አገራዊ መግባባት ይበል የሚያሠኝ ዕርምጃ ነዉ

በኢትዮጵያ በረጅም ታሪኳ አገራዊ ልዩነቶች ሲመጡ በውይይት ከመፍታት ይልቅ፣ በጉልበት ለመፍታት የሚወሰድ ዕርምጃ እንደሚበልጥ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ። በተለይ ባለፉት ሦስት መንግሥታት በሕዝብ ዘንድ የነበሩ ጥያቄዎችና የሚነሱ ልዩነቶችን በንግግር መፍታት ስላልተቻለ ጉዳዮቹም ሆኑ ችግሮቹ እስካሁን ዕልባት ሳያገኙ መቆየታቸው ይነገራል። እነዚህን ልዩነቶች ተወያይቶ ለመፍታት በመንግሥት ደረጃ አገራዊ መግባባት ላይ የሚያደርስ የተባለ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ስለሒደቱ፣ እንዲሁም ስለጥቅሙ ከታሪክ ጋር እያነጻጸሩ ጋዜጠኛ ጁሃር ሳዲቅ ይህን ጽሑፍ አሰናድተዋል።

በአገራችን ኢትዮጵያ ቁጭ ብሎ መተማማት እንጂ፣ ቁጭ ብሎ በጠረጴዛ ዙሪያ ሐሣብ አንሸራሽሮ በልዩነቶች ላይ፣ አንድ በሚያደርጉ ሐሣቦች ዙሪያ የመስማማት ልምድ የለም። አንዱ የሌላውን ሐሣብ ከማድመጥ ይልቅ፣ የኔ ብቻ ትክክል ነው የሚል ጠርዝ ላይ የቆመ አስተሣሰብ ይዞ ከመጓተት ዉጪ ውይይት (discussion) አልተለመደም ። ዉይይቶቻችን በሙሉ እገሌ ምናለ የሚለዉን ሰምቶ ለመፈረጅ እንጂ፣ በሐሣቦች ላይ ረዥም ጊዜ በሰከነ መንፈስ፣ ዘመናዊ በሆነ መልኩ፣ እንደ ሕዝብም እንደተቋምም እንደዚህ ዓይነት ተሞክሮ (Trend) የለንም።

በዚህ የተነሣ ለበርካታ ዓመታት መጨቃጨቂያ የነበሩ ፣ እንዲሁም ሲጠየቁ የነበሩ ሳይመለሱ የቀሩ ችግሮች ላይ የአእምሮና ሐሳብ ፍጭት ተደርጎባቸው ዕልባት ያላገኙ፣ ተገቢ ባልሆነ መልኩ ወደዚህ ትዉልድ ተንከባለዉ የመጡ በርካታ ጉዳዮች እንዲከመሩ አድርጓል። ይህ ሁሉ እንዲሆን መሠረታዊ ችግሩ በሰከነ መንገድ መነጋገር መወያየት አለመቻሉ ነዉ ።

የደርግ መንግሥት የተማሪዉን አብዮት ጠልፎ ንጉሠ ነገሥቱን በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን አዉርዶ ሥልጣን ከያዘ በኋላ፣ በአብዮቱ ዉጤት ከመጨቃጨቅ ዉጪ፣ በኢትዮጵያ ዘላቂነት ጉዳይ፣ እንዲሁም በአገሪቱ በሚንጸባረቁ ልዩነቶች ዙሪያ ለመወያየት የደፈረ አልነበረም። በዚህም በአገራዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሰከነ ዉይይት ካለመደረጉ የተነሣ በነጭ ሽብርና በቀይ ሽብር፣ ወዘተ. ምን ያህል ሕይወት እንዳጣን ታሪክ ይነግረናል ። የነበረዉ የመጠፋፋት፣ የመበላላት፣ ያለመተማመን የሠፈነበት ፖለቲካ “አብዮት ልጇን በላች” እስኪባል መጥፎነቱ ይዘከራል ።

ላለፉት ሠላሣ ዓመታት ሥልጣኑን የተረከበዉ የህወሓት/ኢሕአዴግ/ መንግሥት ከደርግ የተሻለ ለአገራዊ መግባባት ውይይት (National dialogue) የነበረዉ ዕድል (opportunity) በርካታ ቢሆንም፣ አሁንም መረን ከለቀቀ የሥልጣን ጥምና አምባገነንነት፣ የበላይነት መንፈስ፣ ይዞት የመጣዉም የተንሸዋረረ ዓላማ ይህንን ማድረግ አይፈቅድለትም ነበር። ከንጉሠ ነገሥቱ ወደ ደርግ፣ ከደርግ ወደ ህወሓት መራሹ ፈላጭ ቆራጭ መንግሥት እየተንከባለሉ የመጡ መፍትሔ የሚሹ አገራዊ አጀንዳዎችን ትኩረት ከመንፈግ ይልቅ፣ ለ30 ዓመት የተጠመደው ዘርፎ ለማምለጥና አፍርሶ ለመሸሽ ስለነበር አገራዊ መግባባት ማድረግ አልተቻለም። ምናልባት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዉጥረት ሲገጥማቸዉ የተለያዩ ምሁራኖች ቢያወያዩም፣ ከልብ ያለቀሱበት፣ ያልተጨነቁበት፣ ያልመከሩበት፣ ስለነበር ውይይቱ ቃል መቀበል ብቻ ነበር ማለት ይቻላል ።

እንግዲህ ኢትዮጵያ ካለፉት ኹለት ሥርዓቶች ያወሳሰቡት ችግሮች ሳይቀረፉ የክፉ መንፈስ ባለቤት (Evil Minded) የሆነዉ ህወሓት በሥልጣን በቆየባቸው ላለፉት ሠላሣ ዓመታት ትዉልዱን እንዴት ጭንቅላቱን እንደመረዘዉ፣ምን ያህል ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዕሴቶቻችንን የበለጠ አወሳስቦት እንደነበር የሚታወቅ ነዉ። የዘረጋው የጥላቻ መንፈስ ፣ መጥፎ ትርክቶች ፣ የዘረጋው የዘር ፖለቲካ አስተሣሠብ ፣ ፀረ-አንድነትና በሐሣብ የሚሞግቱትን ማጥቃት፣ ወዘተ. የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር ከፍተኛ ሥጋት የተደቀነበት ጣራ (higher climax) ላይ አድርሶት ነበር ማለት ይቻላል።

ይኸዉም ከላይ እንዳልኩት ህወሓት በሥልጣን በነበረበት ወቅት አገራዊ መግባባት ላይ ዉይይት ለማድረግ የሚያግድ ምንም ዓይነት እንቅፋት ሊሆን የሚችል ነገር አልነበረም። በኹሉም የአገሪቱ ክፍሎች በዘረጋው የአፈና መዋቅር የተረጋጋ የፖለቲካ ድባብ ነበረዉ። ቢያንስ እንደ ደርግ በተለያየ ጦርነት የመጠመድ አጋጣሚ አላጋጠመውም፤ በዚህ የተነሣ የተደላደለ ዕድል ነበረዉ ። ነገር ግን ቡድኑ እንደዉ ዕድል በሆነ አጋጣሚ ኢትዮጵያን ገዛ እንጂ፣ ዓላማው ትግራይ ሪፐብሊክ እንደነበር የሚታወቅ ነዉ። ለዛም ነዉ ገንጣይ አስገንጣይ፣ የናት ጡት ነካሽ የሚል ተቀፅላ የተቸረው። ስለሆነም ኢትዮጵያ የምትባል አገር ትግራይ ሪፐብሊክን ለመመሥረት እንደመጠቀሚያ እንጂ፣ ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ነች ብለው አስበዉ አያውቁም ።ከዛ ይልቅ እንደፈለጉ ከጋጧት፣ እንደሸንኮራ ከመጠጧት በኋላ ለተለያዩ የጎበዝ አለቆች አስረክበው ሲሄዱ፣ ዉሾቹ እርስበርሳቸው እንዲናከሱ በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ትግራይን አገር የማድረግ ዓላማ ቡድኑ አንግቦ ስለተነሣና ዕቅዱም ስለነበር ነዉ። ይሄ መሬት ላይ ያለ ሐቅ መሆኑ ለመረዳት ብዙ ርቀት መጓዝ አይጠይቅም።

ከፌዴራል መንግሥት ተነጥለው ትግራይ ከገቡ በኋላ ያደረጉት የመጀመሪያው አገር መሰል (Defacto-State) እንመሠርታለን ማለት ነው። ከዛም ትግራይ ልዩ ኃይልን ስም ቀይረው የትግራይ መከላከያ ኃይል ብለዉ መሠየማቸዉ ሌላዉ አስቂኙ ተግባር ነው። ትግራይ ትስዕር (ታሸንፋለች) የሚለው የደብረጺዮንና ጌታቸዉን ቅዠትና የሔዱባቸዉን ርቀቶች ማሳያ ነዉ። እነዚህ አካላት በኢትዮጵያ አንድነት አምነው አብረዉ ለመጓዝ ያለመፈለጋቸዉ ማሳያው ለመነጋገርና ዕርቅ ይወርድ ዘንድ በርካታ የሽምግልና ሥራ ተሰርቶ ተቀባይነት በሰዎቹ በኩል አለማገኘቱ ነው። ስለዚህ ይህ ቡድን በያዘዉ ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ምክንያት፣ ብዙ ጉዳዮች ላይ ምሁራን ተወያይተው ማቃለል ይቻል የነበረዉ ነገር የበለጠ ሀገሪቱን በችግር ተብትቦ ሊያሠምጣት ጥቂት ቀርቶ ነበር። ነገር ግን ሳይደግስ አይጣላም እንደሚባለዉ አምላክ ኢትዮጵያን ከመከራ በልጆቿ ታንሠራራ ዘንድ በዕብሪት ተወጥሮ የነበረው የህወሓት ሥርአትን በቃኝ የሚል ወጣት ከየቦታዉ ወጣ። ከታንክ አፈሙዝ ጋር ራሱን አጋፈጠ፤ በመጨረሻም ህወሓት ከቤተ-መንግሥቱ ወደ መቐለ እንዲሸሽ ተገደደ ።

ህወሓት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ በአፍጢሙ እንዲደፋ ከተደረገ በኋላ፣ ሊበጠሱ የደረሱ ገመዶችን በኢትዮጵያዊነት የመጠገን ሥራ ተሠርቷል። ኢትዮጵያ የምትባል አገር ለመጥራት የኪሊማንጃሮ ተራራን መውጣት ያህል የሚገዝፍበት፣ በምትኩ ጥላቻና ፅንፍ የረገጠ ዘረኝነት ሲሰብክ ከነበረው የህወሓት ሥርዓት ወጥቶ፣ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ወደሚል የአንድነትና የወንድማማችነት መንፈስ በሕዝቡ እንዲዘራ በሚያደርግ ትኩስ ኃይል ተለወጠ። በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ አዲስ የአብሮነት መንፈስ ተስፋ መፈንጠቅ ጀመረ። በርካታ ኢትዮጵያዊ በእንባ ተራጨ። በአዲስ መልክ መቀራረብ መወያየት ተጀመረ። አምባገነኑ የወያኔ ሥርዓት የከሰሰዉን፣ የበደለዉን፣ ያጠፋዉን ሁሉ በይቅርታ እንሻገር የሚል በር ወለል ተደርጎ ተከፈተ። ከአገር ዉጪ የነበሩ ወደ አገር ቤት ገብተዉ እንዲሣተፉ ተደረገ።

ከዉስጥ የወጣው አዲሱ የለውጥ ኃይል በአገሪቱ እስከምርጫ በሚኖራት ጊዜ ሊከወኑ የሚገባቸው መሠረታዊ ወሳኝ ወሳኝ ጉዳዮች ዙሪያ ከተለያዩ ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር መክሯል ። ለምሳሌ በተቋማት ግንባታ ዙሪያ፣ በደኅንነት ክፍሉ፣ በምርጫ ቦርድ፣ ወዘተ. ላይ ተወያይቷል። በሌላም በኩል የሠላም ሚኒስቴር የሠላም ጉዳዮችን እያየ እንዲፈታ፣ የድንበር ኮሚሽን ከድንበር ጋር በተያያዘ ያሉ ግጭቶችን ለማስወገድ፣ በጥናት ላይ የተመረኮዘ ሥራ እንዲሠራ ማቋቋም፣ የመሣሠሉትን መጥቀስ ይቻላል ። ከዚህ ባለፈ እንደ ‹Destiny Ethiopia› የመሳሰሉ ትላልቅ በጥናት ላይ የተመሠረቱ የመፍትሔ ንድፈ ሃሣቦችም በተወሰነ መልኩ እየሄዱ እንደነበር አስታዉሳለሁ ። ሌላዉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከተለያዩ ምሁራን ጋር እስከቅርብ ጊዜ ውይይት እየተደረገ ይገኛል። ይሄን ሁሉ የማነሣዉ የብልጽግና አባዜ ልክፍት ስላለብኝ አይደለም፤ ነገር ግን የሐሣብ ፍጭት ላይ የመጡ የተሻለ ግንዛቤና መሻሻል ስላለ ያቺኑ ለማስቀመጥ ነዉ ።

በኢትዮጵያ ከምርጫው መደረግ በኋላ በቀጥታ ወደ አገራዊ መግባባት መድረክ እንሄዳለን የሚል በአብዛኛው ዘንድ ሲጠበቅ የነበረ ነገር ነዉ። ነገርየዉ ግን፣ በነበረ አገራዊ ዉጥረት ሳቢያ የተመቻቸ አገራዊ የጥሞና ጊዜ አላገኘም ነበር ማለት ይቻላል። ህወሓት ከወረራቸዉ ሥፍራዎች እንዲለቅ ከተደረገ በኋላ በቅርቡ በአገራዊ መግባባት ዙሪያ መክሮ ኮሚሽን ለማቋቋም ተደጋጋሚ ስብሰባ ያደረገዉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በአገሪቱ ባሉ ኢትዮጵያዉያን ባልተግባቡባቸዉ ጉዳዮች ዙሪያ እና በወደፊቷ በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ለመመካከርና ለመወያየት መግባባት ላይ ለመድረስ የብሔራዊ መግባባት ኮሚሽን በአብላጫ ድምፅ ተቀባይነት አግኝቶ በዐዋጅ እንዲቋቋም ጸድቋል ።

ዐዋጁ ስለኮሚሽኑ የተለያዩ ጉዳዮችን ይዟል። ለምሳሌ ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለሕ/ተ/ም/ቤት ሲሆን፣ የኮሚሽኑ ዓላማዎች ሰባት ናቸው፡- ላለመግባባት መንስኤ ናቸዉ የሚሏቸውን አጀንዳዎች በሙሉ በብቃት መለየት፤ የዉይይት አጀንዳ ማፍለቅ፤ በልኂቃን፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያሉ ያለመተማመን ችግሮቻቸዉን በመግባባት መፍታት፤ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓትና ማኅበረሰብ መፍጠር፤ ጠንካራ አገረ-መንግሥት ለመገንባት ፅኑ መሠረት መጣል ነዉ። ኮሚሽኑ በዐዋጁ እንደተቀመጠዉ ገለልተኛና ከዉግንና የፀዳ መሆኑን ያስቀምጣል ። የኮሚሽኑ ተግባርና ኃላፊነቶች በተመለከተ ወደ 13 የሚደርሱ ነጥቦች ተዘርዝረዋል። ነጥቦቹ ብዙ ስለሆነ ቦታ ለመቆጠብ ይቻል ዘንድ አንባቢ ዐዋጁን አግኝተው እንዲያነቡት ይመከራል። ኮሚሽኑ የሚመሩት ሰዎች በሕዝብ ጥቆማ መሠረት ለዕጩነት የሚቀርቡ እንደሚሆንና የሚጠቆሙ ሰዎች ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆኑ፣ ኹሉንም በዕኩል ዐይን የሚያዩ፣ ፈቃደኛ የሆኑ ይላል። በወጣው የጥቆማ መሥፈርት መሠረት ዜጎች ለአገራዊ መግባባት ኮሚሽኑ ያግዛሉ ብለዉ የሚያስቧቸው ግለሰቦችን እየጠቆሙ ይገኛል ።

በተለያየ ጊዜ አገራዊ መግባባትን ድርድር በሚል የተለያዩ ሰዎች በተለያየ መንገድ ሲተረጉሙት ነበር። ነገር ግን መንግሥት በተደጋጋሚ አገራዊ መግባባት እንጂ ድርድር እንዳልሆነ በሽብር የተፈረጁ ድርጅቶች (ህወሓትና ሸኔ) እንደማይወከሉ አቶ ሬድዋን ሑሴን በተደጋጋሚ ገልፀዋል።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ታሪክ ሥልጣን በአፈሙዝ፣ ፖለቲካዉ አፈሙዝ መሠረት ያደረገ እንደነበር ይታወቃል። በዚህም የተነሣ በንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ በተማሪዎች ሲጠየቅ የነበረዉ ጥያቄ ሳይመለስ ወደደርግ፣ ከደርግ ወደ ህወሓት የተላለፉ ክምር አጀንዳዎች ሳይዘጉ ሲንከባለሉ የዚህ ትዉልድ ጫንቃ ላይ አርፈዋል ። አንዱ ሌላዉን በኃይል የሚገረስስበት የፖለቲካ ባህል ስንት ትዉልድ እንዳመከንን የመጣንበት ታሪካችን ማሳያ ነዉ። ያሉን የተዛቡና ጫፍና ጫፍ ፅንፍ የረገጡ ትርክቶች፣ የሥልጣን ጥሙ፣ ዝናዉ፣ እወደድ ባዩ፣ የጎበዝ አለቃዉ ብዙ የነበረበትን የፖለቲካ ሒደት የምናዉቀዉ ነዉ። እነዚህ ፖለቲካዊም ሆነ በታሪክ ዙሪያ ያሉን የተዛቡ አመለካከቶችንና የማኅበረሰብ ቅራኔዎችን ለመፍታት የሚቻለውና የጥላቻ ምሽጎች የሚደረመሱት እንደነዚህ ባሉ ጉዳዮች በጠረጴዛ ዙሪያ በሐሣብ ተመካክሮና ተፋጭቶ አገራዊ መግባባት ላይ መድረስ ሲቻል አሊያም ሲሠራ ነዉ።

አገራዊ መግባባት ብዙ ብዥታዎችን አጥርቶ አዲስ ዘመናዊ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ይፈጥራል፤ ይሄ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ይጠቅማል። በአጠቃላይ የተሳካ አገራዊ መግባባት፣ የጋራ ጠንካራ አገረ-መንግሥት እንዲኖር ያደርጋል። የብሔራዊ የመግባባት ኮሚሽን ከነዚህ ውጤቶች (outcomes) ባሻገር ስናየዉ እጅግ ጥቅሙ የጎላ፣ ምንም ጉዳት የሌለው በመሆኑ ይበል የሚያሠኝ ተግባር ነዉ። እንደ ትዉልድ በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ፣ ተነጋግሮ ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ማሠብ ትልቅ ዕርምጃ ነዉ። ፈጣሪ ልቦናችንን ይክፈትልን እያልኩ ተሰናበትኩ።

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር !
ጁሃር ሳዲቅን በኢሜል አድራሻቸው colomunistjuhare@gmail.com ያገኙዋቸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here