በጋዜጣው ዘጋቢ
በጋምቤላ ክልል የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ በ42 ሚሊዮን ብር ወጪ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ሊያስገነባ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ተገንብቶ ይጠናቀቃል የተባለዉ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት፣ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የመሠረት ድንጋይ መጣሉን አዲስ ማለዳ ከጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
ለግንባታው 42 ሚሊዮን 909 ሺሕ 172 ብር መመደቡን ያስታውቀው ክልሉ፣ ግንባታውን በስድስት ወራት ውስጥ ሠርቶ ለማጠናቀቅ እንደሚሠራ ገልጿል። ለአዳሪ ትምህርት ቤቱ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጥ መርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ቴንኩዌይ ጆክ፣ እንዲሁም የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሴ ጋጄትን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሠጥቶ እንደሚሠራ ገልጸው፣ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታም የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ አወንታዊ ሚና እንደሚኖረዉ ተናግረዋል።
የትምህርት ቤቱ የግንባታ ሒደት በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊዉ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባም ጨምረው አስታውቀዋል። የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሴ ጋጄት በበኩላቸው፣ ክልል አቀፍ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ለማስገንባት ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።
የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ይበልጥ ለማሳደግ ባለድርሻ አካለት በጋራ እንዲረባረቡ ጥሪ ያቀረቡት ኃላፊዉ፣ ሴት ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ከማምጣት ባሻገር በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲቆዩና ለውጤት እንዲበቁ ከማድረግ አንፃር የሚገነባዉ አዳሪ ትምህርት ቤት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረዉ ገልጸዋል።
የ‹‹ናይል ሌችዌ ኮንስትራክሽን›› ሥራ አስኪያጅ ቦም ሯች በዕለቱ እንዳሉት፣ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ሕንፃ ግንባታው 12 የመማሪያ ክፍሎችን ጨምሮ የአስተዳደር ቢሮ፣ ካፍቴሪያ፣ አጥርና ሽንትቤቶችን ያካተተ መሆኑን አመልክተዋል።
በሌላ በኩል፣ በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ በተከሠተዉ የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት 7 ሺሕ የሚጠጉ የጋምቤላ ክልል ነዋሪዎች መፈናቀላቸዉን የጋምቤላ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታውቋል። መፈናቀሉ የደረሰባቸዉ በኑዌር ዞን በላሬና በጂካዎ ወረዳዎች ሥር የሚገኙ የ4 ቀበሌ ነዋሪዎች መሆናቸዉ ተመልክቷል።
በደቡብ ሱዳን በኩል በተከሠተዉ የእርስ በርስ ግጭት ሳቢያ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ የጋምቤላ ክልል ሕዝቦች መፈናቀላቸዉ የተገለጸ ሲሆን፣ ከቀያቸዉ የተፈናቀሉት የሕብረተሰብ ክፍሎች ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫናዎች መዳረጋቸዉ የተጠቀሰ ሲሆን፣ የሚመለከታቸዉ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠይቋል።
የተፈናቀሉት በኑዌር ዞን በጂካዎ ወረዳ የሦስት ቀበሌ ነዋሪዎች እና በላሬ ወረዳ ደግሞ የአንድ ቀበሌ ነዋሪዎች መሆናቸዉን የተገለጸ ሲሆን፣ ከተፈናቃይቹ መካከል አብዛኞቹ ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸዉ ተነግሯል። ለተጎጂውቹ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ለማድረግ ከሚመለከታቸዉ የመንግሥት አካላትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ጋር ክልሉ እየሠራ ሲሆን፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትና ተፈናቃዮችም ወደ ቀያቸዉ ለመመለስ ዉይይት መጀመሩ ተጠቁሟል።
ቅጽ 4 ቁጥር 168 ጥር 14 2014



