ሕጉ ይሻር ወይም መብቱ ይከበር!

0
1171

በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነቱ አጠያያቂ ቢሆንም፣ የሕጎች ሁሉ የበላይ እንደሆነ የሚነገርለት ሕገ መንግሥት ተግባር ላይ እስካለ ድረስ ቢያንስ ሥርዓትን ለማስከበር ሲባል መርሁ ሊከበር ይገባል። አጠቃላዩም ሆነ የተወሰነው ክፍል እስካልተሻረ ድረስ ለጊዜውም ቢሆን አንቀጾቹን ማክበር እንደሚያስፈልግ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ኹሉም ከሕግ በታች ነው በሚባልበት የሕግ አስተሳሰብ ውስጥ የምንገኝ ትውልዶች እንደመሆናችን የመረጥነውን የሕግ ክፍል ተግባራዊ እያደረግን ለግላችን የማይጠቅመውን ገሸሽ ማድረግ ሕሊና ካለው ሰው የሚጠበቅ አይደለም።

የኢትዮጵያ ሕጎች ከሞላ ጎደል በጽሑፍ ደረጃ የተሟሉ ናቸው ቢባልም፣ አንዳንድ አንቀፆችና አዋጆች አብረው የማያኗኑሩና አላስፈላጊ ናቸው ተብለው ይታማሉ። ይህ እውነታ በየትኛውም አገር ያለ ሊሆን ቢችልም፣ ጠቃሚ የሆነውና ውዝግብ የሌለበት ያለ ምንም ማመንታት ተግባራዊ ሊደረግ ይገባዋል። አይጠቅምም ተብሎ የታመነበት አልያም ክርክር ያለበትን ደግሞ ስምምነት እስኪደርስ አግዶ ማቆየት ወይም ሽሮ በሌላ መተካት በየጊዜው ከሚነሱ አምባጓሮዎች ሕዝብንም ሆነ መንግሥትን መታደግ ያስችላል።

ይህ ባለመሆኑ ክልል ወይም ዞን አልያም ልዩ ወረዳ እንሁን የሚሉ የሕዝብ ጥያቄዎች እየበረከቱ ይገኛሉ። እንደማኅበረሰቡ ፍላጎትና ለፖለቲካ ያላቸው ንቃተ ሕሊና የሚጠየቅበት ጊዜና ሁኔታ ቢለያይም፣ በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መሰል ጥያቄዎች እንዳሉና ለወደፊቱም እንደሚኖሩ አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች።

እንዲህ ዓይነት ፍላጎቶች እንደሲዳማ ተሞክሮ ደም ከማፋሰሳቸው አስቀድሞ ተቀባይነት ሊያገኙ ይገባል። ማኅበረሰቡ ያለ ምንም ልዩነት ሐሳቦቹን እንደሚደግፍ በሕዝብ ውሳኔም ሆነ በሌላ መንገድ ማረጋገጥ ከተቻለ፣ ያለ ምንም ጉዳት በተቻለ ፍጥነት ተግባራዊ ማድረግ ከመንግሥት ይጠበቃል።

የደቡብ ምዕራብ አዲሱ ክልል፣ ደቡብ ክልል እንደተመሠረተበት በአቅጣጫ ቢሰየምም፣ የነዋሪው ፍላጎትና ምኞትን እስካልተፃረረ ድረስ ውጤታማ ይሆናል ማለት ይቻላል። ለወደፊቱ ሌሎች የገጠማቸውን ዓይነት ፍላጎት በነዚህ አዳዲስ ክላስተሮችም ሊያጋጥም እንደሚችል ገምቶ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግም ያስፈልጋል።

ልክ እንደሲዳማዎች፣ ሕጉ የሚጠይቀውን ያህል የጉራጌ ዞን ነዋሪ የጠየቀው ክልል እንሁን የሚል ፍላጎት መነሳት ከጀመረና ሕጋዊ መስመሩን ተከትሎ መንቀሳቀስ ከጀመረ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ ውጤት ባለመገኘቱ ኅብረተሰቡን እንዳስቆጣ መመልከት ይቻላል። የዞኑ ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ ያሳለፈውን ውሳኔና ያቀረበውን ጥያቄ ወደጎን አድርጎ የራስን መንገድ ለማሳየትና የመንግሥትን አቅጣጫ እንዲከተሉ ማስገደድም ሆነ ጫና ማሳደር ተገቢ እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

ከሲዳማው እልቂትና ውድመት መማር የነበረበት መንግሥት በተለያየ አሻጥር የሕዝብን ፍላጎትና ሕጋዊ መብት ለማገድና ተፅእኖ ለመሳደር ከሚሞክር ይልቅ ተፈፃሚ እንዳይሆን ሕጋዊ ማዕቀፉን ማስቀረት ይችላል። ለአገር አይጠቅምም ብሎ የሚያምንበት ከሆነ እንዳሻው በዘፈቀደ መከልከልና መፍቀድ ሳይሆን ወጥ የሆነ መመሪያ አውጥቶ መፍቀድ አልያም መከልከል ፍትሃዊነትን ያመጣል።

ከጥንት ጀምሮ በነበረው አከላለል መሠረት መቀጠልና ወደነበረው መመለስ አልያም እንደማኅበረሰቡ ፍላጎት እየቀያየሩ እንዳዲስ እያካለሉ መሄድ ይቻላል። አዋጩና ዘላቂ የሚሆነው የትኛው እንደሆነ ለማንም ግልፅ ቢሆንም፣ መንግሥት ከመፈራራት ፖለቲካ ወጥቶ ቁርጡን ለሕዝብ ማሳወቅ ግዴታው ነው።

ሰፋፊ የሆኑት ኦሮሚያና አማራ ክልሎችን መከፋፈሉ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይ ሐሳብ እንደሆነ ቢሰማም፣ ቀድመው ሊያሳንሱን ነው የሚል አስተሳሰብ በሁሉም ዘንድ ስለሰረጸ እኩል በአንድነት ሊደረግ ይገባል። ወለጋ አርሲና ባሌ፣ እንዲሁም ጎንደር ጎጃምና ወሎ በእኩል ጊዜ የየራሳቸው ክልል ቢሆኑ ሥልጣናችን ያንሳል የሚሉ የግል ፍላጎታቸውን ተገን አድርገው በሕዝብ ሥም የሚነግዱ ሊያስቡት የሚገባ ቁምነገር አለ። ሕዝቡ በአንድ ተካለለ ወይም ኹለት ሦስት ቦታ ሆነ፤ አስተሳሰቡና ውግንናው እንደማይለያይ ሊታወቅ ይገባል።

በማኅበረሰቡ ውስጥ ስር ሰዶ የገባው የማንነት ፖለቲካ እስካልተወገደ ድረስ፣ አንድ ክልል ተከፋፍሎ ይቅርና በሌላ ክልል ስለሚኖር ወገኔ ስለሚለው ሲቆረቆር እየተመለከትን፣ ኅብረተሰቡ ለአስተዳደሩ የሚመቸውን ከማድረግ ልንቆጥበው አይገባም።

ደቡብ ክልል ውስጥ ለዓመታት ጥያቄ ቀርቦ እስካሁን ውሳኔ ባለመገኘቱ ስጋት የፈጠረው የይገባኛል መንፈስ፣ ጉራጌና ጋሞን በመሳሰሉ ማኅበረሰቦች ዘንድ ይበልጥ ቅሬታ መፍጠሩ እየተሰማ ይገኛል። ሌሎቹ ማኅበረሰቦች ዘንድ ጥያቄው ቢኖርም ወላይታን በመሳሰሉት ዞኖች የነበረው ጥያቄ በክላስተር ተተክቷል በሚል በይፋ ባይሰማም ለወደፊት ምን ሊያስከትል እንደሚችል መገመቱ ቀላል ነው።

የደቡብ ኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች እያነሱት ያለው ጥያቄ ትኩሳት ሳይበርድ ከወደ ሰሜንም ተመሳሳይ ሐሳቦች መንሸራሸር መጀመራቸውን መመልከት ይቻላል። በተለይ በወሎ ግዛት ውስጥ የቀድሞው ክፍለ ሀገር ክልል ተብሎ ይመለስልን በሚሉና የገዢው ፓርቲና የፅንፈኞች ሴራ ነው በሚል በነዋሪው ዘንድ ልዩነትን እየፈጠረ ይገኛል።

እንዲህ ዓይነት ፍላጎት በሕዝበ ወሳኔ መልስ የሚያገኝ ቢሆንም፣ የእንግሊዝን ሕዝብ ላይመለስ የከፋፈለውን ዓይነት ልዩነት በኅብረተሰቡ ዘንድ ፈጥሮ ደም ከማፋሰሱ በፊት ሁሉም ቆም ብሎ እንዲያስብበት አዲስ ማለዳ ትመክራለች።

መንግሥት እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችም ሆኑ ፍላጎቶች ሕዝብን ከፋፍለውም ሆነ አጨቋቁነው ወደማያባራ ጥላቻ ውስጥ ከመክተታቸው በፊት በጥልቅ አስቦ ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባዋል።

አሁን ላለንበት ማንነታችንም ሆነ አስተሳሰባችን መሠረት የሆነው ነባሩ ስርዓት የወለዳቸውን በጎ ነገሮች በጥላቻ ተመሥርተን ላለመጠቀም መወሰን እንደሌለብን ግልፅ ነው። እንደጉራጌ ዞን ጉዳይ የወሎም ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት በጥልቅ ሊታሰብበት ግድ ይላል።

ባህር ሲያቋርጥ ጀልባው የተነደለበት ቀዛፊ፣ ዳርቻ ደርሶ መሬት ለመርገጥ እስኪደክመው ድረስ በፍጥነት ከመቅዘፍ ይልቅ ቀዳዳውን ለመድፈን ቢሞክር የተሻለ ነው። መወተፊያ ቢያጣ እንኳን በእጁ ሸፍኖ ማዕበሉ የፈጀውን ጊዜ ፈጅቶበት ወደነፈሰበት እንዲወስደው ቢጠብቅ መልካም ነው። በሽንቁሩ የሚገባው ውሃ መች ጀልባውን እንደሚሞላበትና እየከበደው ሲቀዝፍ ጉልበቱ ምን ያህል እንደሚፀናለት ሳያውቅ፣ በግዴለሽነት እየቀዘፍኩ ልሞክር ቢል ሰምጦ በውሃ ተዘፍቆ የመሞት እድሉን ያሰፋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ጀልባዋንም ተረካቢ ወራሾቹ አግኝተው አድሰው እንዳይጠቀሙባት የሚያደርግ የአጥፍቶ ጠፊ ተግባር በቤተሰቡ ላይም ጭምር ከመፈፀሙ በፊት በፍጥነት ሊያስብበት ይገባል።


ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here