ሸኔ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በጮቢ ከተማ ከ178 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመንግሥትና የግል ንብረት ላይ ውድመት ማድረሱ ተገለጸ

0
1001

ከ146 ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረውን ጥንታዊውን የጮቢ ደብረ መድሃኒት መድኃኒአለም ገዳምንም ማውደሙም ተነግሯል

 

አርብ ጥር 13 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሸኔ ቡድን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጮቢ ወረዳ በጮቢ ከተማ ሰርጎ በመግባት ከ178 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመንግሥትና የግል ንብረት ማውደሙ ተገለጸ።

የጮቢ ወረዳ አስተዳደርና ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ጨልቀባ ጨቀሳ እንደገለፁት፣ ታኅሣሥ 14 ቀን 2014 የወረዳው መቀመጫ በሆነችው ጮቢ ከተማ ሰርጎ በመግባት ቤተእምነትን ጨምሮ ትምህርት ቤት፣ አምቡላንሶች፣ ጤና ተቋማት፣ የሚሊሻ ቤቶች፣ የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም የመንግሥት አመራር ቤቶች ላይ ጥቃት በማድረስ ሙሉ በሙሉ አውድሟል።

የክልሉ የፀጥታ ኃይል የቡድኑን አባላት ከአካባቢው ለማፅዳት በወሰደው የኦፕሬሽን ተግባር 35 የሚደርሱ የቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውን የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊው ጨልቀባ ገልፀዋል።

እንደ ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊው ገለፃ ይህ የጥፋት ቡድን ሰርጎ በገባበት ወቅት የንፁኃን ሕይወትና ንብረት ማውደሙ እንዲሁም በርካታ አረመኔያዊና ጭካኔ የተሞላበት ተግባር በመፈፀም ፀረ ሕዝብነቱን በግልፅ አሳይቷል።

በከተማዋ የሚገኙ የጤና ተቋማት፣ አምቡላንስና ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ለሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሙሉ በሙሉ በዚህ የሽብር ቡድን የወደሙ መሆኑን የተናገሩት አቶ ጨልቀባ፣ የሚሊሻ ቤቶች፣ ሆቴሎች እና የከተማ ነዋሪዎች ቤቶችም የአሸባሪው ጥቃት ሰለባ ሆነዋል ብለዋል።

ይህ የጥፋት ኃይል በ1868 በአካባቢው ማህበረሰብ እንደተተከለ የሚነገርለትና 146 ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረውን ጥንታዊውን የጮቢ ደብረ መድሃኒት መድኃኒአለም ገዳም ማውደሙም ተነግሯል።

የገዳሙ አገልጋይና ካህን የሆኑት ቄስ ተፈራ ደምሴ እንደገለፁት፣ ይህ ቡድን በታኅሣሥ ወር አጋማሽ ሰርጎ በመግባት በከተማዋ በርካታ ቤቶችና ተቋማት ላይ ጥቃት ካደረሰ በኋላ ይህን ጥንታዊ ገዳም ሊያወድም ችሏል ብለዋል።

ቡልቶ ቱሬ ተብለው በሚታወቁት የአካባቢው አባት የተቋቋመው ይህ ቤተክርስቲያን በውስጡ በርካታ ነዋየ ቅዱሳት፣ ጥንታዊ የብራና መጽሐፍትና ሌሎች የገዳሙ ቅርሶች ሙሉ በሙሉ በዚህ የሽብር ቡድኑ ተዘርፈዋል ብለዋል።

በሌላ በኩል ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ዮሴፍ ጋዲሳ የተባሉ ግለሰብ እንዳሉት የሽብር ቡድኑ መሠረታዊ የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ሙሉ በሙሉ በማውደሙ ምክንያት ማግኘት ያለብንን አገልግሎት እያገኘን አይደለም ሲሉ መናገራቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

አሁንም ይህ የሽብር ቡድን ነዋሪዎች ላይ ስጋት በመጫሩና በቂ የፀጥታ አካላት በአካባቢው ባለመኖራቸው ከዚህ በፊት የተፈጠረው ችግር ዳግመኛ እንዳይከሰት ስጋት አለን በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በከተማዋ የሆቴል ባለቤት የሆኑትና በሽብር ቡድኑ ሙሉ በሙሉ ሆቴሉ የወደመባቸው ዘላለም ግዛው በበኩላቸው፤ የሚሊሻና የመንግሥት የፀጥታ አካላት እንዲሁም የወረዳው የመንግሥት አመራሮች በሆቴሉ መገልገላቸውን እንደ ዋነኛ ምክንያት በመውሰድ ሊወድም መቻሉን አስታውቀዋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here