አንድን ሰው ከትግራይ ክልል ወደ አዲስ አበባ ለማስገባት አዘዋዋሪዎች እስከ 150 ሺሕ ብር እያስከፈሉ ነው

0
3342

የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎች መሀል ከተሞች በማምጣት ሥራ የተደራጁ ሰው አዘዋዋሪዎች በአንድ ሰው ከ80 እስከ 150 ሺሕ ብር እያስከፈሉ መሆኑን አዲስ ማለዳ አዘዋዋሪዎቹን በማነጋገር አረጋግጣለች።

መረጃውን ማግኘት የተቻለው በሥራው የተሰማሩ ሰዎች ጉዳዩን ለማስፈጸም ያመቻቸው ዘንድ በከፈቱት የቴሌግራም ቻናል አማካኝነት ነው።

አዘዋዋሪዎቹ እንደገለጹት ከሆነ፤ የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን ወደ መሀል ከተማ የሚያመጡት ፎርጂድ መታወቂያ በማሠራት እና የቀይ መስቀል የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) አልብሰው ሠራተኛ በማስመሰል መሆኑን በግልጽ አስረድተዋል።

ከተደራጆቹ መካከል ሥሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ ‹‹ቀይመስቀል Transmitter ነኝ። አንድ ሎንግቤዝ እይዛለሁ። ስሄድ የቀይመስቀል ልብስ፤ ፎርጅድ መታወቂያ እና ባጅ በሚሰጠኝ ፎቶ አሠርቼ እወስዳለሁ። የወሰድኩትን ዩኒፎርም ለብሰው በሎንግቤዝ ይዣቸው ነው የምመጣው። እንዲህ ሲደረግ የቀይመስቀል ሠራተኛ ሆኑ ማለት ነው። እስካሁን እንደዛ ነው የማመጣቸው›› በማለት አብራርቷል።

ድርጊቱን የሚያከናውኑት ተደራጅተው ተራ በተራ በመመላለስ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ ነዋሪዎቹን ወደ አዲስ አበባ ለማምጣት የሚያስከፍሉት ብርም ለወንድ እና ለሴት የተለያየ ነው ብለዋል። አንዲትን ሴት ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ ለማምጣት ክፍያው 80 ሺሕ ብር  ሲሆን፤ ለወንድ ደግሞ 150 ሺሕ ብር መሆኑን በሥራው የተሰማሩ አካላት ገልጸዋል።

ለማለፍ ምንም ዓይነት ምክንያት ስለማይኖር እድሜው ከ20 ዓመት በታች የሆነን ሰው ማምጣት እንደማይቻል ተመላክቷል። ከክልሉ ወደ መሀል ከተማ የሚመጡት ሰዎች ግን ምንም ነገር ይዘው መምጣት አይችሉም ነው የተባለው። በተያያዘም ‹‹ብሩን ደግሞ ሳልሄድ ነው የሚከፍለኝ ምክንያቱም ከሄድኩ ኔትወርክ እዛ የለም›› ነው ብለዋል።

ለወንድ ክፍያው ከፍ ያለበትን ምክንያትም፣ ከትግራይ ክልል ይዞ መውጣት አስቸጋሪ ስለሆነ እንዲሁም ለመታወቂያ እና ለአንዳንድ ነገር የማወጣው ብር ከፍተኛ በመሆኑ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል፣ አዘዋዋሪዎቹ ከትግራይ ክልል ውጪ የሆኑና ወደ ክልሉ ለቤተሰቦቻቸው ብር መላክ የሚፈልጉ ሰዎችን በማነጋገር ከሚላከው 30 በመቶ የሚሆነውን ለራሳቸው በማድረግ የማስተላለፍ ሥራቸውን እንዳላቋረጡ ማወቅ ተችሏል።

ከአዘዋዋሪዎቹ መካከል አንዱ ሰሞኑን ወደ ትግራይ ክልል ተጉዞ ሰዎችን ለማምጣት ተረኛ መሆኑን ጠቁሞ፤ ወደ ክልሉ 500 ሺሕ ብር ይዞ እንደሚሄድም ለአዲስ ማለዳ ሙሉ መረጃውን ዘርዝሯል።

ጥሬ ብር የማስተላለፍ ድርጊቱ ከተጀመረ ሰንበትበት በማለቱ በተለይም በድንበር አካባቢ የሚገኙ ኬላዎች የሚገኙ ፈታሾች ጥብቅ ቁጥጥር እያደረጉ መሆኑ እየተነገረ ቢሆንም፤  አስተላላፊዎቹ ግን በተለያዩ ዘዴዎች እየሸወዷቸው ስለመሆኑ በዝውውር ሂደቱ ከተሰማሩ ሰዎች መረጃው ተገኝቷል።

ፈታሾችን የሚያልፉበት ዋነኛው ዘዴ እንዲተላለፍ የተፈለገውን ብር ለብዙ ሰዎች አከፋፍሎ በማስያዝ ነው። እንዲሁ ሲያደርጉ ተነቅቶባቸው በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች እስከመከዳዳትም መድረሳቸው ተሰምቷል።

100 ሺሕ ብር ለሦስት ተከፋፍለው ከቆቦ ወደ አላማጣ ሲጓዙ የተደረሰባቸው ሰዎች ብሩን በመከዳዳታቸው እናትና ልጅ፤ እህትማማቾች ብሎም ጓደኛሞች በመካከላቸው ትልቅ ጥላቻ መፈጠሩን ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ሰዎች ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገረቻቸው የቀይ መስቀል ማኅበር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሰለሞን አሊ፣ የቀይ መስቀልን ዩኒፎርም በማልበስ ሰዎችን ከቦታ ቦታ የሚያዘዋውሩ ሰዎች እስካሁን እንዳላገጠማቸው ገልጸዋል። ሰለሞን ጉዳዩን ከዚህ በኋላ በጥልቀት እንደሚከታተሉ አንስተው፤ ብር በማስተላለፍ ግን ከዚህ በፊትም በአፋር ክልል በኩል በቁጥጥር ሥራ የዋሉ ሰዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here