የመንበረ ጸባዖት ቅድስ ሥላሴ ካቴድራል ሊታደስ ነው

0
537

በአዲስ አበባ ከተማ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ የሚገኘው መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊታደስ ነው ተብሏል።
በዚህም፣ ኪነ-ሕንጻዊ ይዘቱን የሚያጎሉ በርካታ ቅርጻ ቅርጾችን የያዘውን ጥንታዊ ካቴድራል ለማደስ የሚያስችለው ጥናት ላለፉት 9 ወራት ሲካሄድ ቆይቶ ተጠናቋል ተብሏል።
ጥናቱ በካቴድራሉ ሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ አስተባባሪነት፣ በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ፈቃድና ክትትል በተቋራጮች የተካሄደ ሲሆን፣ ዕድሳቱን ለማካሄድ በሚያስችል መልኩ መከናወኑ ተነግሯል።
ካቴድራሉ ሳይጠገን ለረዥም ዓመታት በማገልገሉ ምክንያት፣ ውስጣዊ እና ውጫዊ ክፍሎቹ ማርጀታቸው፣ ማፍሰስ እና የተለያዩ አካላዊ ጉዳቶችን ማስተናገድ መጀመራቸው ተነግሯል።
ከከፍተኛ የውኃ ሥርገት ሥጋት ባሻገር፣ ሕንጻው ጣራው እያፈሰሰ፣ ግድግዳው እየተቀረፈ እና ሞዛይኮቹ እየረገፉ በመውደቅ እንደተጎዳ በጥናቱ ተለይቷልም ነው የተባለው።
በመሆኑም ከኃይማኖታዊና መንፈሳዊ አገልግሎቱ ባሻገር ትልቅ አገራዊ አበርክቶ ያለውን ካቴድራሉን እና ቅርጻቅርጾቹን፣ ኪነ-ጥበባዊና ቅርሳዊ ይዞታቸውን በጠበቀ መልኩ ለመጠገንና ለማደስ ዝግጅቶች በመደረግ ላይ መሆናቸው ተገልጿል። ዕድሳቱ የካቴድራሉን ቅጥረ ግቢ እንደሚያካትትም ነው የተነገረው።


ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here