የገና በዓል ገበያ እንዴት ዋለ?

0
1814

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በድምቀት ከሚከበሩ ዓመታዊ ክብረ በዓሎች መካከል በተለይ በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የገና በዓል ነው። የገና በዓል ሲታሰብ የተለያዩ የበዓል ማድመቂያ ዝግጅቶች ይከናወናሉ።
የገና በዓልን ከቤተሰብ እስከ ወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ ማክበር የተለመደ ነው። ታዲያ ዘመድ አዝማድ በዓሉን በጋራ የሚያከብረው ለቀኑ የሚሆኑ አልባሳትን፣ ምግብ እና መጠጦች ከወትሮው በተለየ በማዘጋጀት ነው።

በዓሉን ለማድመቅ የሚያስችሉ የበዓል ምግቦችን ማዘጋጀት እና በበዓል አልባሳት መድመቅ መሠረታዊ ጉዳይ ነው። የገና የበዓል ገበያ ከወትሮው በተለየ ኹኔታ ድምቀት ይታይበታል። አዲስ ማለዳ በገና የበዓል ገበያዎች ላይ በመገኘት በተለይ በባህል አልባሳት፣ በእንሰሳት ተዋጽዖ፣ በዕርድ እንሰሳት፣ በአትክልት እና በሌሎችም የበዓሉ ግብይቶች ላይ ቅኝት አድርጋለች።

የዘንድሮው የገና የበዓል ገበያ በኢትዮጵያ ካለው ወቅታዊ ኹኔታ አንጻር እንደ ሠላሙ ጊዜ ባይሆንም የተወሠነ ድምቀት ታይቶበታል። የበዓል ገበያ ቅኝቱን የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ በተለያዩ የገበያ ቦታዎች ተገኝቶ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

በኢትዮጵያ በድምቀት ከሚከበሩ ዓመታዊ ክብረ-በዓላት መካከል በተከታታይ የሚከበሩት የገና እና የጥምቀት በዓላት ዋናዎቹ ናቸው። ኹለቱ በዓላት በአብዛኛው በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚከበሩ ሲሆን፣ የገና በዓል በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 ሲከበር፣ የጥምቀት በዓል ደግሞ ጥር 11 ላይ ይከበራል።

የዘንድሮው የገና በዓል ከትላንት አርብ ማለትም ከታኅሣሥ 29/2014 ጀምሮ፣ ዛሬን ጭምር አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል በየቤቱ የሚያከበረው ደማቅ ዓመታዊ ክብረ-በዓል ነው። ዓመታዊ ክብረ በዓል፣ በበዓሉ አክባሪዎች ዘንድ የሚፈጥረው አዲስ ድባብ ይኖራል። በዓል እንዲደምቅ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል በየቤቱ የሚዘጋጁ የበዓል ምግቦች፣መጠጦች እና ሌሎች ተጨማሪ የበዓል ዝግጅቶች የሚጠቀሱ ናቸው። በዕለቱ ዘመድ አዝማድ፣ ጎረቤት ተሰባስቦ በጋራ እየተመገበና እየተዝናና የሚያከብረበት ስለሆነ የበዓሉን ቀን ከሌላው ቀን የተለየ ድባብ ይሰጠዋል። ታዲያ ይህ የበዓል ድባብ እንዲመጣ አስቀድሞ ለበዓሉ ማድመቂያነት የሚያገለግሉ የተለያዩ የምግብ ግብዓቶች እና አልባሳት ይሸመታሉ።

ገና በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት አንዱ መሆኑን ተከትሎ፣ በበዓሉ ሰሞን በተለይ በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ከዶሮ እስከ ሠንጋ የሚደርሱ የዕርድ እንሰሳትን ከማዘጋጀት ጀምሮ፣ እስከ ቅመማ ቅመሞች ዝግጅትና ሸመታ ድረስ ይከናወናል። አዲስ ማለዳ የዘንድሮውን የገና በዓል መነሻ በማድረግ፣ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የገበያ ቦታዎች እና በዓሉን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጁ ኤግዚቢሽኖች ተገኝታ የበዓል ገበያውን ተመልክታለች።

የዘንድሮው የገና በዓል አሁን ካለው አገራዊ ወቅታዊ ኹኔታ አንጻር በኹሉም የበዓሉ አክባሪዎች ዘንድ እንደከዚህ ቀደሙ በደስታ በታጀበ ድባብ ይከበራል ተብሎ ባይታሰብም፣ የሚስተዋለው የገበያው ድምቀት ግን በዓሉ የተሻለ ድባብ እንዲኖርው አድርጎታል። በኢትዮጵያ አሁን ያለው ወቅታዊ ኹኔታ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የመጣው የዋጋ ግሽበት፣ አሁን ያለው የበዓል ገበያ የዛሬ ዓመት ከነበረው የገና በዓል ገበያ ጋር ሲነጻጸር የሚታየው የዋጋ ልዩነት ቀላል የሚባል አይደለም።

የበዓል ኤግዚቢሽን ገበያ
አዲስ ማለዳ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ በተዘጋጁ ኤግዚቢሽኖች ላይ ተገኝታ እንደታዘበችው ከሆነ፣ በኤግዚቢሽኖቹ ከግብርና ምርቶች እስከ ኢንዱስትሪ ውጤቶች ድረስ ያሉ አስፈላጊ የበዓል ግብዓቶች ለገበያ ቀርበዋል። ለበዓል ገበያ በኤግዚቢሽኖች ላይ ለግብይት ከቀረቡ ምርቶች መካከል በዋናነት አልባሳት እና የግብርና ምርቶች ይጠቀሳሉ።

በአዲስ አበባ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች ኤግዚቢሽኖች የተዘጋጁ ሲሆን፣ አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ ከተመለከተቻቸው መካከል በአዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል፣ በአፍሪካ ፓርክ፣ በወዳጅነት ፓርክ እና አራት ኪሎ መስመር ላይ የተዘጋጁት ይጠቀሳሉ። አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ ከተመለከተቻቸው መካከል በወዳጅነት ፓርክ በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን ላይ በአብዛኛው ኢትዮጵያ ውስጥ የተመረቱ የቆዳ ውጤቶች እና የባህል አልባሳት ለገበያ ቀርበዋል።

በፓርኩ የተዘጋጀው ኤግዚብሽን ትኩረቱ በኢትዮጵያ የተመረቱ የፋብሪካ ውጤቶችን ማስተዋወቅ ሲሆን፣ መንግሥት አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች የገናን በዓል ኢትዮጵያ ገብተው እንዲያከብሩ ጥሪ ማድረጉን ተከትሎ፣ በአብዛኛው ዳያስፖራው የኢትዮጵያን ምርት እንዲጠቀም ዕድል መፍጠር ላይ መሠረት ያደረገ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኤግዚብሽኑ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

አራት ኪሎ በተዘጋጀው የመስመር ላይ ኤግዚቢሽን፣ ለገበያ ከቀረቡት ምርቶች መካከል የተለያዩ ከቆዳ የተሠሩ አልባሳት፣ የባህል አልባሳት፣ እንዲሁም እንደ ቅቤ፣ ማር እና ጠጅ የመሳሰሉ የምግብ ግብዓቶች ይገኙበታል። በኤግዚብሽኑ ላይ በተለይ ከቆዳ የተሠሩ አልባሳት ከወትሮው ገበያ መጠነኛ ቅናሽ ተደርጎባቸው ለግብይት የቀረቡ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት በመደበኛ ገበያ ከሚሸጡበት ዋጋ በአንድ ዕቃ ላይ ከ200 መቶ እስከ 500 ብር ቅናሽ አድርገው እየሸጡ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኤግዚቢሽኑ ተሳታፊዎች ጠቁመዋል።

ባለፈው ሳምንት ዕድሳት ተደርጎለት ሥራ በጀመረው በአፍሪካ ኅብረት ፊት ለፊት በሚገኘው አፍሪካ ፓርክ በተዘጋጀው የበዓል ኤግዚቢሽን ለገበያ የቀረቡት የተለያዩ የባህል አልባሳት ሲሆኑ፣ ለወንዶችና ሴቶች ተብለው ለገበያ የቀረቡት አልባሳትም በተለያዩ ዲዛይኖችና በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያሸበረቁ ናቸው። ለገበያ የቀረቡት የኢትዮጵያን ባህል የሚያንጸባርቁ ባህላዊ አልባሳት፣ በመደበኛ ሱቅ ውስጥ ከሚሸጡበት ዋጋ የተወሰነ ቅናሽ ተደርጎባቸው ለገበያ እንደቀረቡ በኤግዚቢሽኑ የባህል አልባሳት ስትሸጥ ያነኘናት ወጣት ዮርዳኖስ ከበደ ትገልጻለች።

ዮርዳኖስ ለገበያ ካቀረበቻቸው የባህል አልባሳት መካከል በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ያሸበረቁ ይገኙበታል። የመሸጫ ዋጋቸው ከ500 እስከ 1700 ብር እንደሚደርስ አዲስ ማለዳ ተመልክታለች። ዮርዳኖስ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸችው ከሆነ፣ በኤግዚቢሽኑ ላይ የተሳተፈችው የበዓል ገበያ ተሣታፊ ለመሆን እና ለገበያ የምታቀርባቸውን የባህል አልባሳት ለማስተዋወቅ መሆኑን ጠቁማለች።

ወቅቱ የገና እና የጥምቀት በዓላት በተከታታይ የሚከበሩበት ጊዜ መሆኑን ተከትሎ፣ በኢግዚብሽኖች የበዓል ገበያ ላይ በአብዛኛው የሚፈለጉት የባህል አልባሳት መሆናቸውን የምትገልጸው ዮርዳኖስ፣ የበዓል መድመቂያ አልባሳት በብዛት እንደሚሸጡ ትገልጻለች።

የዕርድ እንሰሳት ገበያ
በኢትዮጵያ ዓመታዊ ክብረ በዓላት የሚከበሩበር ኹኔታ ከወትሮ በተለየ እና ልዩ ስሜት በሚፈጥር ድባብ ነው። ክብረ በዓላትን ልዩ ከሚደርጋቸው መካከል፣ በበዓሉ አክባሪ ማኅበረሰብ ዘንድ ከአመጋገብ እስከ አለባበስ ከወትሮው በተለየ የሚሠጠው ልዩ ትኩረት ነው።

የገና በዓል ደግሞ በተለይ በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት መካከል አንዱ ነው። የገና በዓልን ከሌሎች በዓላት ልዩ የሚደርገው፣ ከገጠር እስከ ከተማ ያለው የማኅበረሰብ ክፍል ከሠንጋ እስከ ዶሮ እንደየአቅሙ ዕርድ የሚያከናውንበት በዓል መሆኑ እንደሆነ ይነገራል።

አዲስ ማለዳ የገና በዓል የዕርድ እንስሳት ገበያን በተወሰኑ የገበያ አካባቢዎች ተገኝታ ቅኝት ለማድረግ ሞክራለች። አዲስ ማለዳ የዕርድ እንሰሳት እና የእንሰሳት ተዋፆዖ ገበያን ቅኝት ለማድረግ በተገኘችባቸው የገበያ ቦታዎች ላይ፣ እንደየ አካባቢው የገበያ ዋጋው ልዩነት እንዳለው ተመለክታለች።

በገና በዓል ለገበያ ከሚቀርቡ የዕርድ እንሰሳት መካል ዶሮ አንዱ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ በዶሮ ገበያ ላይ እንደየአካባቢው የዋጋ ልዩነት መኖሩን አዲስ ማለዳ ታዝባለች። አዲስ ማለዳ የዶሮ ገበያን ለመቃኘት ከተገኘችባቸው አካባቢዎች መካከል በብዛት ዶሮ ግብይት ይካሄድበታል ተብሎ በሚታሰበው ሾላ ገበያ ሲሆን፣ ሾላ ገበያ ላይ በብዛት ዶሮ ቀርቧል። በሾላ ገበያ የአንድ ዶሮ ዋጋ እንደየዶሮው መጠን ወይም ክብደት ከ300 እስከ 500 ብር ሲሸጥ አዲስ ማለዳ ተመልክታለች። በአዲስ አበባ ሰሚት አካባቢ በሚገኙ ገበያዎች ደግሞ በአንጻሩ አንድ ዶሮ እስከ 600 ብር እየተሸጠ መሆኑን አዲስ ማለዳ ታዝባለች።

ለበዓሉ ዶሮ የገዛ ሰው አብዛኛውን ጊዜ እንቁላል መግዛቱ የማይቀር ጉዳይ ሲሆን፣ በገና በዓል ከዶሮ ገበያ ጋር አብሮ የሚያያዘው የእንቁላል ገበያ ምን እንደሚመለስል አዲስ ማለዳ ለመመልከት ባደረገችው ጥረት የዋጋ ልዩነቱ እንደየ አካባቢው የተለያየ ቢሆንም፣ አዲስ አበባ ውስጥ አንድ እንቁላል ከአምስት ብር ከ50 ሳንቲም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ተመልክታለች።

ኢትዮጵያውያን በበዓላት ወቅት በብዛት የሚሠሩት የዶሮ ወጥ እንደመሆኑ መጠን፣ ለግብዓትነት የሚጠቀሟቸው እንደ እንቁላል ያሉ ምርቶች በበዓል ወቅት የዋጋ ጭማሪ የሚያሳዩበት ሁኔታ ያጋጥማል። በ2013ቱ የገና በዓል ላይ እንቁላል በአምስት እስከ ስድስት ብር መሸጡ የሚታወስ ሲሆን፣ በዘንድሮው የበዓል ገበያ የእንቁላል ገበያ እስከ ሦስት ብር የዋጋ ልዩነት አሳይቷል።

ለገና በዓል ለገበያ ከሚቀርቡ የዕርድ እንሰሳት መካከል በግ እና ፍየል ይገኙበታል። አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ ያለውን የበግ እና ፍየል ገበያ በተወሰኑ የገበያ አካባቢዎች ቅኝት አድርጋለች። አዲስ ማለዳ በቅኝቷ ከደረሰችባቸው የበግ እና ፍየል መሸጫ ገበያዎች መካከል ካዛንችስ አካባቢ የሚገኙ ነጋዴዎችን አነጋግራለች።

በካዛንችስ የበግ እና ፍየል መሸጫ ገበያ የሚገኙ የበግ ነጋዴዎቹ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ዝቅተኛው የአንድ በግ ዋጋ ሦስት ሺሕ ብር ሲሆን፣ ከፍተኛው ደግሞ እስከ ስድስት ሺሕ ብር እየተሸጠ ነው። አዲስ ማለዳ ያጋገረቻቸው ነጋዴዎች በብዛት ለገበያ ያቀረቡት በግ ቢሆንም፣ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ፍየሎችንም ይዘዋል። ነጋዴዎቹ ለገበያ ያቀረቧቸው ፍየሎች መጠናቸው ከአነስተኛ አስከ መካከለኛ ሲሆን፣ በዋጋ ደረጃም ከ4000 አስከ 5000 ብር እየተሸጡ ነው።

ሌላኛው በበዓል ወቅት በብዛት ለገበያ የሚቀርበው እንሰሳት ተዋፆዖ ቅቤ ሲሆን፣ አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ በታዘበችው የሾላ ገበያ ውስጥ የአንድ ኪሎ ቅቤ ዋጋ ለጋ ቅቤን ጨምሮ ከ300 እስከ 450 ብር እየተሸጠ ነው። የቅቤ ገበያ ከባለፈው የገና በዓል ጋር ሲነጻጸር በአንድ ኪሎ እስከ 80 ብር ጭማሪ አሳይቷል።

ለበዓል ሥጋ መብላት ፈልጎ አቅሙ ለማይችል ሰው ደግሞ በአማራጭነት ሥጋ በኪሎ መግዛት ቢፈልግ በሸማቾች ሱቅ በኩል ባሉ ሥጋ ቤቶች አንድ ኪሎ ሥጋ እስከ 250 ብር ሲሸጥ፣ በአንጻሩ በሌሎች ሥጋ ቤቶች አንድ ኪሎ ሥጋ እስከ 500 ብር እየተሸጠ ነው።

በሌላ በኩል የበዓል የአትክልት ገበያ አሁንም በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች እንደየ አካባቢው መሸጫ ዋጋው የተለያየ ቢሆንም፣ አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት ከ25 ብር እስከ 34 ብር መሸጡን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች። የሽንኩርት ገበያ የበዓል ሰሞን ከመድረሱ በፊት አንድ ኪሎ ሽንኩርት ከ25 ብር በታች እየተሸጠ እንደነበር አዲስ ማለዳ ከነጋዴዎች ሰምታለች።

ነጭ ሽንኩርት እንደየ አካባቢው ልዩነት ቢኖረውም ከ30 ብር እስከ 60 ብር በኪሎ እየተሸጠ መሆኑን አዲስ ማለዳ ታዝባለች። የሽንኩርት ገበያ ከባለፈው የገና በዓል ገበያ ጋር ሲነጻጸር በተለይ በቀይ ሽንኩርት ላይ በአንድ ኪሎ እስከ 14 ብር ጭማሪ አሳይቷል። የዛሬ ዓመት የነበረው የአንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩት መሸጫ ዋጋ ከ13 እስከ 16 ብር ነበር።

አዲስ ማለዳ የበዓል ገበያውን ተዘዋውራ እንደተመለከተችው፣ የአንድ ሊትር ፈሳሽ የምግብ ዘይት መሸጫ ዋጋ እስከ 120 ብር መድረሱን ተመልክታለች። ባለፈው ዓመት የገና በዓል ገበያ ላይ አንድ ሊትር ፈሳሽ የምግብ ዘይት እስከ 95 ብር ሲሸጥ እንደነበር የሚታወስ ነው።

በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ የመጣው የዋጋ ግሽበት በበዓል ገበያ ላይ መጠነኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነጋዴዎች ጠቁመዋል። በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ ያሉ የጸጥታ ችግሮች በአቅርቦት እና ፍላጎት አለመጣጣም ላይ ያሳደሩትን ጫና ተከትሎ፣ በተለይ በበግ ነጋደዎች በኩል የሚፈልጉትን ያክል አማራጭ ማቅረብ እንዳልቻሉ ጠቁመዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በአዲስ አበባ፣ በበዓላት ወቅት የኅብረት ሥራ ማኅበራት የበዓል ገበያን ለማረጋጋት የተለያዩ የበዓል ግብዓቶችን ማቅረብ ጀምረዋል። በዘንድሮውም የገና በዓል በአዲስ አበባ ከተማ በዓሉን የሚያከብረው ሕብረተሰብ የተለያዩ ግብዓቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የተለያዩ ግብዓቶችን አቀርበዋል ተብሏል።

በበዓሉ በኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካይነት ለኅብረተሰቡ ይቀርባሉ ከተባሉት ምርቶች መካከል 14 ሺሕ ኩንታል ቀይ ሽንኩርት፣ 6 ሺሕ 210 ዶሮ፣ 760 ሺሕ እንቁላል፣11 ሺሕ 575 ኪሎ ግራም ቅቤ፣ 5 ሺሕ 595 ኪሎ ግራም አይብ፣ 16 ሺሕ 230 ኩንታል የስንዴ ዱቄት፣ 77 ሺሕ ኩንታል ነጭ ጤፍ፣ እንዲሁም 37 ሺሕ ኩንታል ሠርገኛ ጤፍ ይገኙበታል።

 

ተመሳሳይ ርዕሶች

ገናን በላሊበላ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

“የገና በዓል በሰላም እንዲከበር የፀጥታ አካላት ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ተግባር ገብተዋል”፦ ፖሊስ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

“በድል ማግስት ለሚከበረው የገና በዓል እንኳን አደረሳችሁ”፡- የፌዴሬሽን ምክር ቤት – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

የገና በዓል በትግራይ ክልል – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)


ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here