ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገስት ዘ-ኢትዮጵያ ከዛሬ 203 ዓመት በፊት በዛሬዋ ቀን ላይ ተወለዱ

0
1536

አርብ ጥር 6 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ፣ በትውልድ ስማቸው ካሳ ኃይሉ፣ በውትድርና ስማቸው፣ መይሳው ካሳ እንዲሁም ደግሞ በዙፋን ስማቸው ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ከዛሬ 203 ዓመት በፊት ጥር 6/1811 በጎንደር ቋራ ከተማ ተወለዱ፡፡

አባታቸው ደጃዝማች ኃይለጊዮርስ፣ እናታቸው ደግሞ አትጠገብ ወንድወሰን ሲባሉ፤ አባታቸው ደጃዝማች ኃይለጊዮርስ በ1813 በሱዳኖች በመገደላቸውና አትጠገብም ወዲያውኑ ወደ ምንኩስና ህይወት በመግባታቸው ምክንያት፤ ለአፄ ቴዎድሮስ ወንድም ሆነ እህት አልወለዱላቸውም ነበር። ለዚህም ነው ቴዎድሮስ አንድ ለናቱ እየተባለ በታሪክ የሚወሳው፡፡

ታዲያ ካሳ ኃይሉም በዘመነ መሳፍንት ማቀብቂያ 1847 የካቲት 11 ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ በሚል ስም ንግስናውን ተረከቡ፡፡

ቴዎድሮስ ጣዎስ ድሮስ ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን፤ የአምላክ ስጦታ የሚል ትርጓሜንም ይይዛል፡፡

አፄ ቴዎድሮስ እጅጉን አስከፊ ዘመን የሚባለውን ዘመነ መሳፍንት ከኢትዮጵያ ምድር ያጠፉ፣ ስልጣኔን እንደ ውሃ የተጠሙ በጊዜው ከጊዜው ቀድመው የሰለጠኑ ድንቅ ንጉስ እንደነበሩም ታሪክ ይመሰክርላቸዋል።

በ13 ዓመት የንግሥና ዘመናቸው የባሪያ ንግድን በማስቀረት፤ ዘመናዊ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡

ዘመናዊ ጦርን ያደራጁ፣ ዘመናዊ ምሽጎችን የገነቡ፣ ዘመናዊ ሙዚየም ያቋቋሙ፣ የመንገድ ዝርጋታ ያስጀመሩና ብሔራዊነትን የሰበኩ የዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ መነሻ ናቸው ሲሉም ብዙሃን የታሪክ ድርሳናትና ፀሃፍት ስለእርሳቸው ይናገራሉ።

እኚህ ለኢትዮጵያ አንድነትና ዘመናዊነት የታገሉ ታላቅ ንጉስ ታዲያ በ 1860 ሚያዝያ ወር መግቢያ በዕለተ ዓርብ ላይ፤ ራሳቸውን መቅደላ አፋፍ ላይ ለአገራቸው ክብር እና አንድነት ሲሉ ሰዉ፡፡

”መቅደላ ከአፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ፣
የሴቱን አናውቅም፣ወንድ አንድ ሰው ሞተ”

በወቅቱ እንግሊዛዊያን ወደ መቅደላ ሲመጡ 6 ሚሊየን ፓውንድ መድበው፣ 32 ሺህ ዘመናዊ ወታደር ይዘው እንደመጡ ታሪክ ይዘግባል፡፡

ዳግማዊ ሚኒሊክም ለነጭ አልገዛም እጄንም አልሰጥም በሚል የአይበገሬ መንፈስ ለብዙዎች አርዓያ የሚሆን የጀግንነት ጀብዱን በመቅደላ ተራራ ላይ ፈፀሙ።

ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በዚህች ምድር ለ49 ዓመታት የኖሩ ሲሆን አራት ጊዜ አግብተው 6 ወንድ 3 ሴት ልጆች አፍርተዋል።

እነሱም ራስ እንግዳ፣ ራስ መሸሻ፣ ሃይለማርያም፣ አልጣሽ (የምኒሊክ የመጀመሪያ ሚስት) ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ሲሆኑ ብዙዎቹ በመቅደላ ጦርነት ላይ መሰዋታቸውን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here