በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግር እና የተዛባ መረጃ ሥርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ

0
746

በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግር እና የተዛባ መረጃ ሥርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙዎች ማኅበር ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ጥር 07/2014 ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙዎች የጥላቻ ንግግር እና የተዛባ መረጃ ሥርጭት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ስልጠና ሰጥቷል። በስልጠናው ላይ ልምዳቸውን ያካፈሉትና ስልጠና የሠጡት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ነፃነት ተስፋዬ፣ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ በከፋ ደረጃ አገር እና ሕዝብን ከመጉዳቱ በፊት፣ የጥላቻ ንግግር እና የተዛባ መረጃን ለመግታት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ ባለሙያዎች ተግተው እንዲሠሩ አሳስበዋል።
እንደ ነፃነት ማብራሪያ፣ ያልተረጋገጡ እና የተፈበረኩ መረጃዎች በተራቀቀ ቴክኖሎጂ ሳይቀር በመታገዝ ሆን ተብለው አንድን ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ ለማበጣበጥ ታልሞ በመሠራጨት ላይ ናቸው። ስለሆነም ባለሙያዎች የሚደርሳቸውን መረጃ በማረጋገጥ ለሕብረተሰቡ እውነተኛ መረጃ የማድረስ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚደንት ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በበኩላቸው፣ ሙያው ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ባለሙያው በመሰባሰብ እና በጋራ በመሆን መፍትሔ መፈለግ እንዳለበት አሳስበዋል።
ሥልጠና የሰጡት ሌላኛዋ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ምህረት ፍቃዱ፣ ባለሙያው እራሱን በዕውቀት በማሳደግ የጥላቻ ንግግር እና የተዛባ መረጃ ሥርጭት ለመግታት የሚገጥሙ ፈተናዎችን መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል።
ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች በተሳተፉበት በዚህ መድረክ ላይ የተገኙ ሰልጣኞች፣ በኢትዮጵያ ባለው ወቅታዊ የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም ላይ የተሻለ ሥርዓት እንዲዘረጋ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ኹሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ መመካከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 168 ጥር 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here