እየተሳሰብን ክፉ ጊዜን እንለፍ!

0
776

ሰው ለሰው ብቻ ሳይሆን ለተፈጥሮም ጭምር ማሰብ እንዳለበት የምናስተምርበት ዘመን ላይ አይደለንም። እያንዳንዱ ፍጥረት ለኹላችንም ጥቅም እንዳለው የማናውቅ ትውልዶች የምንኖርበት ጊዜም አይደለም። ሰው ለሰው መድኃኒቱ ብቻ ሳይሆን፣ እንዳይታመም አስቀድሞ መከላከያውና ክትባቱም መሆን ነው ያለበት።

ሰው ለሰው መተሳሰብ ያለበት ወቅትን ወይም በዓላትን ብቻ ተመርኩዞ መሆን እንደሌለበት አዲስ ማለዳ ታምናለች። ችግር ሲኖር ወይም መከራ ሲበረታ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ መተሳሰብ ይጠበቃል እንጂ፣ በእንዲህ ዓይነት ወቅት ብቻ መረዳዳት ያስፈልጋል የሚል የለም። ኮሮና ወረርሽኝ ሆኖ የተከሠተ ሰሞን፣ የቆየ ባህላችን የነበረው መተጋገዝ እንደአዲስ ተቀስቅሶ ኹላችንንም ያስደሰተን የቅርብ ትዝታ ነው። ያን የመሰለ በጎ ተግባር ግን በመደበኛ መልኩ መቀጠል ሳይችል ቀርቶ በጥሪና በቅስቀሳ ብቻ የሚገለጥ ሆኖ ዘልቋል።

በጦርነቱ ሳቢያ የተከሰተውን ጉስቁልናና መከራ ለመቀነስ፣ እንዲሁም የዜጎችንም ሥቃይ ለመካፈል የተለያዩ ዘመቻዎች ተካሒደው በመረዳዳት ረገድ ጥሩ ውጤት የተገኘባቸው ነበሩ። ሒደቱ አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ቢሆንም፣ እንከኖች ግን ይታዩበታል። ከማሰባሰብ ሒደቱ ጀምሮ እስከማከፋፈሉ፣ እንዲሁም ወቅቱና ዓይነቱ ቅሬታ ሲቀርብበት ይሰማል። በእንዲህ ዓይነት አገራዊ ጉዳይም ሆነ መደበኛ የመርዳት ሒደቱን ቀስቃሽና ተቀስቃሽ እስኪኖር ዘመቻዎች መጠበቅ የለባቸውም። በሌላ በኩል የአቅሙን የሚሠጥ ሰው ሥጦታው ለታይታ ሳይሆን ከልብ የሆነና ምስጋናን እንደውለታ የማይጠብቅበት መሆን ይገባዋል።

እነ እገለሌ ብቻ ይርዱ ተብሎ መስፈርት እንደማይወጣው ኹሉ፣ ተረጂ መሆን የሚገባውም እንዲህ ዓይነት ወገን ብቻ ነው ብሎ መፈረጅም እንደማይገባ መታመን አለበት። መስጠት የሚቻለው ይህን ይህን ብቻ ነው ብሎ ዓይነቱን መገደብ ተገቢ እንደማይሆነው ኹሉ፣ መረዳት ይገባኛል ብሎ የጠየቀ ማስረጃ አምጣ የማይባልበትና ኹሉም ተዛዝኖ የሚሠጣጣበት ዘመን እንዲመጣ መጣር እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

መረዳዳት በፈቃድ የሚደረግ ቢሆንም፣ እንደየአቅማችን የውዴታ ግዴታችን ተግባር እንደሆነ ኹላችንም ማመን ይጠበቅብናል። ሀብት የግላችን ብቻ የሆነ፣ ያለማንም ልፋት ብቻችንን ቆፍረን ያገኘነው እንደሆነ ሊሰማን አይገባም። ባልተማከለና ፍትሐዊ የሀብት ማከፋፈያ ሥርዓት በሌለበት ሁኔታ፣ አንድ ግለሰብ ያለሌሎች ድካምና ተሳትፎ የትም መድረስ እንደማይችል ሊገነዘብ ይገባል። ተገቢ ዕውቀትና ሥርዓት በሌለበት ሁኔታ በዕጥረት ምክንያት ለሰው ልጆች ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እኩል ሀብትና ንብረትን ማዳረስ ባለመቻሉ፣ ውሱን ነገሮችን ጥቂቶች እንዲይዟቸውና ለሌላውና ለጋራ ጥቅም ሲሉ እንዲያስተዳድሯቸው ማድረግ በእኛ ዘመን የተጀመረ አስተሳሰብ አይደለም።

የገንዘብ አፈጣጠር ወይም የግብይት አካሄዶች በሰው ልጅ መካከል ያለውን ልዩነትም ሆነ የሀብት አለመመጣጠንን ለማቀራረብ ታስበው ጥቅም ላይ የዋሉ እንደሆነም ሊታወቅ ይገባል። ሀብት ያገኘ ሰው ሀብቱ ይበልጥ በሚያስፈልግበት ቦታ ላይ እንዲውል እሱ አዛዥ ሆኖበት ሌላውን እያሠራበት ካላስተዳደረው በስተቀር፣ አከማችቶ ማስቀመጡ የነፍስ ዕዳን እንደሚያቆይበትም በየትኛውም ዕምነት የሚነገር አስተምህሮ ነው።

መረዳዳት ባህላችን እስኪሆን ድረስ ብዙ መሥራት የሚጠበቅብን ቢሆንም፣ የሚለምንም ሆነ የሚጠይቅ ሳይኖር እየተሻማን የምንሰጥበት ዘመን ላይ እንድንደርስ ብዙ መጣር ይገባናል። መለመን ኃጢያትም ሆነ ወንጀል ስላልሆነ፣ መንግሥትም ሆኑ ባለሀብቶች ድሃ በፈለገበት ቦታና መንገድ ፣እስካላጭበረበረ ድረስ፣ ምፅዋት እንዳይጠይቅ የሚደረግበትን ተግባር ማቋረጥ ይገባቸዋል። በአንጻሩ በየምግብ ቤቱ ደጃፍ “ሰውን አላስበላ አሉ” እያሉ የራባቸውን ማንገላታት ተገቢ ባይሆንም፣ ሥርዓት ባለው መንገድ የራበው ምግብ የሚያገኝበት ሁኔታ ቢመቻች መልካም ነው። ብዙዎች፣ በተለይ ተቋማት፣ ተጠያቂነት እንዳያመጣብን በሚል የተረፋቸውን ምግብ እንዲጣልና ጥቅም ሳይሰጥ እንዲወገድ በሚያደርጉበት በዚህ ዘመን፣ ትራፊንም ሰብስበው ለቸገራቸው የሚሸጡ እንዳሉ ይሰማል። ማንኛውም እንዲህ ዓይነት ያልተገባ አሠራር ሥር ሠዶ እንደአገር ችግር ከማስከተሉ በፊት፣ ሥርዓት እንዲበጅለትና ሒደቱን የሚያስተባብር አካል በቋሚነት እንዲኖር አዲስ ማለዳ ጥሪ ታቀርባለች።

ማንኛውም ሰው በፈለገውና በፈቀደው መንገድ፣ በዓልንም ሆነ ሌላ ምክንያትን ተንተርሶ፣ መርዳትም ሆነ ወገኑን ማገዝ ቢችልም፣ የመስጠትና የመረዳዳት ሒደቱ ዓላማውን የማያሳካና ጥቂቶች አላግባብ እንዲበለጽጉበት ዕድል የሚሠጥ መሆን የለበትም። ችግርን የሚያውቁና እውስጡ ያሉ የሌላውን መከራ ይበልጥ ስለሚረዱ የመተጋገዝ አጋጣሚው በእነሱ ዘንድ የበለጠ እንደሆነ ቢነገርም፣ ዕጥረት ባለበትም ሆነ ጉልበተኞች በሚያዘወትሩት አካባቢ ደግሞ ደካሞች ለበለጠ ችግርና እንግልት ሲዳረጉ ይታያል። የተበጣጠሰ ዕርዳታ ሁኖ ያልደረሳቸው እየበዙ ጥቂቶችን በተደጋጋሚ ማዕከል ያደረገ የማከፋፈል ሒደት በተፈናቃዮች ዘንድ እንደታየው በመደበኛ ተረጂዎች በኩልም እንዳይደጋገም መሠራት ይኖርበታል።

መንግሥት ግብር የሚሰበስበው ለምን ዓላማ እንደሆነ ባለሥልጣናቱን ሊያሳውቅ ግድ ይለዋል። ከሀብታም የሚሰበሰብ ሀብት ለራሱ ለሀብታሙ አገልግሎት ብቻ እንዲውል ታስቦ አለመሆኑን ኹሉም ሊረዳ ይገባል። ከድሃ ገበሬ ተነጥቆ ለልማት ተብሎ አቅሙ ላላቸው ኢንቨስተሮች ከሚሰጠው ቦታ በተጨማሪ፣ በርካታ ጉዳዩች ማንን ማዕከል ማድረግ እንዳለባቸው ሊጤን ይገባል። መንግሥት አስቀድሞ ለድሃው መቆም እንዳለበት አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ሀብት ያለው በሀብቱ ደኅንነቱንም ሆነ አቅሙን ይበልጥ ማጎልበት አንደሚችል ሊታወቅ ግድ ይላል። መንግሥት መንግሥት መሆን የሚገባው ስለድሃው ሲል መሆኑን ባለሥልጣናቱ መረዳት ይጠበቅባቸዋል። ለድሃ መቆም ሲኖርባቸው ድሃ ዐንይ በሚል የሚጠየፉ የሚታዩትም የመንግሥትነትን ዓላማ ካለመረዳት የመነጨ ነው። “ድሃ በፈለገበት ይኑር አትከልክሉት” ብለው አፄ ምኒልክ ያወጡትን ዐዋጅ መልዕክት የዘመናችን ባለሥልጣናት ሊረዱ ይገባል። አገርም ሆነ መንግሥት ኅልውናቸው አደጋ ላይ በሚወድቅበት ወቅት ለነፍሱ ሳይሳሳ በበለጠ የሚዋደቀው ድሃው ስለሆነ ይበልጥ እሱ ላይ ብቻ ይተኮር ባይባልም፣ ያለ ድሃም ሆነ ሀብታም አንድ አገር እንደአገር ልትቆም እንደማትችል ልንረዳ ይገባል።

ሠሞኑን ሐብት ያላቸው በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደአገራቸው ተመልሰው እንዲቆዩና አገራቸውን ከገጠማት ችግር እንዲታደጉ ጥሪ ቀርቦላቸው ነበር። ይህ በጎ ዓላማ ያለው ጥሪ ጥሩ ምላሽ እያገኘ ቢሆንም፣ ድሃ ለፍቶ አዳረዎች ላይ ያስከተለው ተጽዕኖ ግን ብዙዎችን ያሳዘነ ነው። ለሀብታም ዕይታ ሲባል ድሃው ፆሙን ይደር፤ የለፋበትንም ይጣ፤ ማለት በየትኛውም መመዘኛ እንደሚያስጠይቅ አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትፈልጋለች።

በአገራችን ያለውን ድህንትንም ሆነ የድሃውን ሁኔታና መጠን፣ እንኳን እዚሁ ተወልደው ያደጉት ይቅርና ሌላውም የሚገምተው ጉዳይ ነው። ገመና መሸፈን ማለት የሚያዋርድን እንጂ ድሃ መሆንን አይደለም። ዘርፎና አጭበርብሮ በምቾት ከሚኖር ይልቅ በችግር ምክንያት ብርድና ፀሐዩ እየተፈራረቀበት ኑሮውን ለማሸነፍ ደፋ ቀና የሚለው ከማንም በላይ በሥራው ሊኮራ ይገባዋል። የራስን ኑሮ ለማሸነፍ ብቻ ሳይሆን፣ ሌላው ዝቅ ብሎ ለመሥራት የማይደፍራቸውን ይህን መሠል ሥራዎች የሚሠሩትን ጎብኚዎቹ ተመልክተው እንዲያግዟቸው ማድረግ እንጂ፣ እነሱን ከልክሎ በራሳቸው እንዲሸማቀቁ የማድረጉ ሥራ ሊታፈርበት ይገባል።

አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ድሃ የሆነ ቤተሰብ እንዳለው ይታመናል። ሀብታም የሚባሉትም የሚረዷቸው የተቸገሩ የቤተሰብ አባሎች እንደሚኖሯቸው ማወቅ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ብርቅ አይደለም። ታዲያ ሥራ አይናቅም እየተባለ በሚለፈፍባት አገራችን ሕጋዊ አድርጎ የተወሰነ ሥራን የሚሠሩ ላይ መድሎና መገለል መፈጸም አይገባም። የመተጋገዝን ባህል በማጎልበት ፈንታ፣ እንዲህ ዓይነት የበዓልንና ጎብኚዎችን መምጣት ተመርኩዞ፣ በዘላቂነት እዚሁ እየሠሩ መኖር የሚፈልጉ ላይ እንዲህ ዓይነት አስነዋሪ ተግባር መፈጸሙ በስማቸው እንዲህ የሚደረግባቸው ላይ የሚፈጥረው የሥነልቦና ጫናም ሊታሰብ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማስታወስ ትወዳለች።

“የሥጦታ ፈረስ ጥርሱ አይታይም” እየተባለ በመንግሥት ደረጃ ምጽዋዓት በሚጠበቅበትና በሚለመንበትም አገር፣ ሠርተው የሚበሉና በሥራቸው ሊኮሩ የሚገባቸውን ለይቶ መከልከል ገጽታን መገንባት ሳይሆን፣ ማበላሸትና ማጥፋት ነው። ደርግ ወደወሎ ሠፈር መግቢያ ጋ የነበረውን የተጎሳቆለ ሠፈር የውጭ እንግዶች ሲገቡ አይተው እንዳያሳፍሩን ብሎ በግንብ አጠረ እንጂ አላሳደዳቸውም። ከቀደመው እንኳን ተምረን “ውስጡን ለቄስ” ከሚል ብሒል ወጥተን በማንነታችንና በምንነታችን የምኮራበት ዘመን እንዲመጣ መረባረብ ይጠበቅብናል።


ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here