው አገሪቱ ያለችበትን ችግር በጥልቅ ተረድቶ በትክክል ከሠራ ችግሩን ለመቅረፍ አቅም አለው ሲሉ እርግጠኛ ሆነው ተናግረዋል፡፡
ችግር የደረሰባቸውን አካበቢዎች ዳያስፖራው ተከፋፍሎ መርዳት እንዳለበት የሚያምኑት ሬዳዋን፣ ለአብነትም ከአሜሪካ የሚመጡት የአፋር ክልልን፣ ከለንደን የሚመጡት የአማራ ክልልን ተከፋፍለው ቢያግዙ፣ ድጋፍ የሚያስፈልገውን የማኅበረሰብ ክፍልና መቋቋም የሚሻውን የወደመ ተቋም መገንባት የሚያስችል አቅም አላቸው ነው ያሉት፡፡
ሬዳዋን አክለውም፣ እያንዳንዱ ዳያስፖራ ይዞት የሚመጣውን ዶላር በአግባቡ በመጠቀም ለራሱ ፍጆታ ከሚያውለው ቀነስ በማድረግና የተለያየ ሥራዎችን በመሥራት ኢትዮጵያ እንድታንሠራራ የማድረግ ዓለማውን ዕውን ለማድረግ መትጋት አለበት ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡
‹‹ወደ ኢትዮዮጵያ ያመጣኝ የዜግነት ግዴታየ ነው፤ ደግሞስ የግድ ችግር ቤትን እስሚያንኳኳ ይጠበቃል እንዴ!›› የሚሉት ሬዳዋን ከድር፣ ባሳለፍነው የታኅሳስ ሦስተኛ ሳምንት 2014 ከአቃቂ ቀሊቲ ክፍለ ከተማ ጋር በመተባበር በሸዋ ሮቢት ለተቸገሩ ወገኖች የአምስት ሚሊዮን ብር የከብትና የቁሳቁስ ዕርዳታ አድርገናልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ሰሞኑን ወደ ደሴ ከተማና ወደ አፋር ክልል ለመሔድ ዕቅድ እንደያዙ አማለክተው፣ በመጨረሻም ወደ ኢትዮጵያ የገቡና የሚገቡ ኹሉም ዳያስፖራዎች የሚመጡት ከሰለጠነ አካቢቢ እንደመሆኑ መጠን፣ የሚገጥማቸውን ችግር ተቋቁመው እስካሁን የተሠራውን አርአያ በመከተል ዓላማቸውን እንደያሳኩ ለማሳሰብ ወደዋል፡፡
ቅጽ 4 ቁጥር 165 ታኅሣሥ 23 2014



